አቶ ሀብታሙ ኪታባ የቀድሞ የኢዜማ ስራ አስፈፃሚ አባል
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16/2015 ዓ.ም፡- አቶ ሀብታሙ ኪታባ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ ከመስራች ኮሚቴ አንዱ ሲሆኑ በስራ አስፈፃሚነትም አገልግለዋል፡፡ አቶ ሀብታሙ በተለያዩ የስራ ሃላፊነቶች ላይ ያገለገሉ ሲሆን፣ በፖሊሲ ዝግጅት ላይ የኢኮኖሚ ክላስተር ፖሊሲ አስተባባሪ ሆነው ሰርተዋል፡፡ በተጨማሪም የኢንቨስትመንት ፖሊሲን በቀጥታ የሚቀርጽ ኮሚቴን መርተዋል፡፡ ትይዩ ካባኔ መዋቅር ውስጥ ከገቢዎች አንፃር ትይዩ ሆነው ሰርተዋል፡፡ በአዲስ አበባ በምርጫ ክልላቸውም ስራ አስፈፃሚ ሆነው ሰርተዋል፡፡ በተጨማሪም ለኢዜማ መሪነት በተደረገ ምርጫ ውድድር ላይ አንዷለም አራጌ ለመሪነት ሲወዳደሩ አቶ ሀብታሙ ለምክትል መሪነት ተወዳድረዋል፡፡
አቶ ሀብታሙ ኪታባ በቅርቡ ከኢዜማ ፓርቲ ከለቀቁ ሰባት ስራ አስፈፃሚ አባላት መካከል አንዱ ናቸው፡፡ ከኢዜማ በጋራ ከመልቀቃቸው ጋር ተያይዞ ከአዲስ ስታንዳርዱ ጋዜጠኛ ብሩክ አለሙ ጋር ያደረጉት ሙሉ ቃለ መልልስ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
አዲስ ስታንዳርድ፡- በቅድሚያ ለቃለ-መጠይቁ ፍቃደኛ ስለሆኑ እያመሰገንኩ ወደ መጀመሪያ ጥያቄዬ ላምራ፡፡ ኢዜማ ጥሩ የህዝብ ድጋፍ ያለው ተገዳዳሪ ፓርቲ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከቅርብ ጊዜ በኋላ ግን ፓርቲው ውስጥ አለመግባባት መፈጠሩ ተሰምቷል፡፡ በቅርቡ እርሶን ጨምሮ ሰባት አባላት ከፓርቲው መልቀቃችሁን ይፋ አድርጋችኋል፡፡ ኢዜማ ውስጥ ምንድነው የተፈጠረው? ከፓርቲው የተለያያችሁበት ግልፅ ምክንያት ምንድነው?
አቶ ሀብታሙ ኪታባ- ከኢዜማ የለቀቅንበት አንደኛው ምክንያት፤ ለምንድነው አባሉ ከኢዜማ የሚለቀው? ለምንድነው የህዝብ ተቀባይነቱን እያጣ የመጣው? ለምንስ ነው ኢዜማ አማራጭ ፓርቲ መሆን እያቃተው የመጣው? የሚለው ጥያቄ ላይ ያለን የእይታ መለያየት እና የሀሳብ ልዩነቶችን ለመፍታት ጉባዔ ተጠርቶ እንድንወያይ የምናነሳው ጥያቄ እየታፈነ ስለሄደ በፓርቲው መሃል መቆየት ትርጉም የሌለው ስለሆነ ነው፡፡ ዋናው እና መሰረታዊው ምክንያት ኢዜማ ለተነሳበት ለራሱ አስተሳሰብ፣ ለራሱ ፕሮግራም ቆሞ አማራጭ መሆን አለመቻሉ ነው፡፡ አላማችን ፓርቲው ለኢትዮጵያ ውጤት ያለው፣ ለህዝብ የሚጠቅም ነገር ይውጣው የሚል ሆኖ ሳለ አመራር ላይ ያለው ቡድን ይህ ሀሳብ በጉባዔ እንዳይታይ በሮችን እየዘጋ በማስቸገሩና በውይይት ሊፈታ ባለመቻሉ ከፓርቲው ለቀናል፡፡ የተፈጠረው መሰረታዊ ልዩነት አማራጭ ሆኖ መውጣት አለመቻላችን ነው፤ ለዛ ደግሞ በሚረዳ መንገድ ጉባዔው ተሰብስቦ ውሳኔ እንዲሰጥ ብንጠይቅም የተሰጠው ምላሽ እንደጠበቅነው ስላልሆነ እነሱ ባመኑበት መንገድ ፓርቲውን ይምሩት እኛ ደግሞ ከፓርቲው ወጥተን ቢያንስ ከህሊና ተጠያቂነት እንዳን በሚል ነው፡፡
አዲስ ስታንዳርድ- ለምን ከፓርቲው ሳትለቁ በውስጥ ሆናችሁ መታገልን አልመረጣችሁም ? አሁን እንደጠቀሱት ፓርቲው ውስጥ መቆየት ከተጠያቂነት አያድንም ብላችሁ ነው ወይስ ሌላ ምንክንያት አላችሁ? በመካከላችሁ የተፈጠረውን ልዩነትንስ ለመፍታት ምን ያህል ጥራችኋል ?
አቶ ሀብታሙ ኪታባ- ውስጥ ሆነን ለሶስት አመታት ታገልናል፡፡ ኢዜማ ውስጥ ባሉት መድረከች ሁሉ ታግለናል፤ በመካከላችን የነበረው ልዩነት ፓርቲው በተመሰረተ በወራት ውስጥ ነው የጀመረው፤ የፓርቲው መሪ ብልፅግናን የሚስቡበት መንገድ፣ ለእኛ መጥተው የሚያስረዱበት መንገድና እኛ የምናይበት ምንገድ የተራራቀ የነበረው ገና ከፓርቲው ጅማሮ ነው፡፡ ይህንን ለመፍታት ብዙ ጥረናል፣ አመታዊ ግምገማችንን ስናደርግ ከውጭ ያሉ የፖለቲካ ሰዎችን ጋብዘን ጥናታዊ ፅሁፍ እንዲያቀርቡ አድርገናል፡፡ በርካታ ውይይቶች አድርገናል፣ ምርጫ ክልሎች አቋም እየያዙ ወደ ማዕከል እየላኩ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ ነገር ግን ማዕከል ላይ ያለው መዋቅር ምክንያታዊ የሆነ ውሳኔ መስጠት አልቻለም እንጂ እኛ በርካት ጥረቶች አድርገኛል፡፡
“ኢዜማን ስንመሰርተው የነበሩት አባላት እየለቀቁ አሁን ላይ በማዕከል ከሚንቀሳቀሱ የተወሰኑ ሰዎች በስተቀር እዚህ ግባ የሚባል አባላቶች የሉትም፡፡ ይህ በተጨባጭ ማረጋገጥ የምትችለው እውነታ ነው፡፡ ለምሳሌ እኔ ያለሁበት 12/13 የምርጫ ክልልን ብትወስድ ስንጀምር ከነበሩ አባላት ውስጥ አሁን የቀሩን 10 በመቶ ቢሆኑ ነው፡፡ በአማራ ክልል ስንጀምር ካለው አባል አሁን የቀረው አባል 7 ወይ 8 በመቶ አይበልጥም፡፡ አሮሚያ ክልል ላይ ሁሉም መዋቅሮች ጠፍተዋል ማለት ይቻላል፡፡ “
አዲስ ስታንዳርድ- ኢዜማ ውስጥ ልዩነት የተፈጠረው ፓርቲው በተመሰረተ በወራት ውስጥ ነው ብለውኛል፡፡ ፓርቲውን ስትመሰርቱ ግልፅ የሆነ የፓርቲው ፖሊሲና ስትራቴጂ መረዳት አልነበረም ? በመካከላችሁ የአላማ አንድነትስ አለነበረም? እንዴት ፓርቲው በተመሰረተ በወራት ውስጥ በመካከላችሁ ልዩነት ሊፈጠር ቻለ ?
አቶ ሀብታሙ ኪታባ- የተፃፈው ላይ የአላማ አንድነት ነበር፤ ግን ልዩነቱ ያለው አካሄድና አተገባበር ላይ ነው፡፡ ፓርቲው የጋራ አቋሞች ይይዛል፤ ለምሳሌ የጉራጌን ክልል የመሆን ጥያቄን በተመለከተ ኢዜማ የያዘው አቋም አለ፡፡ እኛ የያዝነው አቋም ብልፅግና ከያዘው አቋም የተለየ ነው፡፡ የብልፅግና ፕሬዘዳንት የፓርቲያቸውን አቋም ለማንፀባረቅ ወልቂጤ ጉዞ ሲያደርጉ አብሯቸው ተጉዘው ንግግር ያደረጉት የኢዜማ ፓርቲ መሪ ናቸው፡፡ ከራሳቸው ፓርቲ አቋም ተቃርነው የብልፅግናን አቋም ደግፈዋል፡፡ ፓርቲው የያዘው አቀቋም እያለ በአተገባበር ግን የኢዜማን መሪ አቋም የሚደግፍና የሚተገብር አካል ወጥቶ ፓርቲው ከያዘው አቋም በተቃራኒ ሲሰራ ይታያል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚንስቴሩ የፃፉት የመደመር መፅሓፍ ላይ ውይይት ሲዘጋጅ እንደ ኢዜማ መሪ መቃወም ሲገባቸው ማብራሪያ ለመስጠት ከሚገኙ አካላት መካከል ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ አንዱ ናቸው፡፡
እንደ ፓርቲ አንድ አቋም እንይዛለን ግን ተግባራዊ አይደረግም፡፡ ሌላ ምሳሌ ልጨምርልህ፤ በጦርነቱ፣ በአዲስ አበባ፣ በባለፈው ምርጫ፣ በሀገራዊ ምክክር ጉዳዮች እና በለሌችም ጉዳይ እንደ ኢዜማ አቋም እንይዛለን፡፡ ነገር ግን የምንይዛቸውን አቋም የፓርቲው መሪ ይዞ ሊታገሉበት ሲገባ እየሸራረፈ ከብልፅግና ጋር እያስታከኩ መሄድ ነው የመረጡት፡፡ ይህንን ለማስቀረት በዙ ለፍተናል ግን የሚሆን ስላልሆ ጊዜ ከምንገል ብለን ነው ለመልቀቅ የወሰነው እንጂ መሰረታዊ ነገሮች ላይ ተመሳሳይ አቋም ነው የምንይዘው ግን የተያዘው አቋም አይተገበርም፡፡ ይህ መለያየትን ፈጠረ፡፡
ተጨማሪ ምሳሌ ልስጥህ፣ በትግራይ ጦርነት ኢዜማ አቋም ነበረው፡፡ ህወሓት መጥፋት አለበት የሚል ሀሳብ ነበር ሲንፀባረቅ የነበረው፤ ነገር ግን እኛ የሰላም አማራጭን መከተል ይሻላል የሚል አቋም ነበረን፡፡ ብልፅግን ሰላም ይውረድ ብሎ ሲነሳ በፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የሚመራው ቡድን ታጥፎ ሰላም! ሰላም! ማለት ጀመረ፤ ሸኔን (የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊትን) አጠፋለው ብሎ መንግስት ሲዘምት አዎ ሸኔ መጥፋት አለበት ተብሎ ነበር አቋም የተያዘው፡፡ ከዛ መንግስት ከሸኔ ጋር እደራደራለው ብሎ ሲል ኢዜማም አዎ የሚጠቅመው ድርድር ነው ማለት ጀመረ፡፡ ኢዜማ በየጊዜው የራሱ አቋም የሌለው፣ አቋም ብይዝም ብልፅግና አቋም በቀየረ ቁጥር ወደ ብልፀግና ለመጠጋት ጥረት የሚያደርግ ፓርቲ ነው፡፡ ስለዚህ እንደዚ አይነት ፓርቲ ላይ ስራህን ትተህ ገንዘብህን አውጥተህ በውስጥ መቆየት ተገቢ አይደለም፡፡
አዲስ ስታንዳርድ- እስካሁን ከኢዜማ ምን ያህል አባላቱ ለቀዋል ?
አቶ ሀብታሙ ኪታባ- ኢዜማን ስንመሰርተው የነበሩት አባላት እየለቀቁ አሁን ላይ በማዕከል ከሚንቀሳቀሱ የተወሰኑ ሰዎች በስተቀር እዚህ ግባ የሚባል አባላቶች የሉትም፡፡ ይህ በተጨባጭ ማረጋገጥ የምትችለው እውነታ ነው፡፡ ለምሳሌ እኔ ያለሁበት 12/13 የምርጫ ክልል ብትወስድ ስንጀምር ከነበሩ አባላት ውስጥ አሁን የቀሩን 10 በመቶ ቢሆኑ ነው፡፡ በአማራ ክልል ስንጀምር ካለው አባል አሁን የቀረው አባል 7 ወይ 8 በመቶ አይበልጥም፡፡ አሮሚያ ክልል ላይ ሁሉም መዋቅሮች ጠፍተዋል ማለት ይቻላል፡፡ አዲስ አበባ ላይ ካለው አጠቃላይ አባላት በአማካይ አሁን የቀረው ቢበዛ ከ 10 በመቶ አይበልጥም፡፡ የእኛ ብቻ ጎልቶ የወጣው በይፋ ለሚዲያ አሳውቀን መውጣታችን ነው እንጂ በርካታ አባላት ለቀዋል፡፡ በዚህ ልክ አባሉ የሚለቅበት ምክንያት ምንድነው ካልከኝ ከብልፅግና ጋር ያለው አካሄድ ላይ ነው፡፡ ድንገተኛ ጉባዔ ተጠርቶ ከብልፀግና ጋር እንስራ ተብሎ ተወሰነ፣ እኔ በበኩሌ ይህንን ተቃውሚያለው፡፡ በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል የፅሁፍ ስምምነት አልተደረገም፡፡ መጀመሪያ ላይ ብልፀግና ፅሁፍ ልኮ ነበር፤ አስታየት ሰጥተንበት ልከን ነገር ግን መልስ ሳይሰጠን ከፓርቲው መሪው ጋር እየተነጋገሩ መስራት ሲቀጥሉ አባሉ ጉባዔ ይጠራና ውሳኔው ዳግም ይታይ ብሎ ቢጠይቅም ተከልክለዋል፡፡ ይህን ጨምሮ በርካታ ምክንያቶች አባላቱ ለቀው እንዲወጡ አድርጓል፡፡
አዲስ ስታንዳርድ- የኢዜማ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ዶ/ር ሙሉአለም ከፓርቲው ከለቀቁት መካከል ገሚሶቹ የፓርቲውን ደንብና ሕግ ባለማክበራቸው የዲሲፒሊን ክስ ቀርቦባቸው ጉዳያቸው እየታየ ባለበት ወቅት ነው መልቀቃቸውን የሰማነው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ክስ ቅርቦባችሁ ነበር ? በዚህ ጉዳይ ላይ የእርስዎ ምላሽ መንድነው ?
አቶ ሀብታሙ ኪታባ- በዚህ ጉዳይ ላይ የኔ ምላሽ ምን መሰለህ፤ ቅድም የውስጥ ትግል ማድረግ የሚል ነጥብ አንስተህ ነበር፤ እኔ ለምሳሌ በወረዳዬ ላይ ሁለት ቀን ተሰብስበን የፖለቲካ አቋም ያዝን፤ ሌሎች ወረዳዎችም ስብሰባ አድርገው አቋም ይዘዋል፡፡ አንደኛው የያዝነው አቋም ጉባዔ ይጠራ የሚል ነው፣ ሌላኛው አቋም የፓርቲው መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ከፓርቲው አቋም በመውጣት ወደ አላስፈላጊ መንገድ እየሄዱ ነው የሚል ነው፣ በተጨማሪም በአዲስ አበባ ላይ በብልፅግና በሚያደርገው ጉዳይ ላይ እና ፓርቲው ከብልፅግና ጋር በሚሰራው ጉዳይ ላይ አቋም ይዘን ለማዕከል ላክን፡፡ ካዛ ያልተመቻቸውን ሰዎች አግደው መረጃ የሚያቀብሏቸውን ሰዎች ምንም ሳያደርጓቸው ተውዋቸው፡፡ መብታቸውን የጠየቁ ሰዎችን ግን አገዷቸው፡፡
ከተከሰሱት መካከል አንዱ እኔ ነኝ፡፡ የተከሰስኩት ወረዳዬ ላይ ስለሰራው፣ ከአባላት ጋር ተወያይቼ አቋም ስለያዝኩ ነው፡፡ ክሱን ያቀረበው ስራ አስፈፃሚው ነው፤ አጋጅ ኮሚቴ አዋቅሮ ነው ይህን ያደረገው፡፡ ይህ ደግሞ ከሕግ ውጬ ነው፡፡ መክሰስ የሚችለው የወረዳ ዲሲፒሊን ኮሚቴ ነው፣ ወረዳ ላይ ደግሞ እንዳይከሱ ወረዳዎች በፓርቲው አካሄድ ላይ የጋራ አቋም በመያዛቸው ስራ አስፈፃሚው የራሱን ኮሚቴ አዋቅሮ ማገድን ተያያዘው፡፡ ስለዚህ የዲሲፒሊን ክስ ቀርቦባቸዋል የሚሉት ከህግ ውጭ በሆነ እና አግባብነት በሌለው አካሄድ ነው ማለት ነው፡፡
ይህን ያደረጉት በፓርቲው ሕግ መሰረት ሳይሆን የፓርቲው መሪ የግል አቋማቸው ሕግ ስለሚመስላቸው ነው፡፡ አባላት አቋም ሲይዙ ይደነግጣሉ፣ ሕግ የተጣሰ ነው የሚመስላቸው፤ የቀረበብን ክስ በፓርቲው ሕግ መሰረት ክስ የሚያስመሰርት አይደለም፡፡ ይህንንም ለማረጋገጥ በፓርቲውን ሕግ መሰረት መከራከር እንችላለን፡፡ ነገር ግን እነሱ ፍቃደኛ አይሆኑም፡፡ ስለዚህ የተከሰስነው ከሕግ ውጭ በስራ አስፈፃሚ ድረጃ ኮሚቴ ተዋቅሮ ነው፡፡ በርካታ አባላት ሲለቁ ያጡትን የፖለቲካ ስም በሚዲያ ለማግኘት የደረጉት ተራ ጥረት ነው፡፡
“በኢዜማ ጉዳይ ላይ ብልፅግና ገብቶ ከፋፍሏል ብዬ አላምንም ምክንያቱም ኢዜማን እንደገደለው ያውቃል፡፡ ገዢው ፓርቲ መሪዎችን አቅርቦ ስርዓቱን በመምታት ማዳከም ላይ ሚና አለው እንጂ በኢዜማ ጉዳይ ላይ እጁን አስገብቷል የሚል ንባብ ግን የለኝም፡፡”
አዲስ ስታንዳርድ- ብልፅግና የፖለቲካ ፓርቲዎችን እና የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን በማዳከም ላይ ድርሻ አለው ? ለኢዜማ መከፋፈልስ የገዢው ፓርቲ አስተዋፅኦ ምን ድረስ ነው ?
አቶ ሀብታሙ ኪታባ- እውነት ለመናገር ከዚህ ቀደም ከነበረው ህወሓት መር ኢህአዲግ ወቅት አሁን በአንፃራዊነት ለፖለቲካ ፓርቲዎች የተሸለ ነገር አለ ብዬ አምናለው፡፡ በርግጥ የደህንነት መዋቅሩ እየተከታተል ጫና አያደርግም ማለት አልችልም፡፡ እኛ እየታገልነው ስላልሆነ አላየነውም ይሆናል ግን የባልደራስ ፓርቲ ሰዎች ሲታሰሩ ደግሞ እናያለን፡፡ በተጨባጭ ግን ኢዜማ ውስጥ እየተፈጠራ ላለው ነገር ቀጥተኛ የሆነ የብልፅግና እጅ አለበት ብዬ ማመን አልችልም፡፡ ነገር ግን ብልፅግና ውስጥ ያልሆኑ ልባቸው ግን በብልፅግና ሀሳብ የተወሰደ ሰዎች ኢዜማን እመሩት ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ነው እንጂ ኢዜማ ውስጥ በሆነው ነገር ላይ የብልፅግናን ተጠያቂነት ማምጣት በጣም ስህተት ነው የሚሆነው፡፡ ይህን ስልህ ብልፅግና ለመድብለ ፓርቲ ግንባታ እየሰራ ነው እያልኩህ አይደለም፡፡ በመድብለ ፓርቲ ስርዓት፣ በትክክል የሚታገሉ ፓርቲዎችን በተመለከተ ብልፅግና ከሌላው አገዛዝ የተለየ ነው ማለት አልችልም፡፡ ነገር ግን በኢዜማ ጉዳይ ላይ ብልፅግና ገብቶ ከፋፍሏል ብዬ አላምንም ምክንያቱም ኢዜማን እንደገደለው ያውቃል፡፡ ገዢው ፓርቲ መሪዎችን አቅርቦ ስርዓቱን በመምታት ማዳከም ላይ ሚና አለው እንጂ በኢዜማ ጉዳይ ላይ እጁን አስገብቷል የሚል ንባብ ግን የለኝም፡፡
“የኢዜማ መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የመንግስት መዋቅር ውስጥ መስራታቸው ለፓርቲው መስጠት ያለባቸውን ጊዜ እንዳይሰጡ አድርጓል፡፡“
አዲስ ስታንዳርድ- የኢዜማ መሪ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ ከብልፅግና ፓርቲ ጋር እየሰሩ ነው ብለውኛል፡፡ ኢዜማ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ጠንከር ያለ የመንግስትን አቋም የሚተች መግለጫ ሲያወጣ ይስተዋላል፡፡ ይህ ሆኖ ሳለ በምን መልኩ ነው የፓርቲው መሪ እና የእሳቸውን አቋም የሚደግፉት አካላት ከብልፅግና ጋር አየሰሩ ያሉት?
አቶ ሀብታሙ ኪታባ- አንድ ላይ እየሰሩ የተለያያ መግለጫ ማውጣት ያለ የተለመደ ነው፡፡ ለዚህ ምሳሌ የሚሆነው የአማራ ብልፅግና እና የኦሮሞ ብልፅግና የተለያያ ነገር ይፅፉ፡፡ የኢዜማ የመሪ በየመድረኩ የፓርቲያቸውን አቋም ይዘው ሲናገሩ ታይቶ አይታወቅም፡፡ ዶ/ር አብይ ግን ስለ ብልፅግና ፕሮግራም ሌትተቀን ይናገራሉ፡፡ ፖለቲካ ውስጥ ሀሳብህን ይዘህ ነው የምትታገለው፤ የኢዜማ መሪ ግን የፓርቲያቸውን አቋም ይዘው ሲታገሉ ሳይሆን ለብልፅግና ሽፋን ሲሰጡ ነው የሚውሉት፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ብልፅግና አቋም በቀያየረ ቁጥር ወዲያው ወደ ብልፀግና አቋም ይታጠፋሉ፡፡ ለመግለጫ ለመግለጫማ መንግታዊ የሆነው የኢትዮጵያ ሰብዓዎ መብቶች ኮሚሽንም የመንግስትን አሰራር በመቃወም መግለጫ እኮ ያወጣል፡፡ መታገል ያለብን መግለጫ በማውጣት ብቻ አይደለም መሆን ያለበት፡፡
ለምሳሌ በሰሜኑ ጦርነት ጊዜ የህወሓት ሀይሎች ወደ አዲስ አበባ እየቀረቡ ሲመጡ እኔ ያለሁበት የጥናት ኮሚቴ ተዋቀሮ አንድ ጥናት አጠናን፡፡ ጥናቱን የሰራነው ቁስለኞችን፣ በአማራ ክልል ያሉ ሰዎችን፣ በጦርነቱ ጊዜ ሲንቀሳቀሱ የነበር ጋዜጠኖችን እና ሌሎች አካላትን በማነጋገር ነበር፡፡ በጥናቱ ካገኘናቸው በርካታ ግኝቶች መካከል አንደኛው የአማራ ብልፅግና እና የኦሮሞ ብልፀግና በጦርነቱ ላይ ያለቸው የትርክት ልዩነት ህወሓትን እንደጠቀመው የሚያሳይ ነበር፡፡ የኦሮሞ ብልፅግና ሰዎች የአማራን ርስት ለማሰመለስ አንዋጋም ሲሉ የአማራ ብልፀግና ሰዎች ደግሞ የአማራን ርስት ለማስመለስ ነው የምንዋጋው ይላሉ፡፡ ይህ የትርክት ልዩነት ህወሓትን በእጅጉ ጠቅሞት ወደ አዲስ አበባ ተቃረበ፡፡ ይህን ጉዳይ ለህዝብ በማጋለጥ መታገል የፓርቲው መሪ ኃላፊነት ነው፡፡ ግን አላደረጉትም፡፡ በጥናት እንኳ የተረጋገጠ ነገር ሲቀርብ ደስተኛ አይሆኑም፡፡ ይህን ደግሞ የሚያደርጉት ከብልፀግና ጋር በመስራታቸው ነው፡፡
አዲስ ስታንዳርድ- የኢዜማ መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የመንግስት ካቢኔ መሆናቸው ፓርቲው ላይ በምን መልኩ ነው ተፅዕኖ ማድረግ የቻለው ?
አቶ ሀብታሙ ኪታባ- የታቃውሞ ፖለቲካና ሃሳብ ለማስፋት ትልቅ ስራን ይጠይቃል፡፡ ኢዜማ ቤት ያለው ስራ በራሱ ብዙ በመሆኑ ለስራው የሚሰጡትን ጊዜ አናሳ ያደርገዋል፡፡ ይህ እንደሚሆን አውቀን የትምህርት ሚኒስትር ሲሆኑ የፓርቲውን መሪነት ቦታ ልቁልን ስንላቸው አይሆንም ሁለቱንም ይዛለው አሉን፡፡ የኢዜማ መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የመንግስት መዋቅር ውስጥ መስራታቸው ለፓርቲው መስጠት ያለባቸውን ጊዜ እንዳይሰጡ አድርጓል፡፡ አሁን ኢዜማ ኦና ቤት ሆኗል፡፡ እናቱ ጎረቤት የሄደችበት ቤት ነው የሚመስለው፡፡
አዲስ ስታንዳርድ- ከኢዜማ በጋራ መልቀቃችሁ ፓርቲው ከብልፅግና ጋር ያለው ግኑኝነት ጭራሽ እንዲጠነክር አያመቻችም ?
አቶ ሀብታሙ ኪታባ- እውነት ለመናገር ቢያጠናክረውም ባያጠናክረውም ኢዜማ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ጠቃሚ ሆኖ ይቀጥላል ብዬ አላስብም፡፡ ኢዜማ ገዢውን ፓርቲ በተለየ ሁኔታ ማጠናከር የሚችልበት አቅም የለውም፤ በተለየ ሁኔታም ታግሎ መቀየር የሚችልበት አቅም የለውም፤ አቅሙን ጨርሷል ብዬ ነው የማምነው፡፡ ኢዜማን አሁን በታሪክ እንደሚታወሱት ከኢህአፓ፣ መኢሶን ተርታ እነደተሰለፈ ነው የምቆጥረው፡፡ በእኔ እምነት ኢዜማ ከሞተ ቆይቷል፣ ይህ ስብስብ ፓርቲውን ለቆ ሲወጣ ደግሞ የቀብር ስነስርዓቱ ተፈፅሟል፡፡ ስለዚህ ከቀብር ወጥቶ ብልፅግናን በተለየ ሁኔታ መገደፍ የሚችል፣ ታግሎም ደግሞ የተለየ ነገር መፍጠር የሚችል ፓረቲ እንዳልሆነ ውስጥ ያሉትም ያውቁታል፡፡ ነገር ግን ዋጋ የከፈልኩበት ፓርቲ እነደዚህ መሆኑ በጣም ነው የሚያሳዝነኝ፡፡
አዲስ ስታንዳርድ- በተደጋጋሚ የፓርቲ አባሎች ከፖለቲካ ፓርቲ ለቀው ሲወጡ ዜጎች ለፓርቲ ላይ የሚኖራቸው እምነት እንዲጠፋ አያደርግም ?
አቶ ሀብታሙ ኪታባ- ያደርጋል፡፡ ከዚህ ቀደም የተለያዩ ፓርቲዎች ከስመዋል፡፡ ኢዜማ ሲመሰረት ይህንንም ለመቀየር ታስቦ ነበር፡፡ የአባላት ከፖለቲካ ፓርቲ መልቀቅ ተፅዕኖ እንዳለው አውቃለው፣ ግን ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲ ኖረም አልኖረም የኢትዮጵያ ህዝብ በራሱ ታግሎ አገዛዙን መገልበጥ ይችላል፡፡ ይህ ከታሪክ የምናየው ነው፡፡ ከተደራጀው ሀይል ይልቅ የህዝብ እንቅስቃሴ ነው ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ለውጥ የማምጣት ባህል ያለው፡፡ የቅርብ ጊዜውን ብናይ የቄሮ እና የፋኖ ነው እንጂ የትኛው የፖለቲካ ድርጅት ነው ለውጥ ያመጣው ? በእርግጥ አባሎች ከፖለቲካ ፓርቲ ለቀው መውጣቱ ተፅዕኖ ስለሚኖረው ባይሆን ጥሩ ነው፤ ነገር ግን በተለይ በአሁኑ ወቅት ህዝቡ በራሱ ተደራጅቶ ከመታገል ውጭ አማራጭ አለው ብዬ አላምንም ፡፡
አዲስ ስታንዳርድ- በእርስዎ ግምገማ የሀገሪቷ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ምን ይመስላል ? አሁን ካለንበት የፖለቲካ ቀውስ ለመውጣትስ የተሻለ የሚልት የመፍትሄ መንገድ ምንድነው ?
አቶ ሀብታሙ ኪታባ- የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስብስብ ተደርጎ ይቆጠራል፤እኔ በግሌ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስብስብ ነው ብዬ አላምንም፤ ነገር ግን የተያዘበት መንገድ ልክ አይደለም ብዬ ግን አምናለሁ፡፡ የፖለቲካ ሀይሎች ቁጭ ብለው የመነጋገር በህል የለንም፡፡ ስለዚህ መፍትሄው ቁጭ ብሎ በሰከነ መንፈስ መነጋገር ነው፡፡ የአንድ ፓርቲ መሪ መድረክ ላይ ቁጭ ብሎ ሌላው ፓርቲ እንደ ተሰብሳቢ እየቆጠረ ሳይሆን ታች ወርዶ እኩል ተቀምጠው ሲወያዩ ነው፡፡ ብልፅግናም አንድ ወንበር፣ እያንዳንዱ የፖለቲካ ሀይል አንዳንድ ወንበር ይዞ ቁጭ ብሎ ወዴት እንዲሂድ የሚለው ላይ እውነተኛ ውይይት ሀገሪቱ ትፈልጋለች ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህ ቢደረግ ኖሮ ከፍትህ እና ከእኩልነት ውጭ አብሮ ያኖረናል ብሎ የሚያስብ ሀይል አለ ብዬ አላምንም፡፡ መድረኩ ስለጠፋ ሰው በየራሱ መንገድ ይዋትታል እንጂ ቁጭ ብሎ በመነጋገር የአገሪቷ ችግር ይፈታል ብዬ አምናለሁ፡፡ አሁን አገሪቷ ላይ ያለው አለመረጋጋት ምንጭ ገዢው ፓርቲ ቁጭ ብሎ እኩል መነጋገረን አለመፍቀድ ነው እንዲሁም ኢትዮጵያን በሚፈልጋት መልክ ለመቅረፅ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ውጤት ነው ብዬ ነው የማምነው፡፡ ስለዚህ መፍትሄ ሚሆነው ሁሉም አካል እኩል እድል ተሰጥቷቸው መነጋገር ነው፡፡
” የብሔር ፖለቲካ ውስጥ መግባት ብንፈልግ ውይይት ማድረግም አይጠበቅብንም ነበር፤ ብዙ የብሔር ፖለቲካ ድርጅቶች አሉ አንዱን መቀላቀል ይቻል ነበር፡፡ እኔ ብቻ ሳልሆን አሁን አብረውኝ ያሉ ጓደኞቼም በብሔር ፖለቲካ መንገድ ይሄዳሉ የሚል እምነት የለኝም፡፡ “
አዲስ ስታንዳርድ- በርካታ ፓርቲዎች ገዢውን ፓርቲ ለመገዳዳር የሚረዳቸው ሃሳብ ይዘው ሲመጡ በስፋት አይታይም፤በስፋት ይዘው የሚመጡት የተቃውሞ ሀሳብ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከተቃውሞ ፖለቲካ ወደ ፉክክር ፖለቲካ ደርጃ አድጓል ብለው ያስባሉ?
አቶ ሀብታሙ ኪታባ- ብልፅግናዎች ወደ ፖለቲካ ፉክክር አድገናል ብልን እንዳሰብን አደርገው ይቆጥራሉ ነገር ግን እኔ አላስብም፡፡ ምክንያቴን ልንገርህ፤ ፉክክር እኩል መድረክ ላይ ነው የምትፎካከረው፡፡ የጠቅላይ ሚንስትሩ መደመር የሚል የፖለቲካ አስተሳሰብ መፅሓፍ በመንግስት ሚዲያ እየተቸበቸበ ሌላው ደግሞ ጉባዔ እንኳን እንዳያደርጉ እየተከለከሉ ፖለቲካው ፉክክር ሊሆን አይችልም፡፡ እኔ ተፎካካሪ የሚለውን ቃል አልጠቀምበትም እኔ ተቃዋሚ ነኝ፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ፉክክር የሚባል ነገር የለም፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በተቃውሞ ጎራ ያሉት ሃሳብን ቀምሮ በማቅረብ ረገድ የገዢው ስብስብ ቀድሞ አያውቅም፤ የፖለቲካዊ ሃሳብ ፅሑፍ ይዞ በመቅረብ በሰላማዊ ትግል የሚያምኑ ፓርቲዎችን የሚያክል የለም፡፡ ሃሳብ ያስፈልጋል፣ ተቃውሞ ያስፈልጋል፤ ለምሳሌ እኔ በኢኮኖሚ ላይ ክርክር ሳደርግ እኛ ከተመረጥን በሶስት እና አምስት አመታት መካከል መሰራታዊ ፍልጎትን እናሟላለን፣ ስንዴ እናመርታለን፣ በስንዴ እራሳችንን እንችላለን ስንል በተለያዩ አለም ያሉ ምሁራንን አሳትፈን ያጠናነውን ጥናት መሰረት አድርገን ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በቤት ጉዳይ ላይ፣ በከተማ ግንባታ ላይ፣ ህዝቡን ሳያማርር ስማርት ከተሞችን መገንባት ላይ ሃሳብ አቅርበን ክርክር አድርገናል፡፡ ፓርቲዎች ሀሳብ አላቸው፡፡ ስለዚህ ገዢው ፓርቲ ሜዳውን ሚዛናዊ ካላደረገ፣ ለህግ ካልተገዛ የፉክክር ፖለቲካ ሊኖር አይችልም፡፡
አዲስ ስታንዳርድ- በቀጣይ ምን አስባችኋል? አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ ለማቋቋም እቅዱ አላችሁ?
አቶ ሀብታሙ ኪታባ- አሁን ማድረግ የምንፈልገው ውይይት ነው፤ አንደኛ ከኢዜማ ውድቀት ምን ተማርን የሚለው ላይ ውይይት መድረግ እንፈልጋለን፡፡ ሁለተኛ ደግሞ የብሄር ፖለቲካው ካምፕ እና እኛ የምናስብበት ካምፕ ላይ ውይይት ማድረግ ነው፡፡ በዳያስፖራው ሚና ላይ እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ውይይት እናደርጋለን፡፡ ውይይት ካደረግን በኋላ ከውይይቱ ከምንማራቸው ነገሮች የተቀናጀ ሀሳብ ይዘን ወደ መተግበር እንገባለን፡፡ ወደ ተግባር ስንገባ በምን መንገድ ነው የሚለውን ገና የሚወሰን ይሆናል፡፡ በሚድያ ላይ ምስራት ነው የሚያስፈልገን የሚል ከወሰንን ወደ ሚዲያ ልንመጣ እንችላለን፣ ወይ ውሳኔው የሚያስፈልገን የዓብዓዊ መብቶች እንቅስቃሴ ነው የሚል ከሆን ወደዛ እንገባለን፣ የለም የሚያስፈልገው የፖለቲካ ነው የሚል ከሆነ ወደ ፖለቲካ ፓርቲ እንመለሳለን፣ አይ የሚያስፈልገው ሁሉንም ትተን መፀለይ ነው የሚል ከሆነ በየእምነታችን ለሀገራችን እንፀልያለን፡፡ ስለዚህ ቀጣይ መንገዳችንን የምንመርጠው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ውይይት ካደረግን በኋላ ነው፡፡ ይህንን የወሰነው በየትኛው መንገድ ብንሄድ ለሀገራችን እንጠቅማታለን የሚለው ላይ በደንብ ለማሰብ ነው፡፡
አዲስ ስታንዳርድ- ውይይቱን የምታደርጉት ከኢዜማ የለቃቀቃችሁ ሰዎች ብቻ ናችሁ ወይስ ሌሎች አካላትም ይሳተፋሉ?
አቶ ሀብታሙ ኪታባ- ውይይታችሁ ላይ መሳተፍ ፈልጋለው የሚሉ ሰዎችን እንጋብዛለን፡፡ መወያየት ለሚፈልጉ ሰዎች ክፍት የሚሆኑ ውይይቶች ይኖራሉ፤ ምናልባት ኢዜማን በምንገመግምብበት ውይይት ላይ ኢዜማ ውስጥ የነበሩ ሰዎች ብቻ ሊሆኑ ይችላሉ የሚሳተፉት፡፡
አዲስ ስታንዳርድ- ምናልባት በቀጣይ በብሔር ፖለቲካ ለመምጣት ሀሳብ ይኖርዎት ይሆን ?
አቶ ሀብታሙ ኪታባ- እሱ የማይታሰብ ነው፤ የብሔር ፖለቲካ ውስጥ መግባት ብንፈልግ ውይይት ማድረግም አይጠበቅብንም ነበር፤ ብዙ የብሔር ፖለቲካ ድርጅቶች አሉ አንዱን መቀላቀል ይቻል ነበር፡፡ እኔ ብቻ ሳልሆን አሁን አብረውኝ ያሉ ጓደኞቼም በብሔር ፖለቲካ መንገድ ይሄዳሉ የሚል እምነት የለኝም፡፡ የኔ አቋም ግልፅ ነው ይህን ስልህ የብሄር ፖለቲካን የማይበት ዕይታ በአንድ ቋት አትጨምራቸው፤ እያንዳንዱ ብሔርተኝነት ጀርባ የተለያዩ ነገሮች ስላሉ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ሁሉንም የማይበት መንገድ የተለያያ ቢሆንም በተሸለ ምንገድ ይሄኛው አለ ብዬ የምቀላቀለው የብሔር ፖለቲካ ፓርቲ ግን የለም፡፡
አዲስ ስታንዳርድ- አቶ ሀብታሙ ውድ ጊዜዎትን ሰውተው ለጥያቄዎቻችን ምላሽና ማብራሪያ ስለሰጡን በአንባዎዎቻችን ስል እናመሰግንዎታለን፡፡
አቶ ሀብታሙ ኪታባ- እኔም አመሰግናለው፡፡ አስ
የአርታዒ ማስታወሻ፡- በዚህ ቃለ መጠየቅ ውስጥ የተነሱት ሀሳቦች የግለሰቡን እንጂ የአዲስ ስታንዳርድን አቋም አይወክሉም፡፡