ትንታኔ፡ የእርሻ ወቅት እየተቃረበ ባለበት ጊዜ የማዳበሪያ ዋጋ መናሩ አርሶ አደሮችን እየተፈታተነ ይገኛል


በጌታሁን ፀጋዬ @GetahunTsegay12 እና ማህሌት ፋሲል @MahletFasil

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 28/2014 – የማዳበሪያ ዋጋ መናር ለአርሶ አደሮች ላይ ትልቅ ፈተና ሆኗል። የማዳበሪያ ዋጋ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በዚህ አመት ከ150 በመቶ በላይ መጨመሩን መረጃዎች ያመለክታሉ። አዲስ ስታንዳርድ ያነጋገረቻቸው አርሶ አደሮች እንደቀድሞው ማዳበሪያ በብድር መግዛት አለመቻላቸው ችግሩን አባብሶታል ይላሉ።

ለማ አበበ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አገረ ማርያም ወረዳ የሚኖር አርሶ አደር ነው። “እኔ የማርሰው ቆላ ላይ ነው። በአመት ከ 5 እስከ 7 ኩንታል ያክል ማዳበሪያ እጠቀማለሁ።  ለእርሻዬ ማዳበሪያ ካልተደረገበት የሚገኘው ምርት በጣም ትንሽ ነው።  ማዳበርያ መጠቀም ግዴታ ሆኗል። ከዚህ ቀደም ማዳበሪውን በብድር ወስደን ምርቱን ከሸጥን በኋል ብሩን እንከፍል ነበር አሁን እሱንም ከልክለውን ግራ ገብቶናል ” ሲለ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግሯል።  

ለማ የ 38 አመት ጎልማሳ ሲሆን የ4 ልጆች አባት ነው። በግብርና የሚተዳደረው ለማ ልጆቹ ለእርሻ ባይደርሱም ከብቶችን በመጠበቅ ያግዙታል። ትዳር ሲይዝ ከቤተሰቦቹ በስጦታ የሰጡትን መሬት በበሬ እያረሰ ይኖራል “የገበሬን ችግር የሚያውቀው ገበሬ ብቻ ነው” ይላል ለማ። 

ነገር ግን የአልቻልንም። በተመጣጣኝ ዋጋ ማዳበርያ ማግኘት ብቻ ሳይሆን አንዳንድ የከተማ ነዋሪዎች የሚያሳዩት የተሳሳተ ግንዛቤም እንዳሳዘነው ሲናገሩ “የከተማ ሰው ገበሬው ተንደላቆ የሚኖር ነው የሚመስለው።  እኛ እያረስን ተቸግረናል፣ተርበናል አርሰን በምንሸጠው እህል የሚያስፈልገንን መግዛት አቅቶን ነው ያለነው። እንዲህ ባለንበት ሁኔታ የማዳበሪያ ዋጋ ሰማይ ላይ ወጣ። ብድር የለም አሉን። መሬቱ ማዳበሪ ካላገኘ እንኳን የምንሸጠው ለእለት የምንበላውንም አይሰጥም ለኛ ፈተና ነው የሆነብን ” ሲል በምሬት አስረድቷል።   

“በገበሬነት እያጋጠሙኝ ያሉት ፈተናዎች መደበኛ ሰዎች በቀላሉ ሊረዱኝ አይችሉም። የገበሬውን ችግር የሚረዱት አርሶ አደሮች ብቻ ናቸው።”

አርሶ አደር ለማ አበበ

ወይንሸት አለሙ ሌላዋ አገረ ማሪያም ወረዳ የምትኖር አርሶ አደር ነች። ባለቤቷን በሞት ካጣች በኃላ መሬቷን አከራይታ የራሷን እና የልጆቿን ኑሮ እንደምትደጉም ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግራለች። ይህ የኑሮ ዜይቤ ግን አስተማማኝ እንዳልሆነ አስረድታለች። “የ4 አመት እና የ2 አመት ልጆች አሉኝ።  ባለቤቴ አምና ከሞተብኝ በኋላ  ልጆቼን የማስተዳድረው መሬቴን ለጎረቤት አከራይቼ ነው” ብላለች። አክላም  “ማዳበሪያና የዘር ወጭን  በጋራ እንሸፍናለን። ካከራየሁት ጎረቤቴ ጋር ምርት ከተሰበሰበ በኃላ 40% ለሱ 60% ለኔ አርገን እንካፈላለን።”ስትል ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግራለች።

እንደ ወይንሸት  ገለጻ ወጪው ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ እየከበደ በመምጣቱ እና  እንደ ቀድሞው ተመጣጣኝ ባለመሆኑ ሁኒታው አሳሳቢ እንደሆነ ተናግራለች። የማዳበሪያ ዋጋ ማሻቀቡ ህይወትን መቋቋም አዳጋች  አድርጎታልም ብላለች። “ከትንሿ የእርሻ ቦታ በምናገኘው ገንዘብ በሙሉ ማዳበሪያውን ብንገዛ እኔና ልጆቼ ምን እንበላለን?” ስትል ትጠይቃለች።

“የከተማ ሰው ገበሬው ተንደላቆ የሚኖር ነው የሚመስለው።  እኛ እያረስን ተቸግረናል፣ተርበናል አርሰን በምንሸጠው እህል የሚያስፈልገንን መግዛት አልቻልንም።”

ቢቢሲ አማርኛ በቅርቡ ባወጣው ዘገባ በባለፈው ዓመት በኩንታል 1700 ብር ይሸጥ የነበረው ማዳበሪያ ዘንድሮ ዋጋው ከእጥፍ በላይ ጨምሮ 4200 ብር መግባቱን ተናግሯል። “መሬታችን ያለ ሰብል ጾም ሊያድር ይችላል” ሲሉ ገበሬዎች ለዜና አውታሩ ተናግረዋል። የማዳበሪያ ዋጋ እየጨመረ መምጣቱንም አክለው ተናግረዋል። በማዳበርያ ዋጋ ንረት ላይ ያላቸውን ስጋት የገለጹት አርሶ አደሮቹ፣ በምርታቸው ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚያሳድርም ተናግረዋል። “የእኔ እቅድ በዚህ ዓመት ለማዳበሪያ እስከ 25 ሺህ ብር ድረስ አወጣለሁ የሚል ነበር። አሁን ግን ከእጥፍ በላይ ሆኖ ከ50 ሺህ ብር በልጧል። ታዲያ እንዴት አድርጌ እዘራለሁ?” ሲሉ  አርሶ አደር ጌቴ በአግራሞት ይጠይቃል። አርሶ አደር ጌቴ “እስካሁን አንድም ማዳበሪያ አልገዛሁም፤ ለበጋ መስኖ ቀደም ብሎ ከሰው ተበድሬ የዘራሁትንም እንዴት እንደምከፍል ጭንቅ ሆኖብኛል” ይላሉ።

ሹመቴ የተባለ ሌላ ቢቢሲ ያነጋገው አርሶ አደር የጌቴን ስጋት ይጋራል። መሬታቸውን በአዝዕርት ለመሸፈን ቢያንስ 8 ኩንታል ኤንፒኤስ እና 4 ኩንታል ዩሪያ ማዳበሪያ እንደሚያስፈልጋቸው ያስረዱት አርሶ አደሩ፣ “እኔ ደሃ አርሶ አደር ነኝ። በተባለው ዋጋ ገዝቼ ማምረት አልችልም።” ብለዋል።  ለልጄቻቸው የሚሆን ጥቂት በቆሎ ከመዝራት ውጪ ሌላ ምርት ለማምረት እንደተሳናቸው  በምሬት ተጋግረዋል። እንደ ዘገባው ከሆነ የዋጋ ንረቱ እነዚህን አርሶ አደሮች የማያተርፍ እና ማዳበሪያ የማይፈልግ ዘር ለመዝራት እንዲያስብ አስገድዷቸዋል። 

ኢትዮጵያ ከሳምንታት በፊት 12 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ መግዛቷን የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል። የሚኒስቴሩ ኢንቨስትመንትና ግብዓት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) ለቢቢሲ አማርኛ እንደተናገሩት ማዳበሪያውን ወደ ተለያዩ ክልሎች የማከፋፈል ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የማዳበሪያ ዋጋ ለምን ጨመረ?

ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ ሶፊያ የማዳበሪያ ዋጋ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ከ150 በመቶ በላይ መጨመሩን አውስተው፣ የግዢ ውል ቀደም ብሎ ባይደረግ ኖሮ ዋጋው ከዚህ በላይ ሊያሻቅብ እንደሚችል አስረድተዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው በአሁኑ ወቅት እየጨመረ ያለውን የዋጋ ጭማሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚስተዋለውን የዋጋ ንረት እንደ ዋና ምክንያትነት አንስተዋል። “እንደ አገር ቀድመን ጨረታ አውጥተን ውል ስለገባን ነው አሁንም የተሻለ የሚባል ዋጋ ያገኘነው” ይላሉ ሚኒስቴር ዲኤታዋ። 

እንደ እርሳቸው ገለጻ ፣ ትላልቅ የማዳበሪያ አምራች አገራት በኮቪድ-19 ምክንያት ምርታቸውን በመቀነሳቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ እጥረት ተከስቷል።  በተለይ ደግሞ ዩሪያ ለተባለው ማዳበሪያ ማምረቻ የሚያገለግል የተፈጥሮ ጋዝ ዋጋ መቀነሱን  እና ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚያመርቱት አገራት ከምርት ውጭ መሆናቸውንም አስረድተዋል። ቻይና እና ሩሲያ ወደ ውጭ የሚልኩት ማዳበሪያ መቀነሱን ገልጸው ይህም ለአሁኑ የዋጋ ጭማሪ አስተዋፅዖ እንዳለው ተናግረዋል። ሚኒስትር ዴኤታዋ አክለውም በግዥ አፈጻጸሙ መዘግየት የተስተዋለውም በዚሁ ምክንያት ተደጋጋሚ ጨረታ ለማውጣት በመገደዳቸው ተናግረዋል።

በአለም አቀፉ የግብርና መረጃ  መግለጫ  መሰረት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር  “በ2018 ወደ ኢትዮጵያ የገባው ዩሪያ 491,137 ቶን ነበር። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያ የምታስገባው  የዩሪያ መጠን  በከፍተኛ ሁኔታ ቢለዋወጥም እ.ኤ.አ. በ2004 – 2018 እየጨመረ በመምጣቱ  በ2018 491,137 ቶን ደርሷል” ሲል ያስቀምጣል። 

ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ እየገባበት ያለውን ሂደት ከግምት ውስጥ በማስገባት ቀድሞ የሚዘሩ አካባቢዎችን የመለየት ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል ። ክልሎች በአግባቡ ለማድረስ እየሰሩ መሆናቸውንም አክለው ተናግረዋል።

ሶፊያ ሚያዝያ 5 ቀን ለኢትዮጵያ ፓርላማ የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረቡት ሪፖርት፣ መንግስት ለ12. 8 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ የአንድ ቢሊዮን ዶላር የማዳበሪያ ግዥ ስምምነት ማድረጉን ገልጸዋል። ከዚህም ውስጥ 4.95 ሚሊዮን ኩንታል ለገበሬዎች የተከፋፈለ ሲሆን 3.5 ሚሊዮን ኩንታሉ በክልሎች በኩል መሰራጨቱን አስረድተዋ።ቀሪው 4.3 ሚሊዮን ኩንታል ደግሞ የጂቡቲ ወደብ መድረሱን ተናግረው እንደነበር ይታወሳል። 

እንደ ሚኒስትር ዲኤታዋ ከሆነ  ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ከፈፀመችው 17 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ የዘንድሮው ከ5 ሚሊየን ኩንታል በላይ ያነሰ ነው።  ይህም አጠቃላይ ከነበረው ፍላጎት 70 በመቶ ግዥ ነው ሲሆን ፤ በበልግ ወቅት ተጨማሪ ግዥ ሊኖር እንደሚችልም ጠቁመዋል።

ምንም እንኳን በኢትዮጵያ ማዳበሪያ ወደ ሃገር ውስጥ የማስገባት ስራላይ የሚኖረውን ቀጥተኛ ተፅዕኖ በተመለከተ የተገኘ መረጃ ባይኖርም ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈፀመችው ወረራ እና በአለም አቀፍ የማዳበሪያ አቅርቦት ላይ ያስከተለው ውጤት በአለም አቀፍ ደረጃ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል። በመጋቢት ወር ‘ግሮ-ኢንተለጀንስ’ የተባለ ተቋም  “ሩሲያ ማዳበሪያን  ለዓለም ከፍተኛ አቅራቢ ናት ፣ ነገር ግን ከዩክሬን ጋር የጀመረችው ጦርነት የምርቱን ዝውውር በማስተጓጎሉ ለማዳበሪያ ማምረቻ ግብአት የሆነው የተፈጥሮ ጋዝ ዋጋ እንዲጨምር አድርጎታል። የሩሲያ ባንኮችን ጨምሮ የምዕራቡ ዓለም ማዕቀብ ፋይናንስን በመገደቡ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን የበለጠ ሊቀንስ ይችላል። ወረራው እ.አ.አ በየካቲት 24 ከተፈጸም ጀምሮ የማዳበሪያ ዋጋ 32 በመቶ የጨመረ ሲሆን ዲያሞኒየም ፎስፌት እና ዳፕ ደግሞ 13 በመቶ ጭምረዋል” ሲል ረፖርቱ ያስረዳል። 

በተመሳሳይ ዩኤን የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት “ሙሉ በሙሉ ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡ በማዳበሪያ  ምርቶች ላይ ጥገኛ ናቸው እና እየጨመረ ያለው የማዳበሪያ ወጪ በምግብ አቅርቦት እና ዋጋ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።” ሲል አስጠንቅቆ ነበር። 

ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ  የፌደራል መንግስትና የክልል ባለስልጣናት አርሶ አደሩ እየደረሰበት ያለውን ጫና ለመቅረፍ የተፈጥሮ ማዳበሪያን እንደ አንድ ሌላ አማራጭ እንዲጠቀም  እየሞከሩ ነው። አርሶ አደሮቹ ግን የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘውትረው እንደማይጠቀሙና መሬታቸው ሰው ሰራሽ ማዳበሪያ እንደለመደ ገልጸዋል።

ምንም እንኳን የስጋቱ ተጋላጭ የሆኑት ከራሽያ እና ዪክሬን ከአጠቃላዩ የማዳበሪያ ዋጋ 15 እና 16 በመቶ የሚሆነውን የሚያስገቡት ኬንያ እና ኡጋንዳ ቢሆኑም  እንደ ዩኤን ገለጻ “ረጅሙ የዝናብ የእርሻ  ወቅት እየተቃረበ ሲመጣ፣ ከአማካይ በላይ የማዳበሪያ ዋጋ መጨመር የማዳበሪያ ፍላጎትን ሊቀንስ ይችላል። ከተጠበቀው  ከአማካይ በታች ዝናብ ጋር ተዳምሮ በሰብል ምርት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል፣  ይህም ዋና ሰብሎች በገበያ ላይ አለመኖርን  እና በመጨረሻም  የእህል ዋጋ ጭማሪን ያስከትላል” ሲል አብራርቷል። 

.

የተፈጥሮ ማዳበሪያ

ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ  የፌደራል መንግስትና የክልል ባለስልጣናት አርሶ አደሩ እየደረሰበት ያለውን ጫና ለመቅረፍ የተፈጥሮ ማዳበሪያን እንደ አንድ ሌላ አማራጭ እንዲጠቀም  እየሞከሩ ነው። አርሶ አደሮቹ ግን የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘውትረው እንደማይጠቀሙና መሬታቸው ሰው ሰራሽ ማዳበሪያ እንደለመደ ገልጸዋል።

የተፈጥሮ ማዳበሪያን በአግባቡ ለመጠቀም የተለያዪ ተግዳሮቶች እንዳሉም ይነገራል። ለምሳሌ በዚህ አመት የካቲት ወር ላይ  “በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በደቡብ ጎንደር ዞን በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኙ አነስተኛ አርሶአደሮችን “የተፈጥሮ ማዳበሪያ አጠቃቀምን የሚወስኑትን ነገሮች” ለመለየት  ባለመ  ጥናት መሰረት በጥናቱ ከተካተቱት 420 አነስተኛ አርሶ አደሮች መካከል “223 (53.10%) አነስተኛ አርሶአደሮች የተፈጥሮ ማዳበሪያ የተጠቀሙ ሲሆን  197 (46.90%) አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች የተፈጥሮ ማዳበሪያን እንዳልተጠቀሙ” ያሳያል።

” ጥናቱ እንደሚያሳየው የቤተሰብ አስተዳዳሪ እድሜ፣ የጋብቻ ሁኔታ፣ የትምህርት ደረጃ፣ የሰራተኞች ብዛት፣ የግብርና ልምድ፣ የእርሻ መጠን፣ የእንስሳት ብዛት፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያ መረጃ የማግኘት እድል፣ የኤክስቴንሽን አገልግሎት፣ የሠራተኛ ዋጋ፣ የቤተሰብ ገቢ፣ የአፈር ለምነት እና ከእርሻ እስከ ቤት ያለው ርቀት በተፈጥሮ ማዳበሪያ አጠቃቀም ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል።”

 አንድ ጥናት እንደሚያሳየው በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ከ40 በመቶ በታች የሚሆኑ አርሶ አደሮች ማዳበሪያን ይጠቀማሉ ያለ ሲሆን፣  “የሚጠቀሙት እንዲጠቀሙ ከተመከሩት በጣም ያነሰ ነው። ይህ ዝቅተኛ የማዳበሪያ አጠቃቀም በዋነኛነት ዋጋው በዓለም ገበያ ላይ ካለው ዋጋ ከሁለት እስከ ሶስት እጥፍ ስለሚበልጥ ነው” ሲል ያስረዳል። 

አዲስ ስታንዳርድ ቀደም ሲል መጋቢት 13 ቀን 2014 ዓ.ም  በአማራ ክልል የምስራቅ ጎጃም ዞን አርሶ አደሮች ወቅታዊውን የአቅርቦት እጥረት እና የማዳበሪያ ዋጋ ንረትን አስመልክቶ ለዞኑ አመራሮች ቅሬታቸውን ማቅረባቸውን መዘገቧ ይታወሳል።

በዞኑ ከሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ አርሶ አደሮች ተወካዮች ለዞኑ አስተዳደር እንደተናገሩት ለሰብል መኸር ምርት መቀነስ አንዱና ዋነኛው ምክንያት ወቅቱን የጠበቀ የማዳበሪያ አቅርቦት ባለመሟላቱ እና  ዋጋው እየጨመረ በመምጣቱ  ለችግሮቹ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን  ገልጸው ማዳበሪያውን በወቅቱ ለመግዛት እንዳይችሉ እና እንዳይጠቀሙ እንቅፋት እንደሆነባቸው አስረድተዋል።

የአርሶ አደሮቹ ተወካዮች በቂ ማዳበሪያ አቅርቦት አለመኖሩ በቀጣይ የእርሻ ወቅት  የምርት መቀነስ እና በአርሶ አደሩ ህይወት ላይ ተጨማሪ ጉዳት እንደሚያደርስ አሳስበዋል።በውይይታቸውም የዞኑ አመራሮች አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበው ሁኔታውን ለማሳለጥ ከየወረዳው የተውጣጣ ኮሚቴ አቋቁመዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በምስራቅ ጎጃም የሚገኙ አርሶ አደሮች የተፈጥሮ ማዳበሪያን እንዲጠቀሙ ለማድረግ ባለስልጣናት እየሞከሩ ነው። በምስራቅ ጎጃም ዞን የማቻከል ወረዳ አርሶ አደሮች መጋቢት 26 ቀን 2014 ዓ.ም ለመንግስት የመገናኛ አውታር እንደተናገሩት የተፈጥሮ/ኦርጋኒክ ማዳበሪያን በስፋት በማዘጋጀት እና በመጠቀም የግብርና ምርታማነታቸውን ለማሳደግ እየሰሩ እንደሆነ አስረድተዋል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.