ርዕሰ አንቀፅ፡ ኦሮሚያ ዉስጥ ያለው አውዳሚ ጦርነት እንዲቆም የህዝብ ተወካዮች ያቀረቡትን ጥሪ እንደግፋለን

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 14/ 2015 ዓ.ም፡- በኦሮሚያ ክልል ያለው የጸጥታ ሁኔታ በኢትዮጵያ ውስጥ በቅርቡ እየተከሰቱ ያሉትን ሁኔታዎች በቅርበት የሚከታተሉ የሀገር ውስጥ እና የውጭ አካላት ትኩረትን ይፈልጋል። ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ የዜጎች ደህንነትና የፀጥታ ሁኔታ እየከፋ መጥቷል፣ በርካታ የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው አካላት በትጥቅ ትግል ፍላጎታቸዉን ለማሳካት ከመንቀሳቀሳቸው የተነሳ በክልሉ ያለውን የብሄረሰቦች በሰላማዊ መንገድ አብሮ የመኖር እሴታቸው ፈራርሷል፡፡

በተለያዩ ብሔሮች መካከል ያለው የረጅም ጊዜ መቀራረብ፣ ማህበራዊ ስምምነት እና አንድነት አሁን ወደ ትርምስ ተቀይሯል። በምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ እና ጊዳ አያና ወረዳዎች በቅርቡ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ከተፈፀመው አሰቃቂ ግድያ ጀምሮ በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ ሆነ ተብሎ ከ200 በላይ ሰላማዊ ዜጎች ላይ የተፈፀመውን ግድያ እና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መፈናቀላቸው እንዲሁም የመንግሥት መሰረተ ልማቶች እና የሲቪል ሰዎች ንብረቶች መዘረፍና መውደም “እጅግ ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት” (grave violation of human rights) ማሳያ ተብሎ ሊመደብ የሚችል መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብተች ኮሚሽን ገልጧል፡፡

በኢሰመኮ ሪፖርት ላይ የተገለፀው አሰቃቂ ሁኔታዎች የሚፈፀሙት በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች፣ በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አማፂያን፣ በአጎራባች የአማራ ክልል ታጣቂ ቡድኖች እና መንግስት ባስታጠቃቸው የአካባቢው ዜጎችን ጨምር ነው። ይህ በራሱ የችግሩን ውስብስብነት ይጠቁማል።

ምንም እንኳ በሪፖርቱ የተገለፀው የጅምላ ግድያ የለፉት ስድስት ወራት ዝርዝር ጉዳዮችን ብቻ የሚያሳይ ቢሆንም፣ የዚህ ቀውስ ጅማሮ ግና ከአራት ዓመታት በፊት የነበረው የፖለቲካ ውድቀት እና የማጭበርበር ውጤት ነው። ይህም ተግባር ሃይ ባይ በማጣቱ በስተመጨረሻም ወደ ሀገር ደረጃ አድጓል፤ እንዲሁም ክልሉን ወደ ሙሉ የወንጀል ስፍራነት ቀይሮታል።

ይህ ቀውስ  ከፖለቲካ ውድቀት በላይ፣ የሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት መፍረስ ችግርን ያሳያል፡፡ የአማራ ክልል ታጣቂዎች እና መደበኛ ያልሆኑ የፋኖ ታጣቂ አባላት ወደ ኦሮሚያ ድንበር ተሻግረው በትጥቅ ትግል መሳተፍ በገዥው ፓርቲ ቸልተኝነት ተባብሶ የስልጣን ምሶሶ የሆኑትን ህገ መንግሥታዊ ሥርዓትን እና ሉዓላዊነትን የከፋ ችግር ዉስጥ እንዲወድቁ አድርጓል። ይህ ሁኔታ የክልል እና የፌደራል መንግስታቱ ህገ መንግስታዊ ተግባራቸውን በአግባቡ አለመወጣታቸውን ብቻ ሳይሆን የዜጎችን ህይወት እንዴት መጠበቅ እንዳቃታቸውም ግልጽ አድርጓል።

ሆኖም ቀውሱ እየተባባሰ በመጣበት ወቅት የፌደራል መንግስትም ሆነ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ሁኔታውን በሰላማዊ መንገድ  እልባት ለመስጠት ፈቃደኛ አይደሉም። ይልቁንም ከኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ጋር ለመታገል ወታደራዊ ሃይልን መጠቀም ብቸኛው መንገድ እንደሆነ በይፋ አስታውቀዋል።

በዚህ አካሄድ ላይ የተጋረጡ በርካታ ችግሮች ቢኖሩም ሁለቱ ጎልተው ታይተዋል፡፡ የመጀመሪያው ኢትዮጵያን እየመሩ ያሉ ፖለቲከኞች ለበርካታ ጊዜያት የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊትን ለማጥፋት የገቡትን ቃል መፈፀም ካልቻሉበት ካለፉት አራት አመታት ተሞክሯቸው ምንም ያልተማሩ መሆኑ ነው፡፡

ሁለተኛው ደግሞ በትግራይ ተጀምሮ ወደ አማራና አፋር ክልል የተስፋፋውና ለሁለት አመታት የዘለቀውን አውዳሚ ጦርነት ለመቋጨት ከትግራይ ባለስልጣናት ጋር ከተፈራረሙት የሰላም ስምምነት ልምድ አለመውሰዳቸው ነው፡፡

በኢትዮጵያ መንግስት እና በትግራይ ባለስልጣናት መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት ሊደናቀፍ የሚችል መሆኑ ብዙ አመላካች ነገሮች ቢኖሩም ርምጃው የሀገሪቱን ሰላምና መረጋጋትን በማረጋገጥ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረዉ የማይካድ ሀቅ ነው። በኦሮሚያ ክልል ያለውም ጦሪነት ከዚህ ያነሰ ትኩረት የሚሻ አይደለም፡፡

ከኦሮሚያ ክልል የተመረጡ የኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በታህሳስ ወር አጋማሽ ላይ በሀገሪቱ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ የሚበረታታ ተግባር አድርገዋል። በኦሮሚያ ክልል ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ለፓርላማ አፈ ጉባኤ እና ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እንዲሁም ለተለያዩ የፓርላማ ቋሚ ኮሚቴዎች ደብዳቤ አቅርበዋል። ደብዳቤያቸው አስር ነጥቦችን የያዘ ሲሆን አንደኛው በትግራይ እንደተደረገው የሰላም ሂደት በኦሮሚያ ክልልም እንዲደረግ የሚጠይቅ ነው።

በኦሮሚያ የተከሰተውን ቀውስ እየዘገበ እንዳለ ሚዲያ እና በሰው ልጆች ላይ እየደረሰ ያለውን አስከፊ ግድያዎችን እንደሚዘግብ ሚዲያ፣ ይህ እትም የፓርላማ አባላቱን ጥያቄ በጥብቅ በመደገፍ ሌሎችም እንዲቀላቀሉ ጥሪ ያቀርባል።

የኢትዮጵያን ፖለቲካ የሚከታተሉ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ አባላት፣ የሀገር ውስጥ ሲቪክ ማህበራት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የመገናኛ ብዙኃን እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እና በኦሮሚያ ለተፈጠረው ችግር በቅርቡ ወታደራዊ እልባት እንደሚሰጥ የሚያምኑ ሰዎች ይህን የተዛባ አመለካከት በማስወገድ ከነዚህ የፓርላማ አባላት ጋር በመተባበር ይህ አሳዛኝ ሁኔታ በፖለቲካዊ ድርድር እንዲያበቃ መጠየቅ አለባቸው።

ማንም ሰው እንዲሁ ሰላም ሊያገኝ አይችልም፣ በፕሮፓጋንዳም ሰላም ሊገኝ አይችልም፣ ሰላም ተጨባጭ ቁርጠኝነትን፣ ጥረትን እና መስዋዕትነትን ይጠይቃል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.