አሊ ቢራ ማነው?
አሊ ቢራ ከእናቱ ፋጡማ አሊ እና ከአባቱ መሐመድ ሙሳ በ1941 ዓ.ም ከአዲስ አበባ በስተደቡብ ምስራቅ 515 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ድሬዳዋ ከተማ ተወለደ። አባቱ መሐመድ ሙሳ ከአፍረን ቀሎ ኦሮሞ የዓላ ጎሣ ልጅ ሲሆኑ ግራዋ ከምትባል ከተማ ነው የመጡት። እናቱ ፋጡማ አሊ ድገሞ የአፍራን ቃሎ የጃርሶ ንኡስ ጎሳ አባል ናቸው።
መሀመድ እና ፋጡማ ድሬዳዋ ከተማ ተዋውቀው በ1946/7 ዓ.ም አካባቢ ትዳር መሰረቱ፡፡ በገንደ ቆሬ ሰፈር መኖር የጀመሩት የአሊ ቢራ ወላጆች የመጀመሪያ ወንድ ልጃቸውን በግንቦት 30 / 1941 ዓ.ም. አግኝተው በአያታቸው ስም አሊ ብለው ሰየሙት። አሊ ወንድሙን በአደጋ ካጣ በኋላ ለቤተሰቦቹ ብቸኛ ልጅ ሆነ ቀረ። ከዚህ ክስተት በኋላ ብዙም ሳይቆይ ወላጆቹ ተፋተው የሸሪያ ፍርድ ቤት አባቱ አሊን እንዲያሳድግ ወሰነ።
አሊ ትምህርት የጀመረው ገና በልጅነቱ ነበር። በ5 ዓመቱ ወደ ቁርኣን ትምህርት ቤት ተቀላቀለ። የቁርኣን ትምህርት ቤቶች ከእስልምና ሀገራት የመጡ ስርአተ ትምህርት የሚጠቀሙ ሲሆን ቁርኣንን መማር ትኩረት ከተሰጣቸው የትምህርት ዓይነቶች አንዱ ነው። በ11 አመቱ ከ30 የቁርዓን ጁዝ(ክፍሎች) ግማሹን አጠናቀቀ።
በኢስላም ትምህርት ቤቶች፤ በተለይም በአረብኛ ቋንቋ በጣም ፈጣን እና ንቁ ተማሪ በመሆን በስዎቸ ዘንድ እውቅናን አገኘ። በዚህም የተነሳ ኡስታድ ሳጊሂር (ትንሹ አስተማሪ) የሚል ቅጽል ስም ተሰጥቶታል። አሊ ምንም አይነት አረብኛ የማይሰጥበት እና የማስተማሪያ ዘዴው አማርኛ የሆነበት፤ በከዚራ፣ ልኡል መኮንን ትምህርት ቤት ውስጥ ትምህርቱን ቀጠለ፡፡ ከዚያም የአሊ አባት መሀመድ ልጁን ወደ ዓለማዊ ትምህርት ቤት በመላኩ ከጎረቤቶቹ ትችት ስለገጠመው ከትምህርት ቤቱ አውጥተው ወደ ቁርዓን ትምህርት ቤት መልሰው አስገቡት። ከዚያም ከሶስት ብር ወርሃዊ የትምህርት ክፍያ ነፃ ከመሆን በተጨማሪ በወር አስር ብር ደመወዝ እየተከፈለው አስከ አንደኛ ክፍል አረብኛ ቋንቋን እንዲያስተምር እድል ተሰጠው።
አሊ ከትምህርት ቤት ውጭ የሚዝናናበት ነገሮች ነበሩት። ገና በጨቅላ ዕድሜው፤ ለሙዚቃ እና ለመዝናኛ ያለውን ፍቅር ማሳየት ጅማረ። በትምህርት ቤት እና በሚኖርበት በአካባቢ ውስጥ መዝፈን እና መደነስ ይወድ ነበር፡፡ ከአባቱ ጋር በሲኒማ ቤቶች ፊልሞችን መመልከት እና ከሰፈር እድሜ እኩዮቹ ጋር እግር ኳስ መጫወት በልጅነቱ የሚያዝናኑት ልምዶቹ ነበሩ።
አሊ ቢራ የሚለውን ስያሜ ያገኝበት አጋጣሚ
አሊ በ1950ዎቹ መጀመሪያ ላይ፤ የኦሮሞ ቋንቋ እና ባህል ለመኩራት እና ለመጠበቅ ባለው ፍላጎት የሚታወቀውን የኡርጂ በከልቻ ባንድ (በኋላ ስሙ አፍረን ቀሎ ተብሎ የተጠራ) እንደተቋቋመ ብዙም ሳይቆይ በ13 ዓመቱ የባንዱን ጀማሪ ቡድን ተቀላቀለ። ኢብራሂም መሀመድ አደም፣ አቡበከር መሀመድ አደም፣ አሊ አብዲ ጀማ፣ ኤልያስ ኢብራሂም ቡሮ፣ ኢብራሂም ዩሱፍ፣ አብዶሽ አብራ፣ አብዱሰላም ዩሱፍ፣ ኤልያስ ዩሱፍ አደም እና ካሊድ በከር ኡስማን ሌሎች የባንዱ አባላት ነበሩ። ከዚያም አሊ “ቢራ ዳ ባሪ ኤ” የተሰኘ ዘፈን ለመጫወት እድል ያገኘበት የመጀመሪያው የአፍረን ቀሎ ህዝባዊ ትርኢት በ1956 በኢድ ምሽት አካሄዱ። ከዚያም አሊ ዝነኛ ሆነና ከተጫወተው ዘፈን ርዕስ የተወሰደ አሊ ቢራ የሚል ቅፅል ስም ከሁለቱ የባንዱ አሊዎች ለመለየት ተሰጠው፡፡ ወዲያው ወደ ነባር(ከፍተኛ) የአፍረን ቀሎ ባንድ አባልነት አድጎ ሙዚቃ መጫወት ጀመረ።
ከሙዚቃ ስራው እስከ ውጭ ሀገር ቆይታ
የሃይለስላሴ መንግስት ጫና፤ አንደ ሳንሱር እና በአፍራን ቃሎ አባላት ላይ ከመንግስት ባለስልጣናት የሚሰነዘር ውንጀላ አንዲሁም ከመንግስት ጸጥታ አባላት ጋር በድብቅ በመመሳጠር የባንዱ አባላት አርሰበርሳቸው አንዲጠራጠሩ አድርጓቸዋል። በዚህና በሌሎች ምክንያቶች የባንድ ቡድኑ ተለያዩ። የአፍረን ቀሎ ባንድ የወከለው የኦሮሞን የባህል፤ ህዳሴ እና ቆራጥነት ትስስር በመንገዘብ ባንዱ ቀጣይነት አንዳይኖረው ወይም አንዲበተን መንግስት ከፍተኛ ሚና መጫወቱ የሚካድ አይደለም።
ከዚያም በ1957 ዓ/ም አሊና ጓደኛው ኢስማኢል ሙመድ አደም በህገ ወጥ መንገድ ወደ ጁቡቲ ለመግባት ሲሞክሩ በፖሊስ ተይዘው አስር ቤት ገቡ፡፡ ጓደኛው ወዲያወ ሲፈታ አሊ ግን አንድ ወር በእስር አሳልፏል። ከእስር ቤት ከተለቀቀ በኋላ ወደ ጅቡቲ ከሸሹ የቀድሞ ጓደኞቹ ጋር ተገናኝቶ ለአራት ወራት ያህል ከነሱ ጋር ቆየ።
ታህሳስ 22 ቀን 1956 ዓ/ም አሊ አቡበከር ሙሳ፣ መሐመድ ዩሱፍ አንዲሁም አሊዬ አህመድ ከሚባሉ ስሦስቱ ጓደኞቹ ጋር ወደ ድሬዳዋ ተመለሱ። በጁቡቲ በነበራቹ ህዝባዊ ትርኢት ላይ ንጉሱን ተሳድባችዋል በማለት ድሬዳዋ በደረሱበት ዕለት በመንግስት የጸጥታ አካላት ተይዘው የሙሉ ቀን ምርመራ ከተደረገባቸው በኃላ ወደ ሐረር ተወስደው አራት ወር ከአስራ ስድስት ቀን በሐረር እስር ቤት አሳለፉ።
ከዚያም አሊ ሰኔ 13 ቀን 1958 ዓ/ም ወደ አዲስ አበባ ሄደ። አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ መደበኛ ባልሆኑ ቦታዎች ላይ ሙዚቃ መጫወት ቀጠለ። መስከረም 27 ቀን በዛው አመት አሊ በሲኒማ ራስ ለመስቀል በዓል በተዘጋጀ የሙዚቃ ትርኢት ላይ ተጋብዞ ነበር። የዚያ ቀን የመድረክ ስራው አፈጻጸም ምክንያት በንጉሠ ነገሥቱ ክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራ ውስጥ ወዲያውኑ ሥራ መስራት መጀመር አንደሚችል ዋስትና ተሰጠው።
አሊ በእነዚያ ቀናት በአዲስ አበባ ማናቸዉም ክለቦች የአፋን ኦሮሞ ዘፋኞች እንዳልነበሩዋቸው ከልብ አዝኖ ተናግሯል። በክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራ ውስጥ እንደ ጥላሁን ገሠሠ፣ ሙሐሙድ አህመድ፣ ብዙነሽ በቀለን የመሳሰሉ የኢትዮጵያ የቆዩና አንጋፋ ሙዚቀኞች ጋር ተጫውቷል። ከቡድኑ ጋር በመሆን በኢትዮጵያና በሱዳን በኩል ተጉዞ እንደ መሀመድ ዋርዲ ካሉ ታዋቂ ሰዎች ጋር ዘፍኗል። አዲስ አበባ በነበረበት ወቅት እንደ ሀገር ፍቅር ቲያትር እና ራስ ቴአትር ባሉ ትላልቅ ቦታዎች ላይ ትርኢት ያቀርብ ነበር።
አሊ በክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራ ከተቀጠረ ቡኃላ ቡዝም ሳይቆይ ከሜጫ-ቱላማ ማህበር ጋር ግንኙነት ፈጠረ። ሙዚቃ እና ድራማን ጨምሮ በማህበሩ የባህል እንቅስቃሴዎች ላይ ተሳትፏል። በቦታው በሚሰራው ስራዎች የድህንነት ሰዎችን ትኩረት ስቦ ነበር። የክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራ ሂወት ለአሊ ቢራ ፈታኝ አየሆነ መጣ፤ በቦታው የነበረ ሰርአትና ጥብቅ የስነ ምግባር ቁጥጥር ጭምር አታካች ነበር ለአሊ። ከሶስት አመት በኋላ ስራውን ለማቆም ወስኖ ለስራ ወደ አዋሽ ባቡር ጣቢያ ሄደ።
አሊ ወደ አዲስ አበባ ከተመለሰ በኋላ በሙዚቀኛነት እና ሙዚቃ አቀናባሪነት ስራ ቀጠለ። አሊ የአፍ መፍቻ ቋንቋው ከሆነው ከአፋን ኦሮሞ በተጨማሪ በአማርኛ፣ በአረብኛ፣ በሃረሪ እና በሶማሌ ቋንቋዎች የመዝፈን ችሎታ ነበረው።
1967 ዓ/ም “አባ ላፋ” የተሰኘውን አልበም በኦሮሞ ሙዚቃ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን ከአዱ ቢራ ባንድ ጋር ሰርትዋል። አልበሙ ከሌሎቹ መካከል የፍቅር፣ የአብዮት አንዲሁም ፍትሃዊ የመሬት ክፍፍል መልዕክቶችን የተመለከተ ዘፈኖችን ይዟል። በአልበሙ ላይ የተካተቱት የአሊ ተወዳች ነጠላ ሙዚቃዎች መካከል አባ ለፋ፤ ሲንበርባዳ ሆጉ አንዲሁም እሽሩሩ የሚሉ ተወዳጅ ሙዚቃዎች ይጠቀሳሉ።
ከዚያም ከተለያዩ ባንዶች ጋር የሰራ ሲሆን ከነዚም አይቤክስ ባንድ ይጠቀሳል። በተጨማሪም በ1971 ዓ/ም የወጣውን “አማሌሌ” የተሰኘውን ተወዳጅ አልበሙን ጨምሮ ሌሎች ውጤታማ ስራዎችን ለአድማጮች ሰርቶ አቅርብዋል። አንዲሁም አንደ ሙሉቀን መለሰ ካሉ ታላላቅ አርቲስቶች ጋር በራስ ሆቴል መስራት ጀመረ ሲሆን በ1976 ዓ/ም ወደ ውጭ አገር ከመሄዱ በፊት በራስ ሆቴል ለሰባት ዓመታት ሰርተዋል።
እ.ኤ.አ ሚያዚያ 27 ቀን 1984 ዓ.ም ከስዊድናዊት ባለቤቱ ቢርጊታ አስትሮም ጋር ወደ አሜረካ ሄደ፡፡ አሊ ብዙም ሳይቆይ እንደገና መድረክ ላይ ራሱን አገኘ፡፡ በኋላም አንደ አስቴር አወቀ፣ ሀጉስ ገብረህይወት እና ተሸመ ምትኩ ያሉ ኢትዮጵያዊ አርቲስቶች ጋር ተቀላቀለ፡፡ ቡድን መስርተውም ወደ ተለያዩ ከተሞች ተጉዘዋል፡፡ ከዚያ በኋላም በስዊድን እና በሳውዲ አረቢያ ሀገር ከባለቤቱ ቢርጊታ ጋር ኖሯል፡፡ ገንቦት 1992 ዓ.ም ወደ አሜሪካ ከተመለሰ በኋላ ከባለቤቱ ቢርጊታ ጋር የነበረውን ግንኙነት አቋረጠ፡፡ ከዚያም በካናዳ የሬስቶራንት ስራ እየሰራ የሙዚቃ ስራውን ያቀርብ ነበር፡፡ በካናዳ ቆይታውም በ1995 ዓ.ም የሙዚቃ አፍሪካ ሜሪት ሽልማትን አሸንፏል፡፡
በ2005 ዓ.ም ከሃያ አመታት የስደት ጉዞ በኋላ ወደ ሀገር ቤት የተመለሰበት ተሪካዊ ሁኔታ ቀላል አልነበረም፡፡ በታዋቂው የኦሮምኛ የግጥም ደራሲ መሀመድ አህመድ (ቆፔ) ጥረት ወደ ሀገር ቤት ተመለሰ፡፡ አሊ በኢትዮጵያ መንግስትም ከፍተኛ አቀባበል ተደረገለት፡፡ በበርካቶች በጉጉት ሲጠበቅ በነበረው ‹ጋልማ አባ ገዳ ምርቃት› ላይም በአዳማ ከተማ አሊ እራሱ በመድረክ ላይ ተጫውቷል፡፡ በመድረክ ጨዋታው ወቅት ታይቶ የማይታወቅ በለቅሶ፣ በእንባ፣ በጩኸት፣ በዳንስ፣ በመሳም እና በመተቃቀፍ የተገለፀው የተሳተፊዎች ስሜት ለብዙ አመታት የታፈኑ ስሜቶችን ያመለክቱ ነበር፡፡ አሊ ከአዲስ አባባ 45 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው ቢሾፍቱ ከተማ በወቅቱ የኦሮሚያ ክልል መንግስት በስጦታ በሰጠው ቤት እስከ እለተ ሞቱ ድረስ ኖሯል፡፡ በህይዎት ዘመኑም አምስት የሙዚቃ አልበሞችን አበርክቷል፡፡
የግል ህይወቱ
አሊ በህይወት ዘመኑ ሶስት ሴቶች አግብቷል፡፡ በ1982 ዓ.ም ቢርጊታ አስትሮም የተባለች ስዊድናዊት አግብቶ እስከ 1992 ዓ.ም ድረስ በተለያዩ ሀገራት አብረው እየተዘዋወሩ ኖረዋል፡፡ ከእሷ ጋር ከተለያየ በኋላ ኑጁማ መሀመድ የምትባል ሴት በ1993 ዓ.ም አገባ፡፡ ጋብቻው ብዙም ሳይዘልቅ በ1995 ተለያዩ፡፡ አሊ እና ኑጁማ ከተለያዩ ከጥቂት ወራት በኋላ ለሊ ማርከስን በጓደኛዋ በኩል አገኛት፡፡ ከተወሰነ ጊዜ የፍቅር ግንኙነት በኋላ አብረው መኖር ጀመሩ፡፡ ሀምሌ 29፣ 2007 ዓ፣ም በሸርዓ ህግ ኒካህ በማሰር ትዳራቸውን ግጋዊ አደረጉ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰ በኋላም አሊ ህይወቱን ሙሉ ከሊሊ ነማርከስ ጋር ኖረ፡፡
እውቅና እና ሽልማቶች
አሊ ለኦሮሞ ሙዚቃ፣ ቋንቋ እና ባህል እድገት ላበረከቱት የላቀ አስተዋፅኦ በርካታ ሽልማቶችን (በአብዛኛው የህይወት ዘመን ስኬት ሽልማቶች) እና ከተለያዩ ድርጅቶች በርካታ የምስጋና ምስክር ወረቀቶችን አግኝቷል፡፡ አሊ በ2010 ዓ.ም ከጅማ ዩኒቨርሲቲ የተሸለመውን የክብር ዶክተሬት ዲግሪን ጨምሮ በ30 ዓመታት ውስጥ ከ 50 ባላይ ሽላማቶችን አግኝቷል፡፡ በ2011 ዓ.ም በአዳማ ከተማ ከዋናው ሀረር አውራ ጎዳና ወደ አባ ገዳ አዳራሽ የሚወስደው መንገድም በስሙ ተሰይሞለታል፡፡
ከ60 አመታት የተሳካ የሙዚቃ ህይወቱ በኋላ ኢሊ እሁድ ህዳር 27፣ 2015 ዓ.ም አመሻሹ ላይ በፀና ታሞ ክትትል ሲያደረግበት በነበረው አዳማ አጠቃላይ ሆስፒታል አረፈ፡፡