ግንቦት 26፣ 2014 ዓ.ም፣ አዲስ አበባበ፦አንቡላንስ ተሽከርካሪ 21 ሰዎችን በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሱዳን ለማሻገር የሞከረ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ። የቋራ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት የአንቡላን ሹፌር በአንቡላን መኪና 21 ሰዎችን ጭኖ በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሱዳን ለማሻገር ሲያጓጉዝ ተይዞ ፍርድ ቤት መቅረቡን የምዕራብ ጎንደር ዞን ፍትህ መምሪያ ገለፀ።
ተከሳሹ ንጉሴ መኮነን ከኦሮሚያ እና ከደቡብ ክልል አንስተው ወደ ሱዳን ለመሻገር በተለያዩ ደላሎች አማካኝነት የመጡትን 21 ሰዎችን ግንቦት 14 ቀን 2014 ዓ.ም. ከሌሊቱ 8:00 ኪነቢ ቀበሌ ጋንክ ጎጥ ከደላሎች በመቀበል በቋራ ወረዳ ጤና ጥበቃ ፅ/ቤት የአምቡላንስ መኪና ጭኖ ወደ ሱዳን ለመሸኘት በማጓጓዝ ላይ እያለ ከሌሊቱ 8:00 አካባቢ ገለጉ ከተማ አለሙ በር ተብሎ ከሚጠራው ቦታ ላይ የሚገኘውን ኬላና የፀጥታ ሃይልችን ጥሶ ማለፉን የፖሊሰ የምርመራ መዝገብ ያስረዳል።
የፀጥታ አካላቱም ተከሳሹን ለማስቆም ጥይት ቢተኩሱም ኬላዉን ጥሶ በማለፍ ተዘዋዋሪዎቹን ወደ ጨካ እና ባዶ ቤት የደበቃቸው ቢሆንም ተከሳሹ እና ተዘዋዋሪዎች በፀጥታ ሀይል ክትትል መያዛቸው ተገልጿል።
የቋራ ወረዳ ፖ/ጽ/ቤት የወንጀል የምርመራ መዝገቡን አጣርቶ ለምዕራብ ጎንደር ዞን ፍትህ መምሪያ የወንጀል ዐቃቤ ህግ የላከ ሲሆን የዞን ዐቃቤ ህግም መዝገቡን በመመርመር በተከሳሹ ላይ በሁለት ተደራራቢ ክሶች ማለትም በህገወጥ የሰዎች ዝውውርና በሙስና ወንጀል ረቡዕ ግንቦት 24 ቀን 2014 ዓ.ም. በከፍተኛ ፍ/ቤት ክስ መስርቶበታል።
ተከሳሹም ትናነት ግንቦት 25 ቀን 2014 ዓ.ም በዋለው ችሎት ፍ/ቤት ቀርቦ የክሱ ግልባጭ ደርሶት ክሱ ተነቦለት የእምነት ክህደት ቃሉን ሲጠየቅ “ክሱን አልቃወምም፣ የወንጀል ድርጊቱን አልፈፀምኩም” በማለት ክዶ የተራከረ ሲሆን ዐቃቤ ህግም ተከሳሸ የወንጀል ድርጊቱን ስለመፈፀሙ በሰውና በሰነድ ማስረጃ አረጋግጬ ክስ ሰላቀረብሁ የዐቃቤ ህግ ምስክሮች ይሰሙልኝ በማለት ለፍ/ቤቱ አሳስቦ የዐቃቤ ህግ ምስክሮችን ፍ/ቤቱ አድመጧል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤትም የዐቃቤ ህግ ምስክሮችን ካዳመጠ በሗላ መዝገቡን መርምሮ ብይን ለመስጠት ለሰኔ 02 ቀን 2014 ዓም ቀጠሮ ሰጥቷል።አስ