ዜና፡ በአዲስ አበባ ለሶስት ቀን ሞተር ብስክሌት ማሽከርከር እንደማይቻል ተገለጸ፣ የሚዘጉ መንገዶችም ይፋ ሆነዋል

የአዲስ አበባ ከተማ ሞተረኞች፤ ምስል ዋልታ ቲቪ

አዲስአበባ፣መስከረም 20/2015ዓ.ም፡-በአዲስ አበባ በነገው እለት የሚከበረው የእሬቻ በአል ምክንያት በማድረግ ከዛሬ ጀምሮ እስከ እሁድ ድረስ ሞተር ብስክሌት ማሽከርከር እንደማይቻል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራፊክ ማኔጅመት ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

በነገው እለት መስከረም 21፣ 2015 ዓ.ም. ለሚከበረው የኢሬቻ በዓል በሁሉም የመዲናዋ በሮች የሚገቡ የበዓሉ ታዳሚዎች ስለሚኖሩ ከበዓሉ ዋዜማ ጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ድረስ የሞተር ብስክሌት እንቅስቃሴን መገደብ አስፈልጓል ሲል ኤጀንሲው አስታውቋል።

በዚሁ መሠረት ከዛሬ አርብ መስከረም 20 ቀን 2015 ዓ.ም ከንጋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ እስከ እሁድ መስከረም 22 ቀን 2015 ዓ.ም ማታ 12 ሰዓት ድረስ የሞተር እንቅስቃሴ በከተማዋ የተከለከለ መሆኑን ተገንዝባችሁ ተገቢውን ጥንቃቄ እንድታደርጉ ሲል ኤጀንሲው አክሎ አሳስቧል፡፡

ኤጀንሲው የተጣለውን ገደብ ተላልፈው በሚገኙ ሞተረኞች ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ አሳስበዋል፡፡

ይህ እንዲህ አንዳለ ከዛሬ ዓርብ መስከረም 20 ቀን 2015 ዓ.ም ከቀኑ 6፡00 ሰዓት ጀምሮ የኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ በዓል ተከብሮ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ዝግ የሚሆኑ መንገዶችን የአዲስ አበባ ፖሊስ ይፋ አድርጓል።

ከቦሌ አየር መንገድ በሚሊኒዬም አዳራሽ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ወሎ ሰፈር አደባባይ
•ከመገናኛ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ 22 ማዞሪያ
• ከ4ኪሎ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ኮንሰን መስቀለኛ ወይም ወዳጅነት ፓርክ
•ከፒያሳ በቸርቸር ጎዳና ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ቴዎድሮስ አደባባይ
•ከጦር ሃይሎች በለገሃር ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት
•ከጀሞ በትንባሆ ሞኖፖል ወደ ሜክሲኮ የሚወስደው መንገድ አፍሪካ ህብረት አደባባይ
•ከቄራ ወደ ሜክሲኮ አደባባይ የሚሄደው መንገድ ቡልጋርያ ማዞሪያ
•በአዲሱ መንገድ ከቄራ በቂርቆስ ወደ ለገሃር የሚወስደው መንገድ ታቦት ማደሪያ
•ከሳሪስ ፣ በጎተራ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ጎተራ ማሳለጫ
•ከቦሌ ወደ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን የሚወስደው መንገድ አትላስ ሆቴል አካባቢ
•ከአዋሬ ወደ ካሳንቺዝ የሚወስደው መንገድ ሴቶች አደባባይ
•ከልደታ በጌጃ ሰፈር ፣ ጤና ጥበቃ የሚወስደው መንገድ አብነት ፈረሰኛ ፖሊስ አካባቢ
•ከመርካቶ በጎማ ተራ ወደ አምስተኛ የሚወስደው መንገድ በርበሬ በረንዳ
•ከመርካቶ በራስ ቴአትር ወደ ጎማ ቁጠባ ተክለ ሃይማኖት አደባባይ ያሉት መንገዶች ዝግ እንደሚሆኑ ተገልጧል፡፡


በዓሉ በሚከበርበት ዙሪያ እና በአካባቢው በግራና በቀኝ ለረጅም ሆነ ለአጭር ጊዜ ተሽከርካሪ አቁሞ መሄድ ፍፁም የተከለከለ መሆኑን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡ አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.