በቤካ ኣቶማ @bek_boru
አዲስ አበባ፣ ህዳር 15/ 2015 ዓ.ም፡- በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስት እና በትግራይ ባለስልጣናት መሃል የተካሄደው የሰላም ስምምነት ይፋ ከሆነ ማግስት ጀምሮ የተለያዩ ሚዲያዎች በተለያዩ ወገኖች የሚሰጡ አስተያየቶችን እያስተናገዱ ይገኛሉ።
የሰላም ስምምነቱ የትግራይ ተወላጆችን ጨምሮ ሁሉም ኢትዮጵያውያን እንደዚሁም የአለም ማህበረሰብን ትኩረት የሳበ ነበር። ስምምነቱ መፈረሙ ይፋ ከሆነ ጀምሮ ባለስልጣናት፣ ተራ ሰዎች፣ ምሁራን እና የፖለቲካ ፓርቲዎች አስተያየታቸውን በተለያየ መንገድ እየገለፁ ይገኛሉ።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ሃሳባቸውን ካስተላለፉ ከፍተኛ ባለስልጣናት አንዱ ናቸው። “ስምምነቱ በሀገሪቱ ያለውን ደም አፋሳሽ ጦርነት ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ የሚቋጭ በመሆኑ ተስፋ ሰጪ ጅምር ነው” ብለዋል። ጸሃፊው አያይዘውም አለም አቀፉ ማህበረሰብ ሁለቱ ወገኖች የወሰዱትን ወሳኝ እርምጃ እንዲደግፍ ጥሪ አቅርበዋል።
የሰላም ስምምነቱ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች በህይወት ለመቆየት የሚያግዝ ነው። የሕክምና አገልግሎትን ጨምሮ አስፈላጊው ሰብዓዊ እርዳታ እጦት እና የመገናኛ እና የባንክ አገልግሎትን የመሳሰሉ መሠረታዊ አገልግሎቶች በመቋረጡ ምክንያት በችግር ላይ ላሉ ህዝቦች በፍጥነት ለመድረስና ችግሩን ለመቅረፍ ከማስቻሉም በላይ ለሁለት ዓመታት ያህል ተለያይተው ለነበሩ ቤተሰቦች የተስፋ ብርሃን ፈጥሯል።
የ40 ዓመቷ መድሀኒት ሹሚዬ የሶስት ልጆች እናት ሲትሆን ነዋሪነቷ በአዲስ አበባ ከተማ ነው። ጦርነቱ ከተነሳበት ጊዜ ጀምሮ ዘመዶቿ የት እንዳሉም ሆነ በህይወት ይኑሩ አይኑሩ አታውቅም ነበር። ሆኖም ግን ተስፋዋ አላተሟጠጠም ነበር። አንድ ቀን ላገኛቸው እችላለሁ በሚል መልካም እሳቤ ራሷን ታፅናና ነበር።
የሰላም ስምምነቱ እንደ እሷ ላሉ የትግራይ ተወላጆች የቤተሰቦቻቸውን ህልውና ለማወቅ፣ እነሱን ለመገናኘት እና በአጠቃላይ በሰሜናዊው ክልል ያለውን አስከፊ ሁኔታ ለማሻሻል እንደ ወርቃማ እድል የሚታይ ነዉ ትላለች።
ጦርነቱ የትግራይ ክልልን ሙሉ በሚባል ደረጃ እና የአፋር እና የአማራ ክልሎችን በከፊል አውድሟል። በጦርነቱ ምክንየትም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ለህይወተ ህልፈት ተዳርገዋል። ሚሊዮኖችም ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። በመሆኑም አሁን የሚስተዋለው የብዙ ሰዎች ስሜት የሰላም ስምምነቱ አገሪቱን ቀድሞ ሁኔታዋ ለመመለስ የሚያስችል ድልድይ እንዲሆን ነው።
ይሁን እንጂ በርካቶች ከሰላሙ ዘላቂነት ጋር ተያይዞ ጥያቄ እያቀረቡ ነው። የሰላም ስምምነቱ ይጸናል ወይስ ሌላ መሰናክል ያጋጥመዋል? የሚል ስጋት ያላቸው ዜጎች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት እና የትግራይ ባለስልጣኖች በፕሪቶሪያ በተደነገገው ስምምነት መሰረት ቀጣይ ተግባራትን ስምምነቱን አክብረው ለመስራት ቁርጠኝነት እንዳላቸዉ እየገለፁ ነው።
ከሰላም ስምምነቱ ዘላቂነት ጋር ተያይዞ ለሚነሱ ጥያቄዎች በዘርፉ የተሰማሩ ሙሁራን የሚሉት አላቸው። የቻቨኒንግ ስኮላሩ የፖለቲካ እና የደህንነት ጉዳዮች ተንታኝ አቶ በረከት ድሪባ ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር በነበራቸው ቆይታ “ጦርነቱ ቀላል የማይባል ኪሳራ አድርሷል፡፡ በሰው ህይወትም ሆነ በቁሳቁስ ውድመት ምክንያ በአገሪቱ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጫና ፈጥሯል፡፡ በተጨማሪም በአለም አቀፍ ማህበረሰቡ በተለይም የአሜሪካ ግፊት ስምምነት የተፈራርሙት ሁለቱ ወገኖች ለስምምነቱ ተገዥ እንዲሆኑ ሊያደርግ ይችላል” ብለዋል።
በተለይ ደግሞ በመንግስት ቁጥጥር ስር ባሉ እና በህወሃት ተባባሪ ሚዲያዎች ላይ የቋንቋዎች እና የቃላት አገላለጾች ከወዲሁ መሻሻል መጀመር ስምምነቱ ዘላቂነት እንደሚኖረው መገመት ይቻላል” ሲሉ ተናግረዋል።
ነዋሪነታቸውን በአሜሪካ አገር ያደረጉት የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ ተመራማሪ ዶክተር ዮሃንስ ወልደማርያም በበኩላቸዉ የሰላም ስምምነቱ ዘላቂነት ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው ይገልፃሉ። “ምናልባት ይህ ስምምነት ለአጭር ግዜ ሰላም ሊያመጣ ይችላል” የሚል እምነት አላቸው።
በተለይ የአሜሪካ ግፊት ሁለቱ ወገኖች በስምምነቱ እንዲፀኑ ሊያደርግ የሚችል ትልቅ ምክንያት መሆኑን የሚገልፁት ዶክተር ዮሐንስ “የሰላም ስምምነቱ የተደረገው በአሜሪካውያን ከፍተኛ ጫና እና የተስማሚዎችን እጅ በመጠምዘዝ በመሆኑ ለጊዜዉም ቢሆን ሰላም ሊሰፍን ይችላል” ይላሉ።
አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያለትን አጋርነት ወደ ቀድሞ ሁኔታው ለመመለስ በኢትዮጵያ መንግስት እና በትግራይ አመራሮች መካከል በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተፈረመው የጦርነት ማቆም ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ መሆን እንዳለበት አስታውቃለች። ይህም አጎዋ ወደነበረበት መመለስ እና እንደ አይኤምኤፍ፣ የዓለም ባንክ ወዘተ ለሚገኝ የብድር ድጋፍን ይጨምራል።
ጦርነቱ ያስከተለው ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ እና በትግራይ ያለው የሰብአዊ ቀውስ ደረጃ ተዋዋይ ወገኖች የሰላም ስምምነቱን እንዲያከብሩ የሚያደርጉ አስገዳጅ ጉዳዮች መሆናቸውንም ዶክተር ዮሐንስ ገልጸዋል።
“በትግራይ ላይ የተደረገው እገዳ በረሃብና በመድኃኒት እጦት ከሚሞቱት ሰዎች ቁጥር አንፃር ርኅራኄ የለሽ ነበር” ያሉት ዶክተር ዮሃንስ “የኢኮኖሚያዊ ድቀት እያስከተለ የመጣው ጦርነት በጣም ውድ ጦርነት ነው። እነዚያ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ከፍተኛ ዋጋ ያስከፍላሉ” ይላሉ። እነዚህ እና ሌሎችም ምክንያቶች የሰላም ስምምነቱ ሊቆም እንደሚችል የጠቁማሉ ባይ ናቸዉ።
ይሁን እንጂ ስምምነቱ ዘላቂ ሰላም ሊያመጣ ይችላልን? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ከሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች ጦርነት የማቆም ስምምነት እና ስምምነቱን የመፈፀም ቁርጠኝነት በተጨማሪ በርካታ ተያያዥ ጉዳዮችን ማየት ወሳኝ ይሆናል ይላሉ ዶክተር ዮሐንስ፡፡
አብዛኛውን ጊዜ የሰላም ስምምነቶች የውድቀት መንስኤ አፈጻጸም ላይ የሚያጋጥም ችግር እንደሆነ የገለፁት ዶክተሩ ስምምነቱ ግልጽ እና ሁሉን አቀፍ ብቻ ሳይሆን ተዋዋይ ወገኖች ስለ ውሎች እና ግዴታዎች ምንነት ተመሳሳይ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግ በጣም አስፈላጊ መሆኑን አስምረውበታል፡፡ ሁለቱ ወገኖች በዚህ ስምምነት ውሎች ላይ እኩል ግልጽ ስለመሆናቸው ጥርጣሬ እንዳለም ዶክተሩ ይናገራሉ፡፡
“እኔ እንደማስበው ከትግራይ አንፃር በዚህ ስምምነት በሕገ መንግሥታዊ ማዕቀፍ ከሚለው አንቀጽ አንፃር አንድ ነገር አግኝተዋል። ምክንያቱም በሕገ መንግሥታዊ ማዕቀፍ ወልቃይትንና የራያ አካባቢዎችን ወደ ትግራይ ይገባሉ ማለት ነው›› ይላል።
ዶክተር ዮሃንስ አያይዘውም “ከአማራ ፖለቲካ ካምፕ የሚነሳውን ተቃውሞ ግምት ውስጥ በማስገባት ይሄ ምናልባትም ሌላ ሰላሙን ሊያደናቅፍ የሚችል ነገር ሊሆን ይችላል” ይላሉ።
የአማራ ክልል ፕሬዝዳንትም ቀደም ሲል በወልቃይት እና በሌሎች አወዛጋቢ አካባቢዎች ላይ የክልሉ መንግስት እንደማይደራደር ተናግሮ እንደነበር ያታወቃል።
አቶ በረከትም ከዚህ ሃሳብ ጋር ይስማማሉ። “የአማራ ብሔርተኛ የፖለቲካ ኃይሎች የሰላም ስምምነቱ ላይ ቅሬታ አላቸዉ” ይላሉ። “የአማራ የተለያዩ ወገኖች ከሰላም ስምምነት የተገለሉ እንደሆኑ ይናገራሉ። ከዚህም ባለፈ አንዳንዶቹ የሰላም ስምምነቱ በቅርቡ በተቆጣጠሩዋቸው እንደ ወልቃይት እና ራያ ባሉ አወዛጋቢ አካባቢዎች እንደሚችል ስጋት ይቆጥሩታል” ይላሉ።
በፕሪቶሪያ ስምምነት በአንቀፅ 6 ስር በትግራይ ያሉ የውጭ ታጣቂ ሃይሎች ከትግራይ እንዲወጡና በክልሉ አስተማማኝ ደህንንት እንዲፈጠር ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ የትግራይ ታጣቂ ሃይሎች ስምምነቱ በተፈረመ በ30 ቀናት ውስጥ ትጥቅ ፈተው ከህብረተሰቡ ጋር እንዲዋሃዱ እንደሚደረግ ይገልጻል።
በኬኒያ ናይሮቢ በሁለቱ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች በተደረሰው ስምምነት ትጥቅ የማስፈታት ሂደትን ጨምሮ በህገ መንግስቱ መሰረት በተሳካ ሁኔታ ስምምነቱን ለመተግበር ተስማምተዋል።
ዶክተር ዮሃንስ ከዚህ ጋር በተያያዘ እንዲህ ይላሉ። “ትጥቅ የማስፈታት ጉዳይ በተለይ ከዲያስፖራ የትግራይ ተወላጆች ዘንድ ተቃውሞ ገጥሞታል። የትግራይ ዲያስፖራ የትግራይ ሃይሎች የፋይናንስ ምንጭ ሆኖ ህዝቡን ወክሎ ሲንቀሳቀስ የነበረ ሃይል ነዉ’’
በሲያትል በዲሲ እና በሁሉም የአውሮፓ ከተሞች ያየናቸው አስገራሚ ሰልፎች ትልው ትርጉም ያላቸው ነበሩ። በትግራይ ዲያስፖራዎች ሲካሄድ የነበረው የማህበራዊ ሚዲያ ፕሮፓጋንዳ ከፍተኛ ተፅዕኖ ነበረው። አሁን የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ የትግራይን አመራሮችን በግልፅ ሲቃወሙ ተሰምተዋል፡፡ ይህ ደግሞ ለሰላሙ መተግበርና አለመተግበር በጣም ወሳኝ ነገር ነው ይላሉ ዶክተር ዮሃንስ።
ዶክተር ዮሃንስ አያይዘውም ትጥቅ የማስፈታቱ ጉዳይ በባህሪው “ውስብስብ ነው” እና በትግራይ የደህንነት አቅርቦት ላይ ቅድመ ሁኔታ መያዙ ጉዳዩን የበለጠ ውስብስብ ያደርገዋል ሲሉ ይከራከራሉ።
“የትግራይ ታጋዮች ስንት ከባድ መሳሪያ ሊያስረክቡ እንደሚችሉም የሚታወቅ ነገር የለም። መሳሪያ ለማስፈታት እንዴት ክትትል ማድረግ እንደሚቻልን በግልፅ የተቀመጠ ነገር የለም። በትግራይ ክልል ጸጥታ በአስተማማኝ መንገድ መረጋገጡን ማን ሊወስንና ሊያረጋግጥ እንሚችልም የግልፅነት ችግር አለ። ከዚሁ ጋር ተያይዞ በሁለቱ ተስማሚ ወገኖች መሃል የነበረዉን አለመተማመን ጉዳዩን ያከብደዋል” ብሏል።
አቶ በረከት በበኩላቸው የፌደራል መንግስት ትግራይ ዉስጥ ያለዉ አመኔታ በጣም ዝቅተኛ መሆኑን ጠቅሰዉ “በትግራይ ክልል ተፈጽሟል ስለተባለው ግፍ በተለያዩ ሚዲያዎች ሰፊ ሽፋን የተሰጠው በመሆኑ የአገር መከላከያ ሰራዊት የትግራይ ህዝብን መብት ለማክበርና ለማስከበር በህዝቡ ዘንድ እምነት ላይቸረው ይችላል ይህ ደግሞ ለሰላሙ መሳካት ስጋት ሊፈጥር ይችላል” ሲሉም አክለዋል።
በተጨማሪም በስምምነቱ ለትግራይ ሃይሎች ትጥቅ መፍታት የኤርትራን ጦር እና የአማራ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ ከትግራይ መውጣትን እንደ ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጡ የኤርትራዉን መሪ ኢሳያስ አፈወርቂን “በእልፍኝ ውስጥ ያለ ዝሆን” እንደሚያደርገው ዶክተር ዮሃንስ ይናገራሉ።
“ከኢሳያስ እይታ አንጻር የሰላም ስምምነት ያልተጠበቀ ስለነበር በቀጣይ ምን እንደሚሰራ አይታወቅም” ብለዋል፡፡
እንደ አቶ በረከት ገለጻ፣ አንዳንድ የትግራይ ዲያስፖራ ማህበረሰቦች እና ብሄረተኛ የትግራይ ተወላጆች ስምምነቱን “ለትግራይ ተወላጆች አዋራጅ ሽንፈት” አድርገው ይመለከቱታል። በውጤቱም “በዲያስፖራው ድጋፍ የትግራይ ሃይሎች የትጥቅ ትግሉን መቀጠልን ይመርጡ ይሆናል” ብለዋል።
አቶ በረከት አያይዘውም “በኢትዮጵያና በትግራይ ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ያሉ ህዝቦች ላይ የደረሰው ሁኔታ አሰቃቂ በመሆኑ ባለድርሻ አካላት ስምምነቱን አክብረው ከቀጠሉ እነዚህ ምክንያቶች ስምምነቱን ለማደናቀፍ በቂ አይደሉም” ብለዋል። ይሁን እንጂ ስምምነቱ ሙሉ ለሙሉ መረጋጋትና ሀገሪቱን ወደ ቀድሞ ሁኔታው ለመመለስ ተመሳሳይ የውይይት መድረኮች በመላ ኢትዮጵያ ግጭቶች ባሉባቸው አካባቢዎች ሊካሄድ ይገባል ነው ያሉት አቶ በረከት።
ዶክተር ዮሐንስ ግን በዚህ አይስማሙም። “ለአጭር ጊዜ ስምምነቱ ሰላም ሊያመጣ ይችላል፣ ነገር ግን ፍትህ ከሌለ ም ን አይነት ሰላም ይሆናል?” ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ አስ