ወቅታዊ ጉዳይ፡ በአቶ ግርማ የሺጥላ ግድያ ጋር በተያያዘ ማን ምን አለ?

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 20/ 2015 ዓ.ም፡- በትላንትናው ዕለት ሚያዚያ 19 ቀን 2015 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል እና በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የብልፅግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ የሺጥላ እና የግል ጥበቃዎቻቸው ሰሜን ሸዋ ዞን ከመሀል ሜዳ ወደ ደብረ ብርሀን ሲመለሱ ልዩ ቦታው መንዝ ጓሳ አካባቢ በታጠቁ ሃይሎች በደረሰባቸው ጥቃት ሕይወታቸው አልፏል::

በአማራ ክልል ከሌሎች የሀገሪቱ ክልሎች በተለየ የመሪዎች ግድያ እየተበራከተ መጥቷል፡፡ ለምሳሌ ያክል የሸዋሮቢት ከተማ ከንቲባ፣ በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ዋና ክፍል ኃላፊ ኮማንደር ዋጋዉ ታረቀኝ፣ በሸዋ ሮቢት ከተማ የገቢዎች ጽ/ቤት ሰራተኛ በቅርቡ ምንነታቸው ባልታወቀ ታጣቂዎች መገደላቸው የቅርብ ትውስታ ነው፡፡

ከአራት አመታት በፊት በአማራ ክልል ከፍተኛ ባለሥልጣናት ላይ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም የተፈጸመው ግድያን ሌላ ማሳያ አድርጎ መቅረብ ይችላል። በወቅቱ የክልሉን ፕሬዝዳንት ጨምሮ ሶስት ከፍተኛ ባለስልጣናቱን በአንድ ቀን ተገድለውበታል።

በትላንትናው እለትም የፓርቲያቸውን ስራ ሰርተው ሲመለሱ በታጣቂዎች ግድያ የተፈፀመባቸው የክልሉ የብልጽግና ፓርቲ ሃላፊ አቶ ግርማ የሺጥላ በቅርቡ መንግስት የክልል ሀይሎችን መልሶ ለማደራጀት ያሳለፈውን ውሳኔ በመደገፍ ከፊት ሁነው ሲሞግቱ እንደነበር ይታወሳል፤ ይህም በበርካታ የሀገሪቱ የመንግስት እና የፓርቲው መገናኛ ብዙሃን ሰፊ ሽፋን ሰጥተው ዘግበውታል።

የሃላፊውን ግድያ ተከትሎ ከጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ጀምሮ እስከታችኛው የክልሉ የወረዳ አመራሮች ጭምር ድርጊቱን የሚያወግዝ መግለጫዎች አውጥተዋል። አስካሁን ድርጊቱን የሚያወግዝና የሀዘን መግለጫ ከማውጣት ውጭ የገዳዮቹን ማንነት በተመለከተ በግልፅ የተሰጠ መግለጫ  የለም፡፡

በግድያው ዙሪያ ማን ምን አለ?

ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት

አቶ ግርማ የመንግሥትና የድርጅት ሥራዎችን በአካባቢው ላይ ሠርተው ከመሃል ሜዳ ወደ ደብረ ብርሃን እየመጡ በነበረበት ሰዓት መንዝ ጓሳ ላይ በታጠቁ ኢ-መደበኛ ኃይሎች በግል ጥበቃዎቻቸው እና በቤተሰቦቻቸው ላይ ጥቃት መፈጸሙም ገልጿል። በዚህም ግርማ የሺጥላን ጨምሮ የአምስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን አስታውቆ የክልሉ መንግስት የተሰማውን ሀዘን ገልጿል። ድርጊቱ የክልሉን መንግሥትና ህዝብ የበለጠ ያጠናክረዋል ሲል ገልጾ ይህንን የሽብር ሥራ እየሠሩ ያሉ ኃይሎች ላይ የክልሉ መንግሥት የማያዳግም እርምጃ እንደሚወስድ እና የጥቃቱን አድራሾችም ለሕግ እንደሚያቀርብ አመላክቷል፡፡

ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር)

“ሐሳብን በሐሳብ ማሸነፍ ያቃታቸው አካላት የወንድማችንን የግርማ የሺጥላን ነፍስ ነጥቀዋል” ሲሉ የገለጹት ዶ/ አብይ ልዩነትን በሠለጠነ መንገድ መፍታት ባህል በሆነበት ክፍለ ዘመን፣ በሐሳብ የተለየን ሰው ሁሉ በጠብመንጃ ለማሳመን መነሣት የጽንፈኝነት የመጨረሻው ጥግ ነው ሲሉም ግድያውን ኮንነዋል።

ዶ/ር ይልቃል ከፍለ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር

ርዕሰ መስተዳድሩ ድርጊቱ ውድቀትን እንጅ ድልን አያጎናጽፍም፣ ጥፋትን እንጅ ሰላምን አይሰጥም ሲሉ ገልጸው የህዝባችን የቆየ መገለጫው ስርዓታዊነት፣ ፍትሃዊነትና እኩልነት ነው ብለዋል። ከዚህ ታሪኩና ስነልቦናው ጋር የሚቃረኑ ተግባሮች በሙሉ ስርዓት አልበኝነት የወለዳቸው ናቸው ያሉት ይልቃል ከፋለ በህግና ስርዓት እንጅ በደቦ ፍርድ የግልም ሆነ የቡድን፤ እንዲሁም  የህዝብም ሆነ የአገር ጥቅምና ፍላጎት ማሳካት አይቻልም ሲሉ ገልጸዋል። የስርዓት አልበኝነት የመጨረሻ መዳረሻው ጥፋትና መጠፋፋት ነው ሲሉ አሳስበዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአቶ ግርማ የሺጥላ ግድያን አውግዞ አቶ ግርማ በኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል የመቻቻልና የመከባበር  የፖለቲካ ባህል እንዲያብብ፣ አብሮነትና ወንድማማችነት እንዲጠናከርና እንዲፀና  ደከመኝ ታከተኝ ሳይሉ ሲለፉና ሲጥሩ ነበር ብለል። ሀገራዊና መንግስታዊ አበርክቷቸው በኢትዮጵያ የፓለቲካ ታሪክ ማህደር ፈፅሞ የሚዘነጋ አይሆንም ሲል ገልጿል።

ም/ጠ/ ሚኒስቴር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር  አቶ ደመቀ መኮንን

አቶ ግርማ  እና የግል ጠባቂዎቻቸው ላይ የተፈጸመው ድርጊት ፍጹም ተቀባይነት የሌለው፣ የህዝባችንን እሴት የማይመጥን ነውር እና ህገወጥ ድርጊት ነው ያሉት አቶ ደመቀ አቶ ግርማ የህዝብ ህይወት እንዲሻሻል የተሰጠውን ህዝባዊ ኃላፊነት እየተወጣ የሚገኝ መሪ መሆኑን በመግለጽ ህልፈቱ ለክልሉ እና ለሀገሪቱ ህዝቦች ከፍተኛ ጉዳት መሆኑን አስታውቀዋል። መንግስት ይህን ድርጊት የፈጸሙ አካላትን ለህግ በማቅረብ ተጠያቂ እንዲሆኑ እንደሚሰራም ገልጸዋል።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአቶ ግርማ የሽጥላ ላይ የተፈጸመውን የግድያ ጥቃት በጽኑ እንደሚያወግዝ አስታውቆ   የክልሉ መንግስት አመራሮች ላይ ተደጋግሞ እየተፈጸመ ያለው የግድያ ጥቃት ክልሉን የቀውስ ማዕከል የሚያደርግ ፣ የሃገራችንን ሰላም እና መረጋጋት አደጋ ላይ የሚጥል የዜሮ ድምር ፖለቲካዊ ሽብር ውጤት ነው ሲል ገልጿል።

አብን ከዚህ ቀደም በአማራ ክልል አመራሮች ላይ የተፈጸመው የግድያ ወንጀል ተሸፋፍኖ መቅረቱ እና ተጠያቂነት አለመስፈኑ ፣ በክልሉ አመራሮች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት ተባብሶ እንዲቀጥል ምክንያት ነው ሲል እምነቱን ገልጿል።

አሁንም ድርጊቱ አግባብ ባላቸው ተቋማት ሳይጣራ እና አጥቂዎቹ እና አጥፊዎቹ ተለይተው ሳይታወቁ ፣ ከጥቃቱ ፖለቲካዊ ትርፍ ለማግኝት ሲባል በአደባባይ የሚደረጉ ፍረጃዎችን እና መግለጫዎችን እንደሚያወግዝም አስታውቋል።

ከአማራ ክልል ምክር ቤት

የተከበሩ አቶ ግርማ የሺጥላ በክልሉ በሰሜን ሸዋ ዞን ባሶና ወረና ወረዳ ቀይት ምርጫ ክልልን ወክለው መመረጣቸውን እና የክልሉ ምክር  ቤት አባል መሆናቸውን አስታውቆ  በታጠቁ  ፅንፈኛ ኀይሎች በደረሰባቸው ጥቃት የተሰማው ሐዘን መራራ ነው ሲል ገልጿል።

በአማራ ክልል የምሁራን መማክርት ጉባዔ

መማክርት ጉባኤው በአቶ ግርማ የሺጥላ ላይ በታጠቁ ኃይሎች የተፈፀመውን ግድያ  በፅኑ በማውገዝ  የተሰማውን ጥልቅ ገልጾ የሐሳብም ሆነ የፖለቲካ ልዩነቶችን በኀይልና በመግደል ለመፍታት መሞከር ለሕዝባችን እና ሀገራችን ዘለቄታዊ ሰላም አያመጣም ብሏል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

የፌደራሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት “የጽንፈኝነትን ሰይጣናዊነት ያሳየ የግፍ ግድያ” በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫ  አቶ ግርማ የሺጥላ ባደገበት ቦታ መገደሉ የጽንፈኛው ኃይል የመርዝ ፖለቲካ በቀየ የማይወሰን፣ ከጓዳ ጭምር ገብቶ ቤተሰብን የሚበትን ሆኑን አሳይቶናል ብሏል።

አጀንዳ አልባ የጥላቻ ፖለቲካ ዘርተው ጽንፈኝነት በማብቀል ልጆችህን በአደባባዩ የሚቀጥፉ የደም ነጋዴዎችን ማስቆም ካልቻልክ፣ የግፍ በትራቸውን የብዙኃኑን ቤት ማንኳኳቱ አይቀሬ ነው ሲል አሳስቧል። ዓላማቸው  ማተራመስና ሀገራችንን ዕረፍት መንሣት የሆኑ አካላት አሉ ሲል ጠቁሟል።

በተጨማሪም የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ የተለያዩ የክልል መስተዳደሮችም በግርማ የሺጥላ ግድያ የተሰማቸውን ሀዘን ገልፀዋል፡፡ አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.