ትንታኔ: ቀናት ካስቆጠረ አለመረጋጋት ፣ የንብረት ውድመት እና መፈናቀል በኋላ በጂንካ እና አከባቢዋ አንፃራዊ ሰላም ሰፍኗል፣ ከ130 ሰዎች በላይ ቁጥጥር ስር ውለዋል

በእቴነሽ አበራ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 4 ፣ 2014፣ ከሰሞኑ በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን አሪ ወረዳ በተፈጠረው ሁከትና ግጭት የተነሳ የአንድ ሰው ህይወት ያለፈ ሲሆን ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች መፈናቀል እንዲሁም የንግድ ቤቶችና መኖሪያ ቤቶች ላይ ዘረፋ እና ቃጠሎ ደርሷል። ለቀናት በጂንካ ከተማ ከዘለቀው አለመረጋጋት በኋላ የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አለማየሁ ማሞ ከ133 በላይ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ለመገናኛ ብዙሀን ተናግረዋል ። ከነዚህም ውስጥ አራቱ የፖሊስ አባላት፣ የአካባቢው አስተዳደር አካላት እንዲሁም እራሳቸውን የማህበረሰብ ተወካይ ብለው የሚጠሩ የማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎችንም እንደሚገኙበት ገልጸዋል። 

ፖሊስ በተለይ ባለፈው ቅዳሜና እሁድ በተፈጠረው አለመረጋጋት የአንድ ሰው ህይወት አልፏል ቢልም ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የአካባቢው ነዋሪ ለአዲስ ስታንዳርድ በስልክ እንደተናገሩት የተገደሉት ሰዎች ቁጥር አምስት ይደርሳል።

በደቡብ ኦሞ ዞን የሚገኘው የአሪ ማህበረሰብ የአሪ ወረዳ ወደ ዞን ደረጃ እንዲያድግ እና መንገዶችን፣ ሆስፒታሎችንና ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ ለአካባቢው ማህበረሰብ የመሰረተ ልማት ግንባታ እንዲጨምር ሲጠይቅ ቆይቷል።

የደቡብ ኦሞ ዞን ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ መላኩ ለማ ለአዲስ ስታንዳርድ በስልክ እንደተናገሩት የግጭቱ መነሻ ከአሪ ማህበረሰብ የዞን መዋቅር ጥያቄ ጋር የተያያዘ ነው። “በደቡብ ኦሞ ዞን የሚገኙ አራት የአሪ ወረዳዎች ከሦስት ወራት በፊት በየወረዳቸው ምክር ቤት ይግባኝ በማግኘታቸው የዞን መዋቅር ጥያቄ አቅርበዋል” ብለዋል አቶ መላኩ። 

ሰሞኑን በተካሄደው የዞኑ ምክር ቤት ጉባ አጀንዳው በደቡብ ኦሞ ዞን ምክር ቤት ፀድቆ ወደሚቀጥለው ደረጃ ይሸጋገራል ተብሎ ይጠበቅ ነበረ ነገር ግን እየተካሄደ ባለው አዲስ ክልላዊ መዋቅር ማስተካከያ ምክንያት አጀንዳው ሳይቀርብ መቅረቱ ለግጭቱ መንስኤ ሆኗል” ብለዋል አቶ መላኩ። 

አዲስ ስታንዳርድን ያነጋገረው የማህበረሰቡ አባል እንደገለጸው፣ የአሪ ማህበረሰብ ጥያቄ የዞን መዋቅር ብቻ ሳይሆን የህዝብ ብዛቱን የሚመጥን በቂ የፖለቲካ ውክልና እንዲሰጠው የሚል ጥያቄን ያካተተ ነው። የአቶ ማህበረሰብ በደቡብ ኦሞ ዞን ከሚገኙ 16 የተለያዩ ብሄረሰቦች መካከል በቁጥር ትልቁ ነው።  

እንደ አቶ መላኩ ገለጻ፣ ሁለት አዳዲስ የአስተዳደር አካላት ማለትም የሲዳማ እና የደቡብ ምዕራብ ክልሎች መዋቅሮችን በመዘርጋት ላይ ሰለሆነ አዲስ የዞን እና የወረዳ ጥያቄያዎች ምላሽ አልተሰጠውም።

የዞን ምስረታ ጥያቄዎች በክልሉ ምክር ቤት ምላሽ የሚሰጥ ሲሆን ከዞኑ ምክር ቤት የሚጠበቀው የወረዳውን ይግባኝ ማፅደቅ ብቻ ነበር ያሉት አቶ መላኩ  “የዞኑ ምክር ቤት አጀንዳውን ሊመክርነት ባለመቻሉ ነው ግጭቱ የተጀመረው”ብለዋል። ኃላፊው አክለውም የዞኑ አስተዳደር የአሪ ማህበረሰብ የዞን መዋቅር ጥያቄ ባለመመለሱ ይቅርታ መጠየቁን አስታውቆ ጥያቄውን ለሚመለከተው አካል እንደሚልክ ቃል ገብቷል ሲሉ ገልጸዋል። 

የዞኑ አስተዳደር በይፋ ይቅርታ ከጠየቀ ከቀናት በኋላ በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች እና የዞን መዋቅር ጥያቄውን ከሚያስተባብሩ “ሸከን” የተሰኙ የአካባቢው ወጣቶች የጀመረው ግብግብ ወደ ተኩስ ልውውጥ ተሸጋግሯል። የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊው ቅዳሜ ማታ  ጂንካን ጨምሮ በጋዘር፣ ቶልካ እና ሺሸር ከተሞች ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ መደረጉን፣ መኖሪያ ቤቶች እና ሱቆች መቃጠላቸውንና መዘረፋቸውን ገልጸዋል።

የ”ሸከን” አባላት በጂንካ ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረጋቸውን ተከትሎ በአሪ ማህበረሰብ እና በሌሎች ነዋሪዎች መካከል ያለው ውጥረት ተባብሶ እንደነበር የከተማው ነዋሪ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጿል። ሰልፉን የሚቃወመው ጎራ የአንድን የአሪ ማህበረሰብ አባል የሆነ ወጣት ቤት መክበቡን እና ይህን ተከትሎ የአካባቢው የጸጥታ ሃይሎች ማስፈራሪያውን መከላከል ባለመቻላቸው ወጣቶቹ መቆጣታቸውን ነዋሪው አክሎ ተናግሯል።  በኋላም ከፍተኛ ብጥብጥ ተከስቶ ቤቶች ጭምር ተቃጥለዋል፣  የአሪ ማህበረሰብ አባላት ላይ የጅምላ እስራት እስከ ትናንት ምሽት ድረስ ቀጥሏልም ነው ያለው ነዋሪዉ። 

የደቡብ ኦሞ የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ መላኩ ”ከትናንት ጠዋት ጀምሮ መከላከያ ሰራዊት አካባቢውን በመቆጣጠሩ አንጻራዊ ሰላም ሰፍኗል”ብለዋል። ከአካባቢው የተፈናቅለሉም ወደ ቀያቸው እየተመለሱ ነው። ከዞኑ ኮሙዩኒኬሽን ማህበራዊ ትስስር ገጽ ባገኘነው መረጃ የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት በአካባቢው ሞተር ብስክሌቶች እንዳይንቀሳቀሱ ማገዱን ለማወቅ ችለናል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.