በጌታሁን ለገሰ @Birmaduu2
አዲስ አበባ፣ጥር 25/ 2015 ዓ.ም፡– በደቡባዊ ኢትዮጵያ የኦሮምያ ክልል የሚገኘው የቦረና ዞን በምስራቅ አፍሪካ ከሚገኙ ሀገራት ባለፉት አርባ አመታት ባጋጠመው ድርቅ በከፍተኛ ሁኔታ ከተጎዱ አከባቢዎች ዋነኛው ነው። ከስምንት መቶ ሺ በላይ የሚሆኑት የዞኑ ነዋሪዎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ባለስልጣናቱ አስታውቀዋል።
ለአምስት ተከታታይ ግዜያት በተራዘመ ሁኔታ በአከባቢው ምንም አይነት ዝናብ አለመኖሩ የአከባቢውን ነዋሪዎች ህይወት የከፋ እንዲሆን አድርጎታል። በተለይም አርሶአደሮች ዋነኛ መተዳደሪያቸው በዝናብ ወቅት የሚያርሱት ሰብል እና የሚያገኙት የከብት መኖ በመሆኑ ድርቁ ይበልጥ ኑሯቸውነ አመሰቃቅሎታል፤ በርካታ እንስሳቶቻቸውን አሳጥቷቸዋል።
የአከባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ እስታንዳርድ እንዳረጋገጡት የምግብ እና ውሃ እጥረቱ የነዋሪዎችን ህይወት ቀጥፏል። ከብቶቻቸንን ትተን ህይወታችንን ለማትረፍ እየተጣጣርን ነው ሲል በዞኑ የአሬሮ ነዋሪ የሆነው በቃሉ አበራ ለአዲስ ስታንዳርድ ሁኔታውን ገልጿል።
በቦረና ታሪክ እንዲህ አይነት አስከፊ ጊዜ ኖሮ አያውቅም ሲል የገለጸው በቃሉ ሁኔታው በዞኑ ነዋሪዎች ላይ ያስቀመጠው ጠባሳ ከፍተኛ መሆኑ አስታውቋል።
በዞኑ የገጠር መንደሮች የሚገኙ ነዋሪዎች መንደራቸውን ለቀው ወደ ከተሞች በመሰደድ ላይ መሆናቸውን ጠቁሞ ድርቁ እጅግ ያዳከማቸው እና በእድሜ የገፉ ሰዎች ግን በመሞት ላይ ይገኛሉ ብሏል። በቃሉ በተጨማሪም በርካታ ሰዎች ቀናትን ያለ ምግብ እና ውሃ በማሳለፍ ላይ እንደሚገኙ አስታውቆ የተዳከመ አካላቸውን በማየት ብቻ የአከባቢውን ነዋሪዎች መለየት ይቻላል ብሏል። ሁኔታው ከቀጠለ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን ልናጣ እንችላልን ሲል ስጋቱን አጋርቷል።
የአሬሮ ወረዳ የኮሙዩኒኬሽን ሰራተኛ ዲንካ ዳዲ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደገለጸው የአከባቢው ነዋሪዎች የሚበላ ነገር ለማግኘት እየታገሉ መሆኑን ጠቁሞ ለጠኔ ተጋልጠዋል ብሏል።
ሁሉንም ነገር ሞክረው የየዕለት ምግብ ማግኘት ቢሞክሩም ምንም ማድረግ አልቻሉም ያለው ዲንካ ለሞት የሚዳርግ ረሃብ ተጸናውቷቸዋል፤ የህይወት አድን እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ሲል አሳስቧል።
አንዳንድ የእርዳታ ድርጅቶች ህይወት አድን ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ያስታወቀው ዲንካ ከቀውሱ ጋር ሲነጻጸር ይህ ነው የሚባል አለመሆኑን ጠቁሟል። በነዚህ የእርዳታ ድርጅቶች ብቻ ቀውሱን መከላከል እንደማይቻል ገልጿል።
ከምግብ አቅርቦቱ በተጨማሪ ከፍተኛ የሆነ የውሃ እጥረት መኖሩን ያስታወቀው የኮሙዩኒኬሽን ባለሞያው ነዋሪዎቹ የወንዝ እና የተቋሩ ውሃዎችን በመጠቀም ላይ በመሆናቸው ለውሃ ወለድ በሽታዎች ተጋልጠዋል ብሏል። አንዳንድ ነዋሪዎች ለኮሌራ በሽታ መጋለጣቸውን እና የተቋሩ ውሃዎቹም በመድረቅ ላይ በመሆናቸው የሚቀመስ ውሃ እየጠፋ መሆኑን ጠቁሟል። እድሜያቸው የገፋ እና ህጻናት በመሞት ላይ መሆናቸውን ዲንካ አስታውቋል።
የቦረና ዞን አስተዳዳሪ ጃርሶ ቦሩ በበኩላቸው በዞኑ ከሚገኙ አንድ ነጥብ ሰባት ሚሊየን ነዋሪዎች ስምት መቶ ሺ የሚሆኑት የድርቁ ሰለባ መሆናቸውን ለአዲስ ስታንዳርድ አስታውቀዋል።
ሁሉም 13 የዞኑ ወረዳዎች የድርቁ ሰለባዎች መሆናቸውን የገለጹት አስተዳዳሪው ባለፉት አምስት የዝናብ ወቅቶች ምንም አይነት ውሃ ባለመገኘቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ከብቶች መሞታቸውን፣ የተዘሩ ሰብሎች መውደማቸውን ጠቁመው ነዋሪው ለከፋ ድርቅ ተጋልጧል ብለዋል።
ውሃ ወለድ በሽታዎች በተለይም ኮሌራ እና ተቅማጥ በድርቅ በተመቱ አከባቢዎች መከሰቱን የተመለከቱ ሪፖርቶች መደረጋቸውን አቶ ጃርሶ አስታውቀዋል።
ድርቁን ለመቋቋም የአከባቢው ሰራተኞች እና ባለሃብቶች የገንዘብ ድጋፍ ቢያደርጉም እንዲሁም መንግስት እና በጎ አድራጎት ድርጅቶች ጉዳቱን ለመታደግ ጥረት ቢያደርጉም በአከባቢው ያለው ደርቅ የከፋ በመሆኑ ሊጠጣም አልቻለም ሲሉ አስተዳዳሪው ጃርሶ ገልጸዋል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት በ2022 ሰኔ እና ታህሳስ ወር መካከል በሶማሊ፣ ኦሮሚያና በደ/ብ/ብ/ህ/ክልልን ጨምሮ በአፍሪካ ቀንድ የሚገኙ 12 ሚሊዮን ህዝብ ለድርቅ የተጋለጡ መሆናቸውን ገልጧል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ጥር 18 ባወጣው ሪፖርት ድርቁ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ከጥር ወር ጀምሮ እጅጉን እንደሚጨምር ይጠበቃል ሲል ገልጧል፡፡አክሎም በኦሮሚያ ክልል ድርቅ በተከሰቱ አስር ወረዳዎች “ከባድ የውሃ እጥረት ተፈጥሯል” ብሏል።
በአካባቢዎቹ በታህሳስ ወር ላይ የተከሰተው የምግብ እጥረት ከጥር ወር የመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ከተከሰተው በ30 በመቶ በላይ ይጨምራል ሲል ሪፖርቱ ገልጧል፡፡
የክልሉ የአደጋ መከላከያ ተቋማትን አዲስ ስታንዳርድ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ምላሽ ባለማግኘቱ አልተሳካም። አስ