ፈጠራ፡ የኢትዮጵያን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እሴትን ያዘመነው፣ ዲጂታል ዕቁብ

ምስል- ዲጂታል ዕቁብ

በብሩክ አለሙ @Birukalemu21

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 26/ 2015 ዓ.ም፡- ኢትዮጵያ ካሏት እሴቶች አንዱ እቁብ ነው፡፡ ዕቁብ ሰዎች ተሰባበስው ገንዘባቸውን የሚቆጥቡበት አማራጭ ሲሆን ይህ አሰራር በኢጥዮጵያ ውስጥ ለዘመናት ሲተገበር የቆየ አሰራር ነው፡፡

በባህላዊ መልክ ሲደረግ የነበረውን ዕቁብ ለማዘመንና አሰራሩን በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ በማሰብ በ2013 ዓ.ም. ነበር በአራት ባለአክሲዮኖች “ዲጂታል እቁብ”ን የመሰረቱት፡፡  ባህላዊውን ዕቁብ አሰባሰብ በቴክኖሎጂ እንዲደገፍ መተግበሪያ በማበልፀግ ወደ ስራ ገብቷል፡፡ ቴክኖሎጂው በባህላዊ መንገድ ሲተገበር ለነበረው የዕቁብ አጣጥል፣ መተግበሪያን በመጠቀም ቦታ ሳይገድበው እና  ከንክኪ ነፃ ሆኖ  መጣል የሚያስችል  የዲጂታል አሰራር ነው፡፡

የዲጅታል ዕቁብ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ብስራት ፍቅሩ በባህላዊው ዕቁብ ገንዘብ የሚሰበሰበው እጅ በእጅ በመሆኑ ለአደጋ ስለሚጋለጥ እና ዕቁብ ለመግባት የሚፈልግ ሰው  የሚያውቃቸውን ሰዎች ስለሚያስፈልገው ይህንን ችግር ለመቅረፍ ዲጂታል ዕቁብ ተግባራዊ ማድረግ እንዳስፈለገ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል፡፡ 

አቶ ብስራት አያይዘውም የዲጂታል ዕቁብ አባላት (ዕቁብተኛ) በአካል መገኘት ሳይጠበቅባቸው ካሉበት ሆነው በሞባይል ባንኪንግ በመጠቀም መዋጮውን በመክፈል መጠቀም የሚችሉ ሲሆን የእጣው መውጫ ቀንም የእጣ አወጣጡን ሁሉም ዕቁብተኛ ካለበት ቦታ ሆኖ በየዲጂታል ዕቁብ መተግበሪያው በቀጥታ መከታተል ይችላል ብለዋል፡፡

ሰዎች ቦታ ሳይወስናቸው አቅማቸው በማገናዘብ በፈለጉት የገንዘብ መጠን መርጠው ዕቁብ መጣል እንደሚችሉ የገለፀው አቶ ብስራት እንድ እቁተኛ በአካል መገኝት የሚጠበቅበት እጣ የወጣለት እለት ብቻ እንደሆነና እንደ እቁቡ ገንዘብ መጠን ከ2 እስከ 3.85 በመቶ የአገልግሎት ክፍያ እንዲከፍል ይደረጋል ሲል ተናግሯል፡፡

የመንግስትና የግል ድርጅት ሰራተኞች በየወሩ ከ አንደ ሺህ እስከ 10 ሺህ ብር፣ ሾፌሮች በቀን ከ 300 እስከ 1000 ብር፣ በንግድ ስራ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ደግሞ በቀን ከ500 አስከ 5000 ብር መጣል የሚችሉ ሲሆን ብሩንም መተግበሪያውን በመጠቀም በሞባይ ባንኪንግ ወይም በቴሌ ብር መክፍል እንደሚችሉ ስራ አስኪያጁ ገልጧል፡፡

በቅርቡ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በጋራ ለመስራት ስምምነት መደረጉን ያስረዳው አቶ ብስራት ስምምነቱ ዕቁብን በዘመናዊና አስተማማኝ መንገድ መሰብሰብ ያስችላል ብሏል።

በባህላዊው መንገድ ዕቁብ እየጣሉ ያሉ ሰዎች ወደ ዲጂታል ዕቁብ ለመምጣት የሚፈልጉ ከሆነ ማህበራቸው ሳይፈርስ በቴክኖሎጂው ተጠቅመው እቁባቸውን ማዘመን የሚችሉ ሲሆን እጣው የሚወጣው መተግበሪያው ላይ  በቀጥታ  ይሆናል፡፡

በዲጂታል ዕቁብ መተግበሪያ ላይ እጣ የደረሰው ሰው እጣውን መሸጠ የሚችልበት አሰራር የተካተተ ሲሆን ይህም እጣ ያልወጣለት ግን ብር ለሚያስፈልገው ዕቁብተኛ ትንሽ ክፍያ በመክፈል የሚገለገልበት አሰራር ነው፡ አንድ ዕቁብተኛ ክፍያውን መክፈል ካልቻል ድርጅቱ ክፍያውን የሚሸፍን ሆኖ በቀጣዩ ከዕቁብተኛው ከአንድ እስከ ሁለት በመቶ የሚሆን ቅጣት ተቆራጭ ይደረግበታል፡፡

በአሁን ወቅት 400 አቁብተኞችና  ከ7 ሺ  በላይ የዲጂታል ዕቁብ መተግበሪያን ያወረዱ  ሰዎች መኖራቸውን፣ በተለይም በውጭ አገራት ያሉ ዜጎች በዲጂታል ዕቁብ ላይ ፍላጎት ማሳየታቸውን የገለፁት ስራ አስኪያጁ የውጭ ምንዛሬን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባትም ትልቅ አማራጭ ስለሚሆን በቅርቡ ለመጀመር እቅድ መያዙን ገልፀው ከተለመደው የገንዘብ ዕቁብ በተጨማሪም የላፕቶፕ፣ የስልክ፣ የቲቪ፣ የሶፋ፣ የመኪና እና ለተሎች የአይነት አቁብ ለመጀመርም ዝግጅቱ እየተደረገ መሆኑን  ተናግረዋል፡፡

ማህሌት ዘውዱ በዲጂታል ዕቁብ መተግበሪያ ዕቁብ ከሚጥሉ ዕቁብተኞች መካከል አንዷ ነች፡፡  “ሁለት ዙር ዕቁብ በመጣል እጣ ደርሶኛል፡፡ ዕቁብተኞች ለ50 ሺህ ዕቁብ 2 ሺህ ብር ለ20 ሺህ ዕቁብ ደግሞ  ስምንት መቶ ብር የአግልግሎት ክፍያን ለድርጀቱ ይከፈላል” ትላለች፡፡ ማህሌት አያይዛም ወደ ፊትም ድርጅቱ ባዘጋጃቸው የመኪና እና የመሳሳሉትን የአይነት እቁቦች በመቀላቀል እቅዷን በቀላሉ ለማሳካት መዘጋጀቷን ገልፃለች፡

በባልትና ስራ የምትተዳደረው ናርዶስ ግርማ ህጋዊነቱን አረጋግጣ ወደ ዲጂታል  ዕቁብ እንደተቀላቀለች እንደገባች በሶስተኛ ሳምንት እጣ እንደወጣላት ትናገራለች ፡፡

የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አዲሱ አበባው ለአዲስ ስታንዳርድ እንደተናገሩት የገንዘብ ስርዓቱ ወደ ዲጂታል ቴክኖሎጂ መምጣቱ የገንዘብ ዝውውር በባንክ እንዲከናወን ስለሚያደርግ የጥሬ ገንዘብ ስርዓትን በማስቀረት ረገድ ፋይዳ እንደሚኖረው ገልፀዋል፡

የዲጂታል ፋይናንስ መስፋፋቱ ለግብይት ምቹ ስለሚሆን የገንዘብ ዝውውርን ይጨምራል ያለሉት  ባለሙያው ይህ አሰራር የጥሬ ገንዘብ ግብይትን ስለሚቀንስ መንግስት ገንዘብ ለማተም የሚያወጣውን የውጭ ምንዛሬ  ይቀንሳል ሲል ገልጧል፡፡

ከዚህ በፊት የነበረው የባህላዊ ዕቁብ አሰራር ላይ ዕቁብ የሚጥሉ ሰዎች ገንዘቡን በግለሰብ ቤት ነበር ሲያስቀምጡ የነበረው፡፡ የዲጂታል የገንዘብ አሰራር ግን በባንክ በኩል የሚከናወን በመሆኑ ተጠቃሚዎች ባንክ የማስቀመጥ እድል ከፍ ስለሚል ባንኮች ገንዘብ እንዲኖራቸው ስለሚያደርግ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ ያግዛል ይላሉ ባለሙያው፡፡

ባለሙያው አያይዘውም የዲጂታል ዕቁብ አማራጭ  ግብይትን ለማፋጠን ስለሚያግዝ ህብረተቡ ይህንን የመጠቀም ልምዱን እንዲያሳድግ መክረዋል፡፡ አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.