በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች የሚደረጉ ድጋፎችም ቀጣይነት እንዲኖራቸው ስልታዊ እና የተቀናጁ መሆን እነዳለባቸው ማህበሩ አሳስቧል፡፡
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6/ 2015 ዓ.ም – የኢትዮጲያ ቀይ መስቀል ማህበር በድርቅ ክፉኛ ለተጎዱ የቦረና እና የሞያሌ አካባቢዎች ወደ 27 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የምግብ ድጋፍ ለ6130 ሰዎች እንዲሁም የ800 ሺህ ብር የጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ለ1000 ሰዎች ማድረጉን ዛሬ በፅፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡
የማህበሩ ዋና ፀሀፊ አቶ ጌታቸው ታዓ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ እንደተናገሩት ድርቁ በሰውም ሆነ በእንስሶች ላይ እያስከተለ ካለው ጉዳት አንፃር ተጨማሪ ድጋፎችን ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ ማኅበሩ ቀጣይነት ያለው የሀብት ማሰባሰብ ዘመቻ እያካሄደ ይገኛል፡፡
በዚህም መሰረት ባለፈው ሁለት ሳምነት ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ለማሰባሰብ መቻሉን አቶ ጌታቸው ታዓ የማህበሩ ዋና ፀሀፊ አሳውቀዋል፡፡
የማህበሩ ፕሬዝዳንት አቶ አበራ ቶላ በበኩላቸው በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች የሚደረጉ ድጋፎች ዘላቂነት ያላቸው እና የተቀናጁ መሆን እነደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡
በሀገሪቱ በተለይም በዝቅተኛ አካባቢዎች ላይ የሚከሰቱ ተደጋጋሚ የድርቅ አደጋዎች በዘላቂነት መፍትሄ እንዲያገኙ የተቀናጀ እና ሀገር አቀፋዊ የሆነ ርብርብ የሚያስፈልግ ሲሆን ለዚህም መንግስትም ሆነ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡
የማህበሩ ፕሬዝዳንት አቶ አበራ ቶላ በቦረና ዞን በድርቅ ከፍተኛ ጉዳት በደረሰባቸው አባባቢዎች በሁሉም አቅጣጫ ማለትም በውሀ አቅርቦት፣ የተረፉትን ከብቶች በማከምም ሆነ ህብረተሰቡ ወደ ተለመደ ያኗኗር ዘይቤው እንዲመለስ እና ቀጣይ ህይወቱን እንዲመራ ዘር በማቅረብም ሆነ በሌሎች ማህበራዊ እና ጤናን መሰረት ባደረጉ ድጋፎች በቅንጅት መስራት እነዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡
ማህበሩም በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች አሁን እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እነደሚቀጥል እና በተለይም ህብረተሰቡ የሚፈልገውን ነገር ከገበያ መርጦ እንዲገዛ ለማበረታታት ቀጥተኛ የሆነ የገንዘብ ልገሳ ለተጎጂ ወገኖች የሚያደርግ መሆኑን እና እዚህ ላይ ትኩረት ሰጥቶም እንደሚሰራ አቶ አበራ ቶላ የኢትዮጲያ ቀይ መስቀል ማህበር ፕሬዝዳንት ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጲያ ቀይ መስቀል ማህበር የወጣት በጎፈቃደኞች ተወካይ የቦርድ አባል ዶ/ር አዲስአለም ሙላት በተልተሌ እና በዲሎ ተገኝታ ባደረገችው ጉብኝት ህፃናት አዛውንቶች እና በእድሜ ገፋ ያሉ ሰዎች በድርቁ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው እና በተለይ በእድሜ የገፉ ሰዎች ልጆቻቸውንም ሆነ የልጅ ልጆቻቸውን የመንከባከባከብ ሀላፊነት ስላለባቸው በድርቁ ይበልጥ ስለተጎዱ እርዳታ የሚያደርጉ መንግስታዊም ሆነ መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት ለአዛውንቶቹ ትኩረት አድርገው መስራት እንዳለባቸው አስረድታለች፡፡
በተጨማሪም ህብረተሰቡ በማህበራዊ፣በስነልቦናም ሆነ በኢኮኖሚ በመጎዳቱ ከምግብ እና ከገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ የስነ-ልቦና፣ የጤና እና ወደተለመደ ሕይወቱም በቀላሉ እንዲመለስ ጥብቅ የሆነ ክትትል እንደሚያስፈልገው ዶ/ር አዲስአለም ሙላት አሳስባለች፡፡
የኢትዮጲያ ቀይ መስቀል ማህበር በስተመጨረሻም በድርቅ ለተጎዱ ወገኖችን ለመታደግ 9400 ላይ OK ብለው በመላክ 1 ብር እንዲለግሱ እየጠየቀ በአይነት ድጋፍ ለማድረግ ለሚፈልጉ ወገኖችም አዲስ አበባ ስቴዲየም አካባቢ በሚገኘው የማህበሩ ዋና መስሪያ ቤት ግቢ ድረስ በማምጣት መለገስ እንደሚቻል አስታውቋል፡፡
በተጨማሪም በቴሌ ብር ሂሳብ ቁጥር 0907 ወይም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አካውንት ቁጥር 1000529766916 ለቦረና ድርቅ ምላሽ ተብሎ በተከፈተው አካውንት ማስገባት እንደሚቻል እንዲሁም አጭር የባንክ አካውንት ቁጥር 907 በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፤ በዳሽን ባንክ፤ በአቢሲኒያ ባንክ፤ በአዋሽ ባንክ እና በኦሮሚያ ህብረት ሥራ ባንክ ገቢ ማድረግ የሚቻል መሆኑን የገለፀ ሲሆን በውጭ ሀገር ለሚገኙ ወገኖቻችን ደግሞ በማህበሩ ዌብ ሳይት ላይ በተገለፁት የመለገሻ መንገዶች ለወገኖቻችን ድጋፍ ማድረግ እነደሚቻል በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተመቁሟል፡፡ የትዮጲያ ቀይ መስቀል ማህበር