ቦረና ዞን ኤልወያ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮች እርዳታ በመጠባበቅ ላይ እያሉ፤ ፎቶ- አዲስ ስታንዳርድ
በብሩክ አለሙ @Birukalemu21 እና በመድኃኔ እቁባሚካኤል @Medihane
ቦረና/አዲስ አበባ፣ መጋቢት 27/2015 ዓ.ም፡- ለተከታታይ አምስት አመታት በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ ሁሉንም ከብቶቻቸውንና ንብረቶቻቸውን ያጡት የዱብሉቅ ወረዳ አርብቶ አደሮች ከወረዳው የተለያዩ 13 ቀበሌዎች በመፈናቀል በዱብሉቅ ከተማ ተጠልለው መኖር ከጀመሩ ከአንድ አመት በላይ ሆኗቸዋል፡፡ ከ9 ሺ በላይ አባወራ፣ ከ54 ሺ ባላይ ተፈናቃዮችን የያዘው የዱብሉቅ መጠለያ ካለው የተፈናቃዮቹ ብዛት የተነሳ እየተደረገ ያለው ድጋፍ በቂ አለመሆኑን ተፈናቃዮችና የወረዳው አስተዳደር ኃላፊ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል፡፡ ከሰዎች ብዛት የተነሳ የሚላክላችውን እርዳታ ለሁሉም ተፈናቃይ ማዳረስ ፈተና ሆኖብናል ይላሉ ኃላፊው፡፡
በዱቡሉቅ ወረዳ ብቻ ከ43 ሺ በላይ ከብቶች በድርቁ መሞታቸውን እና ዝናብ ከመዝነቡ ማለትም ከሁለት ሳምንት በፊት መንቀሳቀስ የማይችሉ እጅግ የተዳከሙ ከ20 ሺ የሚሆኑ ከብቶች መኖራቸው የሚገልፀው የዱብሉቅ ወረዳ አስተዳደር ኃላፊ አብዱልቃዲር አሊ እነዚህ ከብቶች የመትረፍ እድላቸው እጅግ አነስተኛ መሆኑን በስፍራው ለተገኙ የአዲስ ስታንዳርድ ጋዜጠኞች ተናግሯል፡፡
ገልመ ጉሌ ከዲሬ ወረዳ ተፈናቅሎ በዱብሉቅ መጠለያ ጣቢያ ከተጠለለ አንድ አመት ሞልቶታል፡፡ በመጠለያው ውስጥ ያለው መሰረታዊ የሰብዓዊ እርዳታ ችግር ከመክፋቱ የተነሳ የልጆቻቸውን ፍላጎት ማሟላት በለመቻላቸው እራሳቸውን ያጠፉ በርካታ ሰውች መሆራቸውን ይገልፃል፡፡ ገልመ ጉሌ “በድርቁ በርካታ ከብቶቻቸውን በማጣታቸው እና ልጆቻቸው ሲራቡ ማየት ከብዷቸው እራሳቸውን ሰቅለው እንዲሁም የተቆፈረ ውሃ ውስጥ ገብተው የሞቱ ሰዎች አሉ” ሲል ስለ ድርቁ አስከፊነት ለአዲስ ስታነዳርድ ገልጧል ፡፡
እየተደረገላቸው ያለውን ድጋፍ በተመለከተም ለአንድ አባወራ የሚደርሰው ዱቄት ከአስር ጣሳ የማይበልጥ መሆኑን ይገልፃል፡፡ ለተከታታይ አምስት አመታት ዝናብ ባለመዝነቡ ከብቶች በሞት ማለቃቸውን እና ሰዎችም መሞት መጀመራቸውን ገልፆ አሁንም ድጋፉ የሚቋረጥብን ከሆነ የሰዎች ሞት የማይቀር ነው ብሏል፡፡
“እኛ ልምና አናቅም ነበር፣ ውሃ ለሚጠይቀን ወተት ነው የሚንሰጠው ሲቸግረን ወይ ፍየል ወይ ክብት አውጥተን እንሸጣለን አሁን ግን በድርቁ ሁሉም ከብቶቻችን አጥተናል፡፡ እየተደረገልን ያለው ድጋፍ ካቆመ ውይም ከቀነሰ ሞሞታችን ነው፡፡” ሲል ገልጧል፡፡
ከዱብሉቅ ወረዳ በ36 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከምትገኘው ከቦኮክሳ ቀበሌ የተፈናቀሉት አዲ አሬሮ በመጠለያ ውስጥ መኖር ከጀመሩ አስር ወራት እንዳለፉ ጠቅሰው “በድርሱ ሳብያ ሁሉም ከብቶቻችን ከመሞታቸው በፊት የሰው እጅ አይተን አናውቅም ነበር፤ ከብቶቻችን ከእኛም አልፈው ለሌላውም ይተርፉ ነበር፡፡ አሁን ግን ሁሉንም አጥተን የሚቆነጠርልንን ዱቄት ጠባቂ ሆነናል” ሲል ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል፡፡
ምግባችንንም ሆነ የሚያስፍልገንን ነገር ሁሉ የምናገኝው ከከብቶቻችን ነው የሚሉት አዲ አሬሮ አሁን ግን ይህ ሁሉ ታሪክ ሆኖ ቀርቷል፤ ያማረንን መብላት፣ የሚያስፈልገንን መሰረታዊ ነገሮች ማግኘት ቀርቶ በቀን አንዴ እንኳ መመገብ የማንችልበት ሁኔታ ውስጥ ነን በማለት ይናገራሉ፡፡
በመጠለያው ውስጥም ለአንድ አባወራ የሚሰጠው እርዳታም አስከ አስር ጣሳ ዱቄት መሆኑን የሚገልፁት አዲ አሬሮ አየተደረገ ያለው እርዳታ በቂ ባለመሆኑ በእድሜ የገፉ ሰዎች እና ህፃናት እየተጎዱ ነው ሲሉ አክለው ገልፀዋል፡፡ መንግስት በተለይ ለአዛውንቶች፣ ለልጆችና ለተማሪዎች የተለየ ትኩረት ሰጥቶ እንዲረዳም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመጠለያው ውስጥ ከስምንት ልጆቻቸው ጋር የሚኖሩት አዲ አሬሮ ልጆቻቸውን የማስተማር አቅም በማጣታቸው ልጆቹ ትምህርታቸውን ማቋረጣቸውን ገልፀዋል፡፡ አክለውም የተፈናቃዮቹ ቁጥር ካለው የትምህርት ቤት የመቀበል አቅም ጋር የማይመጣጠን በመሆኑም በትምህርት ገበታ ላይ ያልሆኑ ልጆች በርካታ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
ሌላኛዋ የመጠለያው ነዋሪ የሆኑት አንድ እናት “በመጠለያ ውስጥ ፍትሃዊ የሆነ የእርዳታ ምግቦች ክፍፍል የለም፤ በተለይ እንደኛ አዲስ ለመጡ እና በቡድን ላልተደራጁ ተፈናቃዮች ምንም እይሰጥም፤ ስንሄድ ጠብቁ ይሉናል፤ ስንጠብቅ እንውልና ሲመሽ በቃ ነገ ተመለሱ ይሉናል፤ በንጋታው ስንመለስ ደግሞ በቡድን ለተደራጁት ይሰጣል፤ እኛ ምንም ሳናገኝ እርዳታ በመጣ ቁጥር ደጋግመው የሚወስዱም አሉ፤ እኛ በዶ እጃችንን እንመለሳለን ያለንብት ችግር ተነግሮ የሚያልቅ አይደለም ልጆቻችን በረሃብ እየተጎዱብን ነው፡፡” ሲሉ በምሬት ተናግረዋል፡፡
ገራቾ ደዳ ከፍሊንቃ ቀበሌ ተፈቃቅሎ ለአንድ አመት ያህል በመጠለያው ውስጥ ኖሯል፡፡ ገራቾ እንደሚገልፀው አሁን ተፈናቅለው ያረፉበት አካባቢ ድሮ ከብቶቻቸውን ይዘው መጥተው የሚሸጡበት ቦታ ነው፡፡ “ከብቶቻችን በድርቁ አለቁብን ፍየሎቻችንን ደግሞ እኛ ተመግበን አለቁ፣ ባዶ እጃችንን ስንቀር ለህይወታችን በመስጋታችን ወደ መንገድ ዳር ቀረብ በማለት መንግስት እንዲያየን ወደዚህ አካባቢ ተፈናቅለን መጣን” ሲል ወደ ዱብሉቅ የመጡበትን ሁኔታ ያስረዳል፡፡
ገራቾ እንደሚገልፀው ወደ ዱብሉቅ ተፈናቅለው መምጣታችው ህይወታቸውን ያቆየላቸው መሆኑን ጠቅሶ ነገር ግን እየተደረገላቸው ያለው እርዳታ በቂ አለመሆኑን በስፍራው ለነበሩ ለአዲስ ስታንዳር ጋዜጠኞች አስረድቷል፡፡ አሁላይ እየተደረገ ያለው እርዳታም በቅርብ የተጀመረ መሆኑን ገልፆ ቀደም ሲል ግን የምግብና የውሃ እጥረት በከፍተኛ ሁኔታ መኖሩን ገልጧል፡፡
ከአርባ ስምንት ከብቶች በላይ በድርቁ ያጣው ወጣቱ ገራቾ በመጠለያ ውስጥ የውሃ፣ የምግብና የመጠለያ እጥረት መኖሩን በአፅንዖት ተናግሯል፡፡ “ በመጠለያ ውስጥ ያለው አራት የዉሃ ታንከር ብቻ ነው፣ በሰው ብዛት የተነሳ አራቱም ታንከሮች ከአንድ ቀን በላይ አያቆዩም፤ ሌላው የመጠለያ እጠረት አለብን፤ እንደምታዩት ሸራ ወጥረን ነው ውስጡ የምናድረው ቀን ቀን ሙቀት አለው ማታ ደግሞ ብርዱ አያስተኛም፤ አብዛኞቹ ሸራዎች ፀሃይ በልቷቸዋል፤ አንዳንዶቹም ተቀደዋል፡፡ ዝናብ ሲዘንብ በስብሰን ነው የምናድረው፣ ደና መጠለያ ባለመኖሩ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ከቶናል” ብሏል፡፡
እስከ ቅርብ ግዜ ድረስ ምንም አይነት እርዳታ እየደረሳቸው እንደልነበር በመጠለያ ውስጥ ያገኘናቸው ኤሌማ ቦሩ የተባሉ አንድ እናት ገልፀው አቅም ያለቸው እንጨት እየቆረጡ በመሸጥ እራሳቸውን እንደቆዩ አስረድተዋል፡፡ አሁን ላይ ግን በተሻለ መልኩ እርዳታ እየደረሳቸው እንደሆነ ቢገልፁም በቂ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከ 178 ክብቶች 4 ከብቶች ብቻ የተረፉላቸው፤ በዚህም የተነሳ በሀዘንና በጭንቀት የአዕምሮ እክል ደርሶባቸው ለ38 ቀናት ከትትል ተደርጎላቸው ወደ ጤንነታቸው የተመለሱት አቶ ሁሴን ሻኔ “ድሮ ቦረና መጥተህ ውሃ ብትጠይቅ ወተት ነው የሚሰጥህ፣ ዛሬ ግን ኪንን የሚውጥበት ውሃ እንኳን የለውም፤ የቦረና ህዝብ ለምኖ አያውቅም ነበር ዛሬ ግን የሰው እጅ ጠባቂ ሆነናል፡፡” ሲል ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግሯል፡፡ በመጠለያ ውስጥ የሚሰጠው እርዳታ ለ45 እስከ 30 ለሚሆን ሰው ከ4 ቁምጣ ያልበለጠ ዱቄት ብቻ ነው፣ በማለት የሚናገረው አቶ ሁሴን ለአንድ አባወራ የሚደርሰው ከ5 ኪሎ ያልበለጠ ዱቄት መሆኑን በሀዘን ስሜት ተሞልተው ገልፀዋል፡፡
አክለውም የታመሙ ሰዎች ለህክምና ሲሄዱ መድኃኒት እዚህ ስለሌለ ከውጭ ግዙ እንደሚባሉ ገልፀዋል፡፡ “እዚህ ያለው ህዝብ ወደ መጠለያው የገባው በችግር ምክኒያት ነው፤ የመድኃኒት መግዣ ከየት ያመጣል፤ ስለዚህ አማራጭ ስለሌለው ቤቱ ገብቶ ሞቱን መጠባበቅ ነው ያለው አማራጭ፤ በዚህ የተነሳ የሞቱ ሰዎች አሉ፤ በረሃብ የሞቱ አዛውንቶች አሉ” በማለት ገልጧል፡፡
“ተፈናቃዮቹ የመጠለያ ችግር አለባቸው፣ የማደሪያ ቦታዎች ምቹ አይደሉም ቀን ሙቀት አለው ማታ ደግሞ ብርዱ ከባድ ነው፣ ዝናቡም ለህመም እየዳረጋቸው ነው፤ የሰውች ቁጥር በየቀኑ እየጨመረ በመሆኑ እየተደረገ ያለው የምግብ እረዳታ አነስተኛ ነው፤ ሌላው የመድኃኒት አቅርቦት ችግር አለ፣ ከተፈናቃዮቹ ብዛት አንፃር በቂ መፀዳጃ ቤትም የለም፣ እንዲሁም በወረዳው በሚገኙ ጣቢያዎች ውስጥ ውሃ የሚያድርስ ተሸከርካሪዎች እጥረት ስላለ በበቂ ሁኔታ ውሃ ማድረስ አለተቻለም” ሲል የዱብሉቅ ወረዳ አስተዳደር ኃላፊ አብዱልቃዲር አሊ ለአዲስ ስታንዳርድ ሃሳቡን አካፍሏል፡፡
ህፃናት፣ በእድሜ የገፉ ሰዎች እና የሚያጠቡ እናቶች እየተጎዱ በመሆኑ ለእነሱ የተለየ ምግብ እና ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል የሚለው ኃላፊው ሁሌም እየተረዱ መኖር ስለማይችሉ መልሶ የማቋቋም ስራ መሰራት እንደለበት ገልጧል፡፡ አክሎም ዝናብ እየዘነበ በመሆኑ ማረስ ሲኖርባቸው የሚያርሱብት ከብቶች በድርቁ በማለቃቸው ድጋፍ ተደርጎላቸው እራሳቸውን እንዲችሉ መደረግ ግድ ነው ብሏል፡፡ ነገር ግን በግብርናና በመሳሰሉተ ስራ እራሳቸውን እስኪችሉ ድረስ እየተደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስቧል፡፡
ዝናቡ ያስከተለው ተጨማሪ ተፅዕኖ
ለአምስት አመታት በቦረና ምድር ላይ ሳይዘንብ የቆየው ዝናብ ከሶስት ሳምንት በፊት ምድሪቱን እያራሳት ቢገኝም ነገር ግን ሌላ ተጨማሪ ተፅዕኖ እያስከተለ ይገኛል፡፡ አብዱልቃዲር አሊ እንደሚለው ተፈናቃዮቹ ለመጠለያነት እየተጠቀሙበት ያለው የፕላስቲክ ሸራ አብዛኛው የተቀዳደደ በመሆኑ የሚዘንበው ዝናብ ተፈናቃዮቹን እያራሰ ለብርድና ለተለያዩ ህመሞች እየዳረጋቸው ይገኛል፡፡ ጎርፍ በመጠለያቸው ውስጥ በመግባት በእርዳታ የተሰጣቸውን ምግብ እያበላሸባቸው እንደሚገኝ ገልጧል፡፡
በመጠላያ ጣቢያው ውስጥ በተኛው ውሃ ሳቢያ የወባ እና ኮሌራ በሽታ ይነሳል የሚል ስጋት እንዳለ የሚገልፀው ኃላፊው በዚህ ሰሞን ብዙ ሰዎች ላይ ሳል እየተስተዋለ ይገኛል ሲል ገልጧል፡፡
የውሃ ማከሚያ ምድኃኒትና አጎበር በስቸኳይ መዘጋጀት አለ በማለት ጥሪ ያቀረበው አብዲልቃድር እስካሁን የተላከላቸው የውሃ ማከሚያ መዳኒት መኖሩን ገልፆ ነገር ግን በቂ አይደለም ሲል ተናግሯል፡፡
አሁን ድረስ ሸራ ያላገኙ፣ በተበጣጠሰ ሸራ ውስጥ ሆነው በዝናብ የሚደበደቡ ተፈናቃዮች መኖራቸውን ለአዲስ ስታንዳርድ ያስረዳው ኃላፊው መንግስትም ሆነ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅቶች የአጎበር፣ ሸራ፣ የምግብና የመድኃኒት ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በድርቁ ሁሉንም ከብቶቻቸውን ያጡት የቦረና ዞን አርብቶአደሮች አርሰው እርዳታ ከመጠበቅ መላቀቅም አልቻሉም፡፡ ተፈናቃዮቹ ሁሉንም ከብቶቻቸውን በድርቁ በማጣታቸው አርሰው እራሳቻውን መዶገም አልቻሉም የሚለው አብዱልቃዲር “ዘር አዘጋጅተን በትራክተር እንዲያርሱ ለማድረገ ብንሞክርም ትራክተር ማግኘት አልቻልም፡፡ ዞኑንም ትራክተር እንዲሰጠን ጠይቀናል ተከራይተንም እንዲያርሱ ለማድረግ ሞክረናል ግን ማግኘት አልቻልም፡፡ አንዳንድ ሰዎች በእጃቸው ለማረስ እየሞከሩ ነው፡፡” ሲል አስረድቷል፡፡
ሰሞኑን በዘነበው ዝናብ በሁለት ሳምንት ውስጥ ብቻ በወረዳው ከ5700 በላይ ፍየሎች ሞተዋል ያለው ኃላፊው የሞታቸው ምክኒያት በድርቁ ተዳከመው የነበሩ በመሆኑ ዝናብ እና ብርዱን መቋቋም ባለመቻላቸው ነው ሲል ገልጧል፡፡
በመጨረሻም ተፈናቃዮቹን መልሶ ማቋቋም ስለሚያስፈልግ የዘር፣ የማዳበሪያ፣ የትራክተር እና የመሳሰሉትን በመለገስ እራሳቸውን እንዲደግፉ ማድረግ ያስፈልጋል ብሏል፡፡
በኤልወያ አምቦ (አምቦ ጢቂቲ) የተፈናቃይ ካምፕ ያለው ችግር
የቦረና ዞን ዋና ከተማ ከያቤሎ ወደ 100 ኪሎ ምትር ርቀት ላይ የሚገኘው የኤልወያ ተፈናቃይ ካምፕ ውስጥ ያለው ችግር ከዱብሉቅ የሚለይ አይደለም፡፡ ተፈናቃዮቹ የሚደርሳቸው እርዳት ጥቂት ከመሆኑ የተነሳ ልጆችና አዛውንቶች በምግብ እጠረት የተነሳ ለክፍተኛ ረሃብና ህመምና ተዳርገዋል፡፡ በመጠለያው ውስጥ የአዲስ ስታንዳርድ ጋዜጠኞች ያገኛጋገሯቸው ተፈናቃዮች እንደሚሉት በርካታ ሰዎች ረሃቡ ባስከተለባቸው ህመም ለሞት ተዳርገዋል ሲሉ ገልፀዋል፡፡
ከዘጥን ወር በፊት መከኒሳ ከሚባል አካበቢ በመፈናቀል ወደ ኤልወያ መጠለያ ጣቢያ መግባቷን የምታስረዳው ደኪ ገልማ የተባለች ወጣት ለረጅም ጊዜያት ምንም አይነት እርዳታ እንዳልደረሳቸው ገልፃ በወቅቱ በርካታ አዛውንቶች አቅም አንሷቸው የሞት አፋፍ ላይ ደርሰው ነበር ብላለች፡፡ “አንድም ከብት አልቀረልንም ሁሉንም ነው በድርቁ ያጣነው ከዛ በኋላ ነው ወደዚህ ስፍራ የተሰባሰበነው” የምትለው ደኪ እዚህም ከመጣን በኋላ የሚጠለሉበት ሻራ እንኳ አጥተው ወደ ከተማ ሄደው እየለመኑ መንገድ ዳር የሚያድሩ በርካቶች ናቸው ስትል ተናግራለች፡፡
የቀበሌው ሃላፊ የሆኑት ሃፒ ገርቢቻ በመጠለያ ጣቢያው ውስጥ ከአንድ ሺ አንድ መቶ አስር በላይ የሚሆኑ አባወራዎች እንደሚገኙ ይገልፃሉ፡፡ ከአራት መቶ በላይ የሚሆኑ ከአጎራባች ቀበሌዎች የተፈናቀሉ ሰዎችም በቅርቡ ተፈናቅለው እንደመጡ የሚገልፁት ሃፒ በመጠለያው ውስጥ የእርዳታ እጥረት መሆሩንና ሰዎች በህክምና እጦች በህመም አየሞቱ ነው ብለዋል፡፡
አክሎም ወደ መጠለያው ከመቋቋሙ በፊት የሚበሉት አጥተው ሜዳ ላይ ወድቀው ህይወታቸው ያለፈ በርካቶች መኖራቸውን ለአዲስ ስታንዳርድ ገልፀዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ከ30 በላይ የሚሆኑ ልዩ ትክረት የሚሹ የተዳከሙ አዛውነምቶች አሉ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
እርዳታ ያልደረሳቸው ተፈናቃዮች ከገጠር ወደ ከተማ…
በስፍው የነበሩ የአዲስ ስታናንዳርድ ጋዜጠኖች እርዳታ ካልደረሰባቸው አካባቢ ወደ ያቤሎ ከተማ የመጡ የድርቁ ተጎጂዎች እርዳታ ጭነው በከተማዋ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ተሸከርካሪዎችን በመከተል ከጫኑት እረዳታ እንዲያካፍሏቸው ሲጠይቁ ተመልክተዋል፡፡ አዲስ ስታንዳርድ ያነጋገራቸው እንዚህ ሰዎች ከነበሩበት ስፍራ ምንም እርዳታ እንዳልደረሳቸው በመግለፅ ወደ ያቤሎ ከተማ አስተዳደር በመሄድ እርዳታ ቢጠይቁም ሊስተናገዱ አለመቻላቸውን ገልፀው በከተማዋ ውስጥ እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎችን እየተከታተሉ እንዲያካፍሏቸው ለመለመን መገደዳቸውን አስረድተዋል፡፡
ከዩብዶ ቀበሌ ነው የመጣነው የሚሉ ከ25 በላይ የሚሆኑ ሴቶች በያቤሎ ከተማ በመዘዋወር የሚያገኙትን እርዳታ ይዘው በረሃብ ውስጥ ለሚገኙት ቤተሰቦቻቸው ይዘው እንደሚሄዱም አስረድተዋል፡፡
በቦረና ዞን የተገኙት የአዲስ ስታንዳርድ ጋዜጠኞች በሁሉም መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ተመሳሳይ ችግር መኖሩን የተረዱ ሲሆን በዋናነት የምግብ፣ ለመጠለያነት የሚያገለግል ሸራ፣ አልባሳት፣ የህክምና መድኃኒቶች፣ ለእርሻ የሚውሉ ቁሶች ( ትራክተርን ጨምሮ) እርዳታ ቅድሚያ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ከተፈናቃዮቹ ተረድተዋል፡፡አስ