ዜና፡ የአሜሪካ ኤምባሲ ዲፕሎማቶች በደቡብ ትግራይ ያካሄዱትን ጉብኝት አቶ ጌታቸው ረዳ አወገዙ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16/2015 ዓ.ም፡- የትግራይ ክልል ግዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ የአሜሪካን ኤምባሲ ዲፕሎማቶች በደቡብ ራያ አላማጣ ከተማ ያካሄዱትን ጉብኝት አወገዙ። በደቡብ ትግራይ ከሚገኙት አከባቢዎች መካከል በአማራ ክልል ሀይሎች ቁጥጥር ስር የምትገኘው አላማጣ ከተማ ከትላንት በስቲያ የአሜሪካ ዲፕሎማቶችን ጉብኝት አስተናግዳለች።

ዲፕሎማቶቹ ከከተማዋ አስተዳደር ጋር መገናኘታቸውን የሚያሳዩ የአከባቢውን ባህላዊ አልባሳት ለብሰው የተነሱት ፎቶ በማህበራዊ ሚሰዲያ በስፋት በመሰራጨት ላይ ይገኛል። የአሜሪካን ኤምባሲ የዲፕሎማቶቹን ጉብኝት አስመልክቶ የሰጠው ይፋዊ ማብራሪያ የለም። በርካታ የትግራይ ተወላጆች የዲፕሎማቶቹን ጉብኝት በመቃወም በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስተያየታቸውን አስፍረዋል።

ጉዳዩን በተመለከተ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በማህበራዊ ሚዲያ የትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ “የአማራ ኃይሎች በሕገወጥ መንገድ በኃይል የያዙትን አካባቢ ዲፕሎማቶቹ መጎብኘታቸው የትግራይ ግዛቶች በጽንፈኛ ኃይሎች የኃይል ቁጥጥር ስር መኾኑን እንደመቀበል ይቆጠራል ብለዋል። ዲፕሎማቶቹ የአካባቢዎቹ ሕገወጥ አስተዳደር ባላሥልጣናት ባቀነባበሩት ድራማ ለምን እንደተሳተፉ ግልጽ አይደለም ሲሉ ገልጸው ድርጊቱ አሜሪካ ለፕሪቶሪያው ግጭት ማቆም ስምምነት ያላትን ቁርጠኝነት የሚጻረርና ተቀባይነት የሌለው ነው” ብለዋል።

በክልሉ የሚንቀሳቀሰው ሳልሳይ ወያነ ፓርቲ የውጭ ግንኙነት ክፍል ሃላፊ ሃይሉ ከበደ በበኩላቸው የዘር ማጽዳት ተግባር በፈጸሙና አከባቢውን በጉልበት በተቆጣጠሩ ሃይሎች ግብዣ በአከባቢው የሚደረግ ማንኛውም ይፋዊ ጉብኝት ተቀባይነት የለውም፣ አደገኛ ተግባርም ነው ሲሉ ገልጸዋል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.