By Natnael Fite @NatieFit
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 23/2015 ዓ.ም፡- አለባበሳቸው እንደማንኛው የሀገሪቱ ዜጎች የሆነ ሁለት ንጹሃን የኋሊት የፊጥኝ ታስረው የክልል የጸጥታ ሀይሎች መሆናቸውን የሚያመለክት የደንብ ልብስ የለበሱ የጸጥታ ሀይሎች ሲገደሉ የሚያሳይ ቪዲዮ በያዝነው በሰኔ ወር በማህበራዊ ሚዲያ የትስስር በስፋት መሰራጨቱ ይታወሳል። ግድያውን የፈጸሙት ሰዎች የለበሱት የደንብ ልብስ የሲዳማ ክልል ልዩ ሀይል መሆኑን የሚያሳይ ምልክት ያለው ነው።
በቪዲዮ ተቀርጾ የተሰራጨው ግድያው የተፈጸመው በምዕራብ ኢትዮጵያ የቤኒሻንጉል ክልል መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና የፈረንሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ ማረጋገጣቸውን አስታውቀዋል። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ድርጊቱ ከፍርድ ሂደት ውጪ የተፈጸመ ግድያ ነው ሲል የገለጸ ሲሆን የፈረንሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ ደግሞ ድርጊቱ የተፈጸመው በ2013 አጋማሽ መሆኑን በዘገባው አመላክቷል።
ግድያው የተፈጸመው በቤኒሻንጉል ክልል መተከል ዞን ድባቴ ወረዳ ጊፖ መንደር በ2013 ዓ.ም መሆኑን የአከባቢው ተወላጅ የሆኑት እና ጉዳዩን በቅርበት የተከታተሉት ተመስገን ገመቹ ለአዲስ ስታንዳርድ አረጋግጠዋል። በዚያን ቀን ሀብታሙ አያና እና ተክሌ መንገሻ የተባሉ ሁለት ሰዎች አሰቃቂ በሆነ መንገድ ተገድለዋል፤ ሁለቱም ሰላማዊ ገበሬዎች ናቸው፤ ተክሌ የተባለው ሰው አባቱ መታሰሩን ሲሰማ ቀጥታ አባቱ ወደታሰረበት ቦታ ሄደ፤ ወደዚያ በቀጥታ መሄዱ ብቻ ሰላማዊ መሆኑን ቢያሳይም ይዘው አሰሩት፤ ሲሉ ተመስገን ገመቹ ሁኔታውን ለአዲስ ስታንዳርድ አብራርተዋል። እንደ ተመስገን ገመቹ ከሆነ ተክሌ እና ሀብታሙ ታስረው ወደ ግልገል በለስ እስር ቤት በተወሰዱ በቀናት ውስጥ ነው የተገደሉት። በወቅቱ የመከላከያ ሰራዊት አባላት፣ የሲዳማ ክልል ልዩ ሀይል አባላት እና የአማራ ክልል ልዩ ሀይል አባላት የአከባቢውን ጸጥታ ለማስፈን ተመድበው ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ገልጸዋል።
ባለፉት ሁለት አመታት በቤንሻንጉል ክልል 78 የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች የሆኑ በማንነታቸው ምክንያት መገደላቸውን እና ይህንንም የሚያረጋግጥ ማስረጃ እንዳላቸው የገለጹት ተመስገን ለመቁጥር የሚያስቸግር ግድያ እና ዝርፊያ በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች መፈጸሙን አስታውቀዋል።
የሲዳማ ክልል መንግስት ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ በተንቀሳቃሽ ምስሉ የሚታዩት የክልሉን ልዩ ሀይል ደንብ የለበሱት ሰዎች እንደማያውቃቸው በመግለጽ የክልሉ ልዩ ሀይል አባልት አይደሉም ብሏል። መግለጫው ልዩ ሀይሉ በመልካም ስነ ምግባሩ የሚታወቅ፣ በዲሲፕሊን የታነጸ እና ተልዕኮውን በክልል እና በሀገር ደረጃ መፈጸም የሚችል ነው በማለት ልዩ ሀይሉ በድርጊቱ ምንም አይነት ተሳትፎ የለውም ሲል ክዶታል።
በአሁኑ ወቅት ከድርጊቱ ጋር የተያያዘ ወንጀለኞቹን ተጠያቂ ለማድረግ የፍርድ ቤት ምርመራም ይሁን ለህዝብ የተገለጸ መረጃ የለም። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የቤኒሻንጉል ጉምዝ ቢሮ ሃላፊ ጉርሜሳ ባፉታ ለአዲስ ስታንዳርድ እንዳስታወቁት በጉዳዩ ዙሪያ የተደረገው ምርመራ የመጨረሻ ውጤት ይፋ እንደሚደረግ እና የተጠያቂነት እርምጃው ላይም ክትትል እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
በተንቀሳቃሽ ምስል የተደገፉ ግድያዎች
ድርጊቱ በሀገሪቱ የተከሰተ የመጀመሪያ አይደለም፤ የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች በክልሉ አሰቃቂ ግድያ ሲፈጽሙ የሚያሳይ በርካታ ተንቀሳቃሽ ምስል በስፋት ተሰራጭተዋል። በለፈው አመት ሰዎች በህይወት እያሉ ሲቃጠሉ የሚያሳይ ምስል በስፋት ተሰራጭቷል። ይህ አሰቃቂ ድርጊቱ ከተፈጸመ 15 ወራትን ቢያስቆጥርም የፌደራል መንግስቱም ይሁን የክልሉ መንግስት ድርጊቱን ፈጻሚዎች በግልጽ ክስ አልመሰረቱባቸውም። በወቅቱ ከድርጊቱ ጋር በተገናኘ የተጠረጠሩ አራት ሰዎች በቁጥጥር ስር ቢውሉም ክስ ይመስረትባቸው ወይም ፍርድ ይሰጣቸው የሚታወቅ ነገር የለም።
በአደባባይ የተገደለው አማኑኤል ወንድሙን ጨምሮ በርከታ የሀገሪቱ ሰዎች ከፍርድ ሂደት ውጭ የጸጥታ ሀይል መለዮ በለበሱ የመንግስት ሀይሎች ተንቀሳቃሽ ምስል በማስደገፍ በግልጽ ግድያ ተፈጽሞባቸዋል። በጋመቤላ በጸጥታ ሀይሎች የተፈጸመው ጭፍጨፋ 50 ሰዎችን ቀጥፏል።
ተጠያቂ እንዳይሆኑ የሚሰጥ ከለላ
በኢትዮጵያ የጸጥታ ሀይሎች መለያ በለበሱ ሰዎች ከፍርድ ውጭ በዘፈቀደ በአደባባይ የሚካሄዱ ግድያዎች እየጨመሩ መጥተዋል፤ የድርጊቱ ፈጻሚዎች ተጠያቂ አለመሆን አሳሳቢ ሁኗል። በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሰቪል እና ፖለቲካ መብቶች ኮሚሽነር አብዲ ጂቢር ለአዲስ ስታንዳርድ እንዳስታወቁት ኮሚሽኑ በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች የተፈጸሙ እና በተንቀሳቃሽ ምስል የተደገፉ ወንጀሎች ዙሪያ መረጃዎች አሰባስቧል። ኮሚሽኑ ባካሄደው ምርመራ ያገኘውን ውጤት እና ምክረ ሀሳብ ለመንግስት ማቅረቡንም አስታውቀዋል።
ኮሚሽነሩ በተጨማሪም ኮሚሽኑ ተጠያቂነትን ለማስፈን መንግስት ስለወሰዳቸው እርምጃዎች ክትትል ማድረጉን ጠቁመው ከላይ በተጠቀሱት ጉዳዮች ዙሪያ መረጃ እንደሌላቸው አስታውቀዋል።
ያሬድ ሀ/ማርያም የሰብአዊ መብቶች ተከላካይ ማዕከል ዳይሬክተር ለአዲስ ስታንዳርድ ባጋሩት አስተያየት በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እየተፈጸሙ ያሉ ድርጊቶች ከመቸውም በላይ እየጨመሩ መምጣታቸውን ገልጸዋል። ባለፉት ግዜያት በመንግስት ሀይሎች የሚፈጸሙ ግድያዎች በሚስጥር የሚከናወኑ በመሆኑ ምርመራ ማከናወን አስቸጋሪ ነበር ያሉት ያሬድ በአሁኑ ወቅት ትልቁ ችግር መንግስት በህብረት ለሚፈጸሙ የዚህ አይነት ድርጊቶች ተጠያቂ እንዳይሆኑ የሚሰጥ ከለላ ነው ብለዋል። መንግስት ወንጀል የፈጸሙ ጥፋተኛ የጸጥታ ሀይሎችን ለፍርድ በማቅረብ ተጠያቂ ሊያደርጋቸው ይገባል፤ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶችም መንግስት ላይ ጫና ማሳደር ይገባቸዋል ሲሉ አሳስበዋል።
አዲስ ስታንዳርድ በጉዳዩ ዙሪያ የኦሮምያ እና የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች የሰላም እና የጸጥታ ቢሮ ሃላፊዎች አስተያየታቸውን ለማካተት ያደረገችው ጥረት አልተሳካም። አስ