ዜና: ኦፌኮ መንግሥት እና የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት እንዲደራደሩ፣ የአማራ ታጣቂ ሀይሎች ኦሮሚያ ላይ የሚያካሂዱት ወረራ እንዲቆም ጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 3 ፣ 2014፣:- በኦፌኮ የተለያዩ ተዋጊ ኃይሎች ወደ ፖለቲካዊ መድረክ በመመለስ ለኦሮሚያና ለሰፊው ሕዝብ ሰላም እንዲያወርዱ ቢጠይቅም ጦርነቱ በከፋ መልኩ ቀጥሎ በመንግስት አዲስ ዘመቻ ተከፍቷል ሲል ገልጿል፡፡

ፓርቲው ይህን ያለው ዛሬ ባወጣው መግለጫ ሲሆን መንግስት ሰሞኑን በአዲስ መልኩ ያወጀው ዘመቻ በጥቂቱ ፈንጥቆ የነበረውን የሰላም ጭላንጭል መልሶ የሚያደበዝዝ፤ ኦሮሚያና አገሪቱን ለተጨማሪ አደጋ የሚያጋልጥ እንጂ ዘላቂ መፍትሄ እንደማያስገኝ ነው ፓረቲው የገለጸው ፡፡

መግለጫው በአጎራባች የኦሮሚያና የአማራ ክልሎች መካከል እየተባባሰ ስለመጣው የሰላምና ፀጥታ ችግርም ያነሳ ሲሆን  የጦር መሳሪያ የታጠቁ ኃይሎች በተለያዩ ስፍራዎች በኩል የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትን ወሰን በኃይል በመጣስ ጦርነት አውጀው የመሬት ወረራና የግዛት ማስፋፋት ተግባር ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ ብሏላ፡፡ እነዚህ ኃይሎች ሰላማዊ ሰዎችንበመግደል፤አርሶ አደሮችን ከመሬታቸው በማፈናቀል ክልሉን ወደማያባራ የግጭት ቀጠና እየለወጡት እንደሚገኙ ማረጋገጡን ገልጿል፡፡

የአማራ ክልላዊ መንግስት  ከሰሜን ሸዋ ዞን ቅንቢቢት ወረዳ 280 ሄክታር በላይ መሬት እና ምስራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ ጥሶ በመግባት የከረዩና ኢቱ ኦሮሞ  መሬትን በመውሰድ በክልሉ ውስጥ ያለ የሚያስመስሉ ታፔላዎች በመትከል ሰፊ የመሬት ወረራና የግዛት ማስፋፋት እያካሔደ መሆኑን ገልጿል፡፡ይህ በአስቸኳይ መቆም አለበት እንዳለበት አሳስቧል፡፡

በመጨረሻም ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው እየተሰተዋለ ባለው ኑሮ ውድነት ላይ የመከረ ሲሆን የዚህ የኑሮ ውድነት ዋነኛው መንስዔ አገሪቱ በሁሉም አቅጣጫዎች የገባችበት የርስ በርስ ጦርነት መሆኑንም ገልጧል፡፡ ኦፌኮ ለኑሮ ውድነቱም መፍትሄ የለውን ሃሳብ ያስቀመጠ ሰሲሆን ለዚህም መፍትሄው ሀገሪቱን በሁሉም አቅጣጫ እያመሰ ያለውን የርስ በርስ ጦርነት ወደሚያስቆም ውይይትና ድርድር ፊትን ማዞር ብቻ ነው ሲል ገልጿል፡፡

ሙሉ መግለጫው እንደሚከተለው ቀርቧል\

1) ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በቅድሚያ የተወያየው በኢትዮጲያ መንግስትና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት መካከል እየተካሔደ ያለውን ጦርነት በማስመልከት ነው፡፡ ኦፌኮ በተለያዩ ግዜያት ይህ ጦርነት በድርድር እንዲቆም ተደርጎ ተዋጊ ኃይሎች ወደ ፖለቲካዊ መድረክ በመመለስ ለኦሮሚያና ለሰፊው ሕዝባችን ሰላም እንዲያወርዱ ሲያሳስብ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ በቅርቡ በተካሔደው 2ኛ ጠቅላላ ጉባዔ ላይም የሰላም ጥሪውን በሙሉ ድምጽ በመደገፍ መልዕክት ማስተላለፉም አይዘነጋም፡፡ ይሁን እንጂ ጦርነቱ በከፋ መልኩ ቀጥሎ በመንግስት አዲስ ዘመቻ ተከፍቷል፡፡ ይህ መንግስት ሰሞኑን በአዲስ መልኩ ያወጀው ዘመቻ በጥቂቱ ፈንጥቆ የነበረውን የሰላም ጭላንጭል መልሶ የሚያደበዝዝ፤ኦሮሚያና አገሪቱን ለተጨማሪ አደጋ የሚያጋልጥ እንጂ ዘላቂ መፍትሄ እንደማያስገኝ ደጋግመን ማሳሰብ እንፈልጋለን፡፡ ኦፌኮ ከዚህ ቀደም እንደገለጸው በሁለቱ አካላት መካከል ያለው ግጭት ፖለቲካዊ መንስዔ ያለው ሲሆን መፍትሄውም ፖለቲካዊ መሆን አለበት ብሎ ያምናል፡፡ ስለዚህ መንግስት ‘ሸኔን ማጥፋት’ ከሚለው ውጤት አልባ የዘመቻ አዙሪት ወጥቶ በሰሜኑ ያገራችን ክፍል እንደጀመረው ሁሉ በኦሮሚያ ክልል ያለውን አለመግባባትም ተመሳሳይ በሆነ ሰላማዊ አካሄድ እንዲፈታ በድጋሜ ጥሪ እናደርጋለን፡፡ በሁለቱም ወገን ያሉ ተዋጊዎችም ለሰላማዊው ህዝብ ህይወት እና ንብረቱ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እንጠይቃለን፡፡

2) ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በሁለተኛነት የተወያየው በአጎራባች የኦሮሚያና የአማራ ክልሎች መካከል እየተባባሰ ስለመጣው የሰላምና ፀጥታ ችግር ነው፡፡ ከሰሞኑ ይፋ እየተደረጉ ካሉ ዘገባዎች መረዳት እንደሚቻለው ከአማራ ክልላዊ መንግስት በመነሳት የጦር መሳሪያ የታጠቁ ኃይሎች በተለያዩ ስፍራዎች በኩል የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትን የታወቀ ወሰን በኃይል በመጣስ ጦርነት አውጀው የመሬት ወረራና የግዛት ማስፋፋት ተግባር ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ኃይሎች ሰላማዊ ሰዎችን በመግደል፤አርሷደሮችን ከመሬታቸው በማፈናቀል ክልሉን ወደማያባራ የግጭት ቀጠና እየለወጡት እንደሚገኙ ታውቋል፡፡ በተለይም ይህ የጦር ዘመቻና የመሬት ወረራ በምስራቅ ወለጋ፤ሆሮ ጉድሩ ወለጋ፤ሰሜን ሸዋ፤ ምዕራብ ሸዋና በምስራቅ ሸዋ ዞኖች፤ በተቀናጀ አኳኋን እየተካሔደ እንደሚገኝ ከአባሎቻችን እና ከአካባቢው ማህበረሰብ ለመረዳት ችለናል፡፡ ታጥቀው ወረራ እያካሔዱ ባሉ የአማራ ክልል ኃይሎች በሚዲያ የሚሰጡት መግለጫም ይህንኑ ያረጋግጣል፡፡ ይህን ወረራ የሚያካሂዱት ከክልሉ መንግስት እውቅና ውጪ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ “ጽንፈኛ” ኃይሎች ናቸው ቢባልም ይህ እውነት እንዳልሆነ የሚያመላክቱ ማስረጃዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ያክል ከሰሜን ሸዋ ዞን ቅንቢቢት ወረዳ 280 ሄክታር በላይ መሬት ላይ የኦሮሚያ አርሷደሮችን በመንቀል መሬቱን የወሰደው የአማራ ክልል ልዩ ፖሊስ እንደሆነ የመንግስት ሚዲያ ሳይቀር አጋልጧል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ምስራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ የሁለቱን ክልሎች ድንበር ብዙ ኪሎሜትሮችን ጥሶ በመግባት የከረዩና ኢቱ ኦሮሞ ለዘመናት የኖሩበትን መሬት ወሮ በመያዝ፤ ስፍራው በአማራ ክልል ውስጥ ያለ የሚያስመስሉ ታፔላዎች በመትከል ሰፊ የመሬት ወረራና የግዛት ማስፋፋት እያካሔደ ያሉት የአማራ ክልላዊ መንግስት አካላት እንደሆኑ ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ እንዲህ ያለው አሰራር ህገመንግስቱን ከመፃረር አልፎ የሁለቱ ክልሎች ወንድማማች ህዝቦች ወደለየለት ጦርነት እንዲገቡ በር የሚከፍት መሆኑን ኦፌኮ አበክሮ ያስጠነቅቃል፡፡ እንዲሁም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ሥር ያለው የኦሮሞ ልዩ ዞን ህዝባችን ከማንኛውም ስርዓት በከፋ ሁኔታ እየተገደለ፤እየታሰረ፤እየተዘረፈና በክልሉ መኖር እስከማይችልበት ደረጃ ላይ እየደረሰ ስለመሆኑ የሚያመለክቱ መረጃዎች አሉ፡፡ ይህ በአስቸኳይ መቆም አለበት ብለን እናምናለን፡፡የአማራና ኦሮሞ ህዝብ ሰፊ ድንበር የሚዋሰን ከመሆን አልፎ በሚሊዮኖች ተሰባጥሮ ያለ ሲሆን ቀደምት መንግስታት ሲያደርሱ በነበረው በደል ምክንያት ቁርሾዎች ተፈጥረው እስካሁን ያልሻሩ ቁስሎች እንዳሉ የሚካድ አይደለም፡፡ ይህ በጥላቻ ፕሮፓጋንዳ እየታገዘ የሚካሔደው የመሬት ወረራና የግዛት ማስፋፋት ዘመቻ ቀድሞውንም ባልሻረ ቁስል ላይ ጨው በመነስነስ የሁለቱን ህዝቦች ግንኙነት ወደከፋ የመጠፋፋት ጦርነት ሊገፋ እንደሚችል ሁለቱም ወገኖች ሊገነዘቡ ይገባል፡፡ በሁለቱ ክልሎችና እነዚህ ትልልቅ ህዝቦች መካከል የሚደረገው ጦርነት አገሪቱንም ለብተና፤ የአፍሪካን ቀንድ ደግሞ ለከፋ አለመረጋጋት የሚያጋልጥ መሆኑ ታውቆ ይህ ድርጊት በአስቸኳይ እንዲቆም ኦፌኮ ያሳስባል፡፡

3. ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ቀጥሎ የተወያየው ከእለት ወደእለት እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነት ላይ ነበር፡፡ የምግብ እህል፤ የቤት ኪራይ፤ ነዳጅ፤ሸቀጣሸቀጥ፤ማዳበሪያ፤የዘር እህል ወዘተ ዋጋ በማይታመን ሁኔታ እጥፍ ድርብ እየጨመረ በመምጣቱ አብዛኛው ህዝብ የእለት ጉርሱን፤ የዓመት ልብሱን፤ አንገት ማስገቢያ ጎጆ እንዳያገኝ እያደረገው ይገኛል፡፡ የዚህ የኑሮ ውድነት ዋነኛው መንስዔ አገሪቱ በሁሉም አቅጣጫዎች የገባችበት የርስ በርስ ጦርነት ነው፡፡ ይህ የርስ በርስ ጦርነት አገሪቱን ሰላምና መረጋጋት በመንሳት የውስጥና የውጪ ንግድ እንዲቀዛቀዝ፣ የአርሷደሩና የፋብሪካዎች ምርታማነት እንዲቀንስ፣ የውጪ ኢንቨስትመንት እንዲሳሳ፣ መንግስት ለልማት ማዋል የነበረበትን በጀት ወደ ጦርነት ዞሮ እንዲባክን በማዕቀቡ ምክንያት በእርዳታና በብድር ወደአገር ይገባ የነበረ ገንዘብ እንዲቋረጥ ወይም እንዲቀንስ በማድረጉ አገሪቱን ለኢኮኖሚ ውድቀት ዳርጓታል፡፡ ያለው ጥሬ ሐቅ ይህ ሆኖ ሳለ መንግስት ግን ከኃላፊነት በመሸሽ ጣቱን ወደ ንግዱ ማህበረሰብ እየቀሰረ ይገኛል፡፡ ይህ አካሔድ በችግር የተጎሳቆለው ህዝብ ትኩረቱን ከመንግስት ለጊዜው ወደሌላ ያዞረው እንደሆነ እንጂ በፍጥነት እየወደቀ ያለውን የአገሪቱን ኢኮኖሚ እንዲያገግም ለማድረግና፤ ሰማይ የነካውን የኑሮ ውድነት ለመቀነስ የሚፈይደው ነገር የለም፡፡ መፍትሄው ሀገሪቱን በሁሉም አቅጣጫ እያመሰ ያለውን የርስ በርስ ጦርነት ወደሚያስቆም ውይይትና ድርድር ፊትን ማዞር ብቻ ነው ብሎ ኦፌኮ ያምናል፡፡

በአጠቃላይ አገሪቱን ቀስፎ የያዘውን የፀጥታ እጦትና የኑሮ ውድነት ችግር ለመፍታት ያለው አማራጭ በተለያዩ ክልሎች እየተካሔዱ የሚገኙ የርስ በርስ ጦርነቶች ማስቆም፤የፖለቲካ ልዩነትን በጦርነት ሳይሆን በምክክር መፍታት መሆኑን ኦፌኮ በድጋሜ ያሳስባል፡፡ ስለዚህ መንግስትም ሆነ ማንኛውም ታጥቆ የሚንቀሳቀስ ኃይል ወደምክክር መድረክ በመመለስ፤ የኢኮኖሚ ውድቀት፤ በህዝብ ላይ የተጫነውን መከራ፤ እንዲሁም አገሪቱን ከብተና እንዲያድኑ ጥሪ እናስተላልፋለን፡፡ አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.