አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2/2014 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከምዕራብ አርሲ ዞን ፖሊስና ከሌሎች ፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት 122 ኩንታል አደገኛ ዕፅ ይዞ ማስወገዱን አስታወቀ።
በወረዳው ውስጥ አደገኛ ዕፅ ለመቆጣጠር በተከታታይ የፓትሮል ቅኝትና ከፍርድ ቤት የመበርበሪያ ትዕዛዝ በማውጣት ቤት ለቤት በተደረገው ድንገተኛ ብርበራና ፍተሻ አደንዛዥ ዕፁን በቁጥጥር ሥር ማዋል እንደተቻለ የሻሽመኔ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ሽመልስ ቀናው ገልፀዋል።
ከአደገኛ ዕፁ ጋር በተያያዘም አምስት ተጠርጣሪዎች ተይዘው ሕግ ፊት ቀርበው ከሦስት ዓመት እሰከ ስድስት ዓመት የፍርድ ዉሳኔ እንደተሰጠባቸው ኮማንደሩ ተናገረዋል።
ዕፁ የትውልዱን አእምሮ አደንዝዞ ለወንጀል ድርጊት ስለሚገፋፋ በሀገር ላይ የሚያደርሰው ጉዳትና አስከፊነት በመገንዘብ ከሌላው ጊዜ በተሻለ ሁኔታ ቁጥጥርና ክትትል እየተደረገ እንደሆነና አደንዛዥ ዕፅ ያበቅላሉ ተብለው በሚጠረጠሩ ቀበሌዎች ላይ ለሕብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እየተሰጠ እንደሚገኝ ኮማንደሩ አያይዘው ጠቁመዋል።
በወረዳው አደገኛ ዕፅን በዘላቂነት ለማጥፋት የቀበሌ አመራሮችን እና የአካባቢውን ማሕበረሰብ በማስተባበር ከግብርና ባለሙያዎች እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በትኩረት እየተሰራበት መሆኑን የገለፁት ኃላፊው በመሬቱ ላይ ዕፁን የሚያበቅል ገበሬ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድበትና መሬቱም ሳይቀር እንደሚወረስ ገልፀዋል።
በመጨረሻም ዕፁን የሚያመርቱ እና የሚያዘዋውሩ ግለሰቦች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አስጠንቅቀው፤ ይህንንም ተላልፈው በሚገኙ ሰዎች ላይ የተጠናከረ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ አሳውቀዋል ።አስ