ትንታኔ፡ የበርካቶችን ህይወት እየቀጠፈ ያለዉ የስትሮክ በሽታ የመንግስት ትኩረት ይሻል: ሃኪሞች

በሞላ ምትኩ @MollaAyenew

አዲስ አበባ፣ ህዳር 27/ 2015 ዓ.ም፡- የ29 ዓመቷ የትምወርቅ ደርቤ የቀን ስራዋን ከጠዋቱ 11 ሰዓት ለመጀመር በጠዋት ትጀምራለች።  የሁለት ልጆች እናት በመሆኗ እነሱን የመንከባከብ፣ ልብሳቸውን የማጠብ፣ የዕለት ምግባቸውን የማብሰልና መመገብ፣ ወደ ትምህርት ቤት የማድረስ እና ወደ ቤታቸው የመመለስ ኃላፊነት አለባት።  በተጨማሪም በሙያዋ ነርስ በመሆኗ በሥራ ቦታ ብዙ ሰዎችን መርዳት ይጠበቅባታል።  የትምወረቅ እንደ አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያን እናቶች የዕለት ተዕለት ተግባሯ በተጨናነቀና ፋታ በሌለው ሁኔታ የተቃኘ ነው።

አንድ ጠዋት ግን አቦው የቀን ጎደሎ እንደሚሉት ዓይነት ሆነና እንደተለመደው ስራውን ለመጀመር ከምኝታዋ ስትነሳ እንግዳ ነገር አጋጠማት።

“ለቤተሰብ ምግብ ለማብሰል በማለዳ ስነሳ እንግዳ ስሜት ተሰማኝ ።  አፌ ተሳሰረ ለመናገር ስሞክር መንተባተብ ጀመርኩ እንደዚሁም  በግራ እጄ እና እግሬ ደነዘዘ  ፊቴም ወደ አንድ በኩል ተጣመመ።  በፍጥነት ወደ መላ ሰውነቴን  ተዛመተ፣ ራሴን መቆጣጠር አቃተኝ” ስትል ገልጻለች።

የትምወርቅ ወደ አክሰን የስትሮክና ስፓይን ህክምና ማእከል ተወሰደች፡፡ ምርመራ ተደርጎላት  ለሦስት ቀናት ያህል አልጋ ይዛ እንዲትታከም ተደረገች። ትንሽ መሻሻል ስታይባት  ለሶስት ወራት ያህል የቅርብ ክትትል እየተደረገላት በቤቷ አርፋ መድሃኒት እንዲትወስድ ታዘዘላት። “ለሦስት ተከታታይ ወራት መድሃኒት ከወሰድኩ በኋላ ከሞት ተርፌ ወደ ሥራ መመለስ ቻልኩ” ትላለች።

ለየትምወርቅ ሕክምና  ያደረጉት ዶክተር ወንድወሰን ገብረአማኑኤል ሲሆኑ በአሜሪካን አገር ለረጅም ግዜ በዚሁ ስራ ሲያገለግሉ  የነበሩና አሁንም እያገለገሉ ያሉ ስፔሻሊስት ናቸው። ከውጭ አገር ተመልሰው በአዲስ አበባ ሲኤምሲ አካባቢ የስትሮክ ህክምና ማዕከል ከፍተው በጭንቅላት ላይ በደም መተላለፊያ ቧንቧ መዘጋት ወይም በቧንቧው መጎዳት ምክንያት የሚያጋጥም የደም መፍሰስ ምክንያት የሚፈጠረውን  ስትሮክ ያጋጠማቸውን ወገኖቻቸውን በመርዳት ላይ የሚገኙ የነርቭ ሐኪም ናቸው።

ምንም እንኳን በስትሮክ ምክንያት ለሞት ወይም ለዘላቂ የአካል ጉዳት የተዳረጉ ዝጎች ቁጥር ቀላል ባይሆንም የትምወርቅ ግን በሕይወት ለመትረፍ ከታደሉት መካከል አንዱ ሆናለች

እንደ የትምወርቅ ሁሉ በማዕከሉ ታክመው በህይወት የተረፉ በርካቶች እንዳሉ ዶክተር ወንድወሰን ይናገራሉ።    ዶክተሩ አያይዘውም  47 ወጣት ወንዶች ከኮማ ተነስተው ለሞት አደጋ ከሚዳርገው  ስትሮክ ተይዘው ከታከሙ በኋላ እንደገና በእግራቸው መሄዳቸውን እና 52 ሴቶች በግራ ጎናቸው ሽባ የመሆን ችግር ቢያጋጥማቸውም በተሳካ ሁኔታ የደም መርጋት ከአንጎላቸው መውጣቱን መስክረዋል።  ለዚህ ተግባር የሚውል  ትሮምቤክቶሚ የተባለና በኢትዮጵያ በአይነቱ የመጀመሪያው የሆነ መሳሪያን በመጠቀም እንደሆነ ተናገረዋል።  ከዚህም በተጨማሪ 65 ሴቶች የእይታ ችግር ያጋጠማቸው ሲሆን በተደረገላቸው ህክምና መዳናቸውን በቲዊተር ገፃቸው አስፍረዋል።

ጥናቶች እንደሚያመለክቱት የስትሮክ በሽታ በአገሪቱ እየተስፋፋ ምምጣቱንና ከስትሮክ ጋር በተያያዙ ለህልፈተ ህይወት የሚዳረጉ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ መዕጣቱን ነው። ይሁን እንጂ በቅርቡ ከተቋቋመው ከአክሰን ስትሮክ እና ስፓይን ሴንተር እንዲሁም በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆሲታል ውስጥ ካልሆነ አንድ ዲፓርትመንት በስተቀር ለስትሮክ ተጎጂዎች አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም አለመኖሩ ትኩረት እንዳክተሰጠው መናገር ይቻላል።

በዓለም ስትሮክ በገዳይነቱ  ሁለጠኛ ዘላቂ የአካል ጉዳት በማድረሱ ደግሞ ሶስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን  በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሀገራት  ላይ እያሳደረ ያለው ተፅእኖ  ከፍተኛ ነው። የዓለም ጤና ድርጅት እ.ኤ.አ. በ 2004 ዓ.ም ያወጣው ዘገባ እንደሚያመለክተው በዓለም 15 ሚሊዮን ሰዎች በስትሮክ ይጠቃሉ።  ከእነዚህም ውስጥ 5 ሚሊዮን የሚሆኑት ለህልፈተ ህይወት  የሚዳረጉ  ሲሆን ሌሎች 5 ሚልዮን ደግሞ  ቋሚ የአካል ጉዳት ስለሚደርስባቸው ለቤተሰብ እና ለማህበረሰብ ሸክም ይሆናሉ። በዚሁ ሪፖርቱ እንደተመለከተው  በኢትዮጵያ ከተመዘገበው አጠቃላይ የሞት ቁጥር ውስጥ አምስት በመቶው በስትሮክ ምክንያት የተከሰተ ነው።

በአዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ አጠቀላይ ሆስፒታል የኒውሮሎጂ ክፍል ሃላፊ የሆኑት  ዶክተር ፍቅሩ ፀሐይነህ  “ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ስትሮክ  ብዙም ተፅዕኖ ስላልነበረው  ትኩረት አልተሰጠውም” ይላሉ።  ይሁን እንጂ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ የስትሮክ ተፅእኖ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል ያሉት   ዶክተር ፍቅሩ  ምንም እንኳን በአገር አቀፍ ደረጃ የዳሰሳ ጥናት ባይኖርም ከሆስፒታሎች የሚወጡ ክሊኒካዊ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት  በኢትዮጵያ የስትሮክ ታማሚዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መጥቷል ብለዋል።

ዲክተር ያሬድ ዘነበ ዘውዴ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ኮሌጅ ዩኒቨርስቲ የነርቭ ስፔሻሊስት እና ተባባሪ ፕሮፌሰር ናቸው።  በጥቁር አንበሳ አጠቃላይ ሆስፒታል በየዕለቱ ለህክምና ከሚመጡት  ሰዎች መካከል ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑት በስትሮክ በሽታ የተያዙ ናቸው።  ስትሮክ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ቢመጣም መንግሥት ትኩረት እንዳልሰጠው ይናገራሉ።

ዶክተር ያሬድ አያይዘውም በሀገሪቱ ውስጥ የስትሮክ ህክምና አገልግሎት የሚሰጥበት ብቸኛው የመንግስት ሆስፒታል ጥቁር አንበሳ ነው።   ህክምናው የሚሰጠው በዲፓርትመንት ደረጃ ከመሆኑም በላይ የመሣሪያዎች እጥረት ስላለበት በቂ የሕክምና አገልግሎት ለህሙማን እየሰጠ ነው ማለት አይቻልም። በተቋሙ ያለው አንድ ሲቲስካን ብቻ በመሆኑ  ብዙ ታማሚዎች ተራ ለመጠበቅ ይገደዳሉ ይላሉ።

ስትሮክ በአብዛኛው  ከ50 እስከ 60 ዓመት የዕድሜ ክልል ያሉ ሰዎችን   ለሞትና ለዘላቂ ጉዳት የሚዳርግ ቢሆነም በአገሪቱ በቂ የስትሮክ ህክምና ማዕከል አለመኖሩን ዶክተር ወንድወሰን ገልፀዋል።  ማእከሉ ሃኣ አልጋዎች ያሉተ ሲሆን አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የስትሮክ ህክምና ማእከል በአዲስ አበባ ሲእምሲ አካባቢ የከፈቱት ዶክተር ወንድወሰን ማዕከሉ አስፈላጊ የሆኑ የስትሮክ ማከሚያ ማሽኖችን  እንዲያሟላ መደረጉን ይናገራሉ።  የትምወርቅ ደርቤ እና ሌሎች 164 ሰዎች በዚሁ ማእከል በዶክተር ወንድወሰን በተደረገላቸው ህክምና መዳን ችለዋል።

የማዕከሉ መከፈት በአዲስ አበባ እና አካባቢው ላሉ ነዋሪዎች ከፍተኛ እገዛ እንደሚኖረው ቢታመንም ከ120 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላት ኢትዮጵያ በርካታ ተመሳሳይ ተቋማት እንደሚያስፈልጓት ባለሙያዎች ያሳስባሉ። ዶክተር ያሬድ እንደሚሉት መንግስት ለስትሮክ የሚሰጠው ትኩረት በጣም አነስተኛ በመሆኑ ማሻሻል እንደሚገባ ይናገራሉ። ዜጎችም የበሽታው ምልክቶች ሲታዩባቸው በፍጥነት ወደ ህክምና መሄድ እንዳለባቸው ገልጸዋል። በሽታው በተከሰተ እስከ አራት ሰዓት ተኩል ባለው ጊዜ ውስጥ ወደ ሆስፒታሎች መድረስ ከቻሉ በሕይወት የመትረፍ እድላቸው ከፍተኛ ነው ይላሉ። ዶክተር ያሬድ አያይዘውም ይህ ካልተቻለ ጥቃቱ ከተከሰተ በ24 ሰአታት ውስጥ ወደ ህክምና ስፍራ መድረስ ይኖርባቸዋል ሲሉ ይመክራሉ።

“ስትሮክ ግዜ የማይሰጥ በሽታ በመሆኑ በአገሪቱ የሕክምና ማዕከላትን የማስፋፋት ስራ ሊሰራ ይገባል። አዳዲስ ተቋማት መገንባት ባይቻል እንኳን በሁሉም ሆስፒታሎች የስትሮክ ህክምና አግልግሎት የሚሰጥበት ሁኔታ ማመቻቸት ይገባል” ይላሉ። 

መንግስት እና የጤና ባለድርሻ አካላት በስትሮክ ላይ ለሚደርሰው ከፍተኛ ጉዳት ልዩ ትኩረት ሰጥተው ችግሩን ማቃለል የሚችሉባቸውን መንገዶች መፈለግ አለባቸው” ያሉት ዶክተር ያሬድ “የመገናኛ ብዙሃንም በስትሮክ ላይ ተገቢውን ግንዛቤ ለመፍጠር መስራት እንደሚጠበቅባቸው ዶክተር ያሬድ ያሳስባሉ።

እንደ ዶክተር ያሬድ ገለጻ ህብረተሰቡ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ ወይም በቀን ቢያንስ ለ30 ደቂቃ የጉልበት ስራ በመስራት ከስትሮክ ስጋት ራስን ሊጠብቅ ይገባል። የደም ግፊት፣ ስኳር፣ የስብ ክምችት፣ ሲጋራ ማጨስ እና የሰውነት ክብደት መጨመር ለስትሮክ በሽታ ስለሚያጋልጡ ከእነዚህ መራስን መጠበቅ ያሻል ብለዋል።

የስትሮክ ህክምና በጣም ውድ ከመሆኑም ባሻገር አገልግሎቱን የሚሰጡ ተቋማት በበቂ ሁኔታ ባለመኖራቸው ችግሩ እንዲባባስ አድርጎታል።ታካሚዎች የደም ሥሮችን ወይም የአንጎልን ክፍል ብቻ የሚለይ አንጂዮግራፊ እንዲደረግላቸው እስከ 60,000 (ስልሳ ሺህ) ብር መክፈል ይኖርባቸዋል። ከዚህ የመጀመሪያ እርምጃ በኋላ ህሙማኑ አስፈላጊውን ህክምና እና መድሃኒት ለማግኘት በመቶ ሺህ የሚቆጠር ብር መክፈል ይጠበቅበታል።

“ዘላቂው መፍትሄ የህክምና ማዕከላትን ማስፋፋት እና የህክምና ወጪውን የህዝቡን ኢኮኖሚያዊ አቅም ባገናዘበ መልኩ ማከናወን ነው” ያሉት ሚኒስትሩ “ምልክቶቹን እና የመከላከያ መንገዶችን በተመለከተ መገናኛ ብዙሃን በህብረተሰቡ ዘንድ ግንዛቤ በመፍጠር የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት ያህል መኖር አለባቸው” ብለዋል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.