ዜና ፡- የኢትዮጵያ መንግስት ከሌሎች ታጠቂ ኃይሎች ጋርም ሰላማዊ ድርድር እንዲደርግ ኢዜማ ጠየቀ ፣ በትግራይ የሚገኙ ፓርቲዎች በበኩላቸወ ስምምነቱ የትግራይ ህዝብ የፈጠረውን አቅም የሚያመክን መሆኑን አስታወቁ

አዲስ አበባ፣ጥቅምት25/ 2015 ዓ.ም፡- በኢትዮጵያ መንግስት እና በትግራይ አመራሮች መካከል የተደረገው ስምምነት “መርህ የተከተለ” መሆኑን በመጥቀስ በተመሳሳይ መልኩ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ከሚገኙ ሌሎች ታጠቂ ኃይሎች ጋርም ሰላማዊ ድርድር በማድረግ ሰላማዊ መፍትሄ መፈለግ ተገቢ መሆኑን የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) አስታወቀ፡፡

ኢዜማ የኢትጵያ መንግስትና የህወሓት ባለስልጣናት የተፈራረሙት የሰላም ስምምነት ተገቢነት ገልፆ ከሌሎች ታጠቂ ሀይሎችም ጋርም ሰላም እንዲፈጠር በአፅንኦት መስራት እንደሚያስፈልግ አሳስቧል ፡፡

ኢዜማ በኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት መካካል የተፈረመውን የሰላም ስምምነት አስመልክቶ ትላንት በሰጠው መግለጫ የሰላም ስምምነቱ “ይበል የሚያሰኝ” መልካም ጅማሮ በመሆኑ ተግባራዊነቱ ላይ ባለድርሻ አካላት ሁሉ ፍጹም ታማኝ መሆን ይጠበቅባቸዋል ሲል አሳስቧል፡፡

መግለጫው አያይዞም “የሀገርን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ለማስከበር ትጥቅ ይዞ የሚንቀሳቀስን ኃይል የማዘዝ ሥልጣን ሊኖረው የሚገባው የፌደራል መንግሥት ብቻ ስለመሆኑ ሀገራዊም ሆነ ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን አስረግጦ በማስገንዘብ ህወሓት ትጥቁን እንዲፈታ ሊደረግ ይገባል” ብሏል፡፡  

በአፍሪካ ህብረት መሪነት በደቡብ አፍሪካ ለ 10 ቀናት ሲካሄድ ቆይቶ በኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት መካካል የተፈረመው ስምምነት በሀገሪቱ “አንድ የመከላከያ ኃይል ብቻ” እንዲኖር መስማማታቸውን አስታውቀዋል።

ኢዜማ  በየትኛውም ክልል ውስጥ የሚገኙ የፌደራል ተቋማትንም ሆኑ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር የመጠበቅና የአየር ክልሉን ሙሉ ለሙሉ የመቆጣጠር ሥልጣን በብቸኝነት የፌደራል መንግሥቱ መሆኑን ህወሓትም ሊገነዘበው፤ መንግሥትም ሊዘነጋው አይገባም ሲል አሳሳስቧል፡፡

መንግስት ስምምነቱ እንዳይጨናገፍ እና ተመልሰን የጦርነት አዙሪት ውስጥ እንዳንገባ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚኖርበት ጠቅሶ ለተግባራዊነቱም ሁሉም አካል በትጋት መስራት  ይጠበቅባቸዋል ብሏል፡፡

በሌላ መልኩ ደግሞ በትግራይ ክልል የሚገኙ ሶስት ፓርቲዎች የሰላም ስምምነቱ “ተቀባይነት የለውም” እንደሌለው ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሓት መካካል የተፈረመውን ስምምነት “በመቃወም” በትላንትናው እለት የጋራ መግለጫ  ያወጡት ሳልሳይ ወያነ ትግራይ ፣ ውድብ ናጽነት ትግራይ እና ብሄራዊ ባይቶና ዓባይ ትግራይ  ሲሆኑ የተደረገው ስምመነት ህገ መንግስትን መሰረት አድርጎ የሚኖረው የድርድርና የንግግር ሂደት ግዛታዊና ብሄራዊ አንድነትን የሚሸረሽርና የሚያጥ ሂደትስ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም ብለዋል።

ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው እንዳስታወቁት “በትግራይ ህዝብ ላይ የተፈጸመ ዘር ማጥፋትን ተከትሎ የኢትዮጵያ ህገመንግስት አንደፈረሰ የሚታወቅ መሆኑን ጠቁመው በዚህ መነጽር የምዕራብ ትግራይ ህዝብና መሬት ሁለት ተፋላሚ አካላት በአኩል የሚደርሳቸው፤ የሚያጋጭ ቦታ አንዲሆን የሚደረግ ማነኛውም የሰላም ሂደትና ተግባር በግዜው ካልታረመ ለትውልድ የሚሻገር ችግር አንደሚፈጥር ምንም ጥርጥር የለውም” ብሏል፡፡

አክለውም ህወሓት በፈረሰው የኢትዮጵያ ህገ መንግስት መሰረት አድርጎ፤ የሚያስር ወይም የሚይዝ የድርድር ሂደት ተቀብሎ በተለያዩ ቦታዎች የሚገልጸው ማረጋገጫ የትግራይን መሬትና ህዝብ አሳልፎ የሚሰጥ፤ የህዝብን ፍላጎት የሚጻረር፤ ህዝባዊ ትግል  የፈጠረውን አቅም የሚያመክን አቋም ሰለሆነ መቃዎም አለብን ሲሊ አቋማቸውን ገልፀዋል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.