ዜና፡ የጉራጌ ዞን ላልተወሰነ ጊዜ በተደራጀ ኮማንድ ፖስት እንዲመራ ተወሰነ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 16/ 2015 ዓ.ም፡- የጉራጌ ዞን የክልል አደረጃጀት ጥያቄን ተከትሎ ኢ-መደበኛ ቡድኖች አየፈጠሩ ያሉት ሁከትና ብጥብጥ በመደበኛ ህግ ማስከበር ስርዓት ማስቆም ባለመቻሉ ከህዳር 16 ቀን ጀምሮ በተደረጃ ኮማንድ ፖስት እንዲመራ መወሰኑን የደቡብ ክልል ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ገለፀ፡፡

የቢሮዉ ሀላፊ አቶ አለማየሁ ባውዲ ትላንት ለሚዲያ በሰጡት መግለጫ በጉራጌ ዞን የክልል አደጃጅት በሚል ሽፋን የተጀመረው እንቅስቃሴ መቀጠሉን ገልፀው ይህ ኢመደበኛ ቡድን አጥፊ ድርጊቶችን እየሰራ ነው ያለው ብለዋል።

ነሐሴ 12 ቀን 2014 ዓ.ም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባደረገው ስብሰባ የጉራጌ ዞንን ጨምሮ ሀድያ፣ ሀላባ፣ ከምባታና ጠምባሮ፣ ስልጤ እና የም ልዩ ወረዳ በክላስተር እንደ አንድ ክልል እንዲደራጁ ውሳኔ ማስተላለፉን ተከትሎ ውሳኔውን በመቃወም በወልቂጤ ከተማ በተለያዩ ሁለት ጊዜያት የስራ የማቆም አድማዎች ተደርገዉ ነበር፡፡

በለፈዉ ሳምንት በዞኑ ዋና ከተማ ወልቂጤ የክላስተር አደረጃጀቱን በመቃወም ለሶስተኛ ጊዜ የተደረገውን የስራ ማቆም አድማ ተከትሎ ከአንድ መቶ ባለይ የሚሆኑ ወጣቶች መታሰራቸውን የከተማው ነዋሪዎች መናገራቸዉን አዲስ ስታንዳርድ ዘግባ ነበር፡፡

ኃላፊው ኢመደበኛ ያሉትን ቡድን በስም ባይጠቅሱም በዞኑ ውስጥ አጠቃላይ የመንግስት መደበኛ አሰራር ቀጣይነት እንዳይኖረው፣ የመንግስትን አሰራር ጠልፎ ለራስ ፍላጎት ለመጠም እና ህዝቡንም ተገቢ ባልሆነ መንገድ እያወዛገበ መጠቀል የሚፈልግ ሃይል ነው ብለዋል፡፡

አክለውም ቡድኑ የጉራጌን ህዝብ ከክልሉ ህዝብ ጋር የሚያቃቅር፣ የሚያጋጭ እና የህዝብ ለህዝብ ትስስሩን የሚሸረሽር ተግበባራትን በመፈፀም ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ይህንን ተግባር የሚፈፅመውን ሀይል በተደራጀ መንገድ ስርዓት ለማስያዝ ይሰራል ነው የተባለው፡፡

እየተፈጠረ ያለው ችግር በመደበኛ አሰራር ለማስተዳደር አስቸጋሪ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል ያሉት አቶ አለማየሁ ከዛሬ ጀምሮ አከባበውን የተደራጀ ኮማንድ ፖስት እንደሚመራው ገልፀዋል፡

የፌድራል ፖሊስ፣ የክልሉ ልዩ ሃይል እና ሌሎችም የፀጥታ አካላትን ጨምሮ  በቅንጅትና በተደራጀ መንገድ አካባቢው ውስጥ እየተፈጠረ ያለውነን የፀጥታ ችግር ያስተዳድራል ብለዋል፡፡

ኮማንድ ፖሰቱ ከዚህ በኋላ ለጥፋት የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችና ብድኖች፣ በህግ ያልተፈቀደ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ አካላት ላይ እርምጃ ይወሰዳል ሲሉ ያስጠነቀቁት ኃላፊው አስካሁንም በተደረገ ፀጥታን የማስከበር ስራ በጥፋቱ የተሳተፉ ከ 70 ባላይ የሚሆኑ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ገልፀዋል።

አክለውም ከዚህ በፊት ቡድኑ እንዳሻው ስብሰባ ሲጠራ መቆየቱን ጠቅሰው ከዛሬ ጀምሮ በየትኛውም አካባቢ ያልተፈቀዱ ስብሰባዎች ማድረግ የተከለከለ ነው ብለዋል፡፡አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.