ዜና፡ ባሕርዳር፣ ጎንደርና ላሊበላን ጨምሮ በስድስት ከተሞች የሕዝብ የአገልግሎት ሰጪ፣ የመንግሥት፣ የማኅበረሰብና የንግድ ተቋማት ከነገ ጀምሮ አገልግሎት እንዲሰጡ ታዘዘ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 3/ 2015 ዓ.ም፡- የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ በባሕርዳር፣ ጎንደር፣ ደብረ ብርሃን፣ ደብረ ማርቆስ፣ ሸዋ ሮቢትና ላሊበላ የሕዝብ የአገልግሎት ሰጪ፣ የመንግሥት፣ የማኅበረሰብና የንግድ ተቋማት ከነገ ነሐሴ 4/2015 ጀምሮ ክፍት እንዲሆኑ አዘዘ።

የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ የተለያዩ ትዕዛዝችና ክልከላዎችን ደንግጓል፡፡ ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ ትዕዛዞችና ክልከላዎች  የደነገገው የሕዝብን ሠላምና ደህንነት ለማስጠበቅ የወጣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 6 /2015 አንቀጽ 5 መሰረት መሆኑን ዛሬ ነሃሴ 3 ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

በዚህም መሰረት በባሕርዳር፣ ጎንደር፣ ደብረ ብርሃን፣ ደብረ ማርቆስ፣ ሸዋ ሮቢትና ላሊበላ ከተሞች እስከ ነሐሴ 17፣ 2015 የሚቆይ የሠዓት እላፊ ገደብ ተጥሏል ብሏል፡፡ ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት ከሚሰጡ ተሽከርካሪዎች፣ የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት ሰጪ ባለሞያዎች እና የፀጥታ አስከባሪ ተቋማት ባልደረቦች ውጪ ለማንኛውም ሰው እና ተሽከርካሪ ከምሽቱ አንድ ሰዓት በኋላ መንቀሳቀስ በጥብቅ የተከለከለ ነው ሲል አስጠንቅቋል።

በከተሞቹ የባጃጅ እና የሞተር ሳይክል እስከ ነሐሴ 17፣2015 ድረስ እንዳይንቀሳቀሱ ክልከላ የተጣለባቸው ሲሆን ሌሎች የከተማ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ከነሐሴ 4 ጀምሮ ወደ ሥራ የመመለስ እና አገልግሎት የመስጠት ግዴታ አለባቸው ሲል አዟል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ ከፈቃድ ውጪ በአማራ ብሔራዊ ክልል ከተሞች የአደባባይ ስብሰባ፣ ሰልፍ እና መሰል እንቅስቃሴዎችን ማድረግ እንዲሁም በማንኛውም መልኩ የህዝብ እንቅስቃሴን የሚያስተጓጉል እና የትራንስፖርት አገልግሎትን የሚያሰናክል ድርጊት በጥብቅ የተከለከለ መሆኑን ገልጧል።

በተጨማሪም በአማራ ብሔራዊ ክልል ውስጥ ለጸጥታ ሥራ ከሚንቀሳቀሱ የህግ አስከባሪ አካላት እና ከነዚህ አካላት ፈቃድ ውጭ የጦር መሣሪያ ይዞ መዘዋወር ፈጽሞ የተከለከለ ነው ተብሏል።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሽፋን ከአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ትእዛዝ ውጭ ወቅታዊ ሁኔታን ሰበብ በማድረግ ግለሰቦችን ከመደበኛው ህግ አግባብ ውጪ ማሰር እና ማቆየት፣ የንግድ ቤቶችን ማሸግ እና መሰል እርምጃዎችን መውሰድ በጥብቅ የተከለከለ መሆኑ በመግለጫው ተገልጧል።

የተዘረዘሩትን ትዕዛዞችና ክልከላዎችን በሚጥሱ ላይ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አንቀጽ 7 መሰረት ሃይልን በመጠቀም፣ እንዲሁም ሌሎች አግባብነት ያላቸውን እርምጃዎችን በመውሰድ ትዕዛዝና ክልከላዎችን እንዲያስፈጽሙ ለሁሉም የህግ አስከባሪ አካላት ጥብቅ መመሪያ ተሰጥቷል።

የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ በመግለጫው በስድስቱ ከተሞች ዙሪያ የመጣው “የጥፋት ቡድን” መሣሪያውን እንዲያስረክብና እጁን እንዲሰጥ የተሰጠውን ዕድል ባለመጠቀሙ እርምጃ ተወስዶበታል፣ የሕግ የበላይነትም እንዲከበር ተደርጓል ብሏል። በአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የጠቅላይ መምሪያ ዕዙ እስካሁን 14 ተጠርጣሪዎችን በአዲስ አበባ ከተማ በቁጥጥር ሥር ማዋሉንም አስታውቋል፡፡

“በአሁኑ ሰዓት ከተሞቹ ከዘረፊዉ መንጋ ስጋት ነጻ ሆነዋል” ያለው መግለጫው የመከላከያ ሠራዊቱ እና የክልሉ ህግ አስከባሪ አካላት በየሥርቻው የተራረፈውን ዘራፊ በማጽዳት ላይ ናቸው ሲል ገልፆ ቡድኑ በአንዳንድ አካባቢዎች ወደ ቅርስ ቦታዎችና የእምነት ተቋማት በመግባት ለመደበቅ እየሞከረ ነው ብሏል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.