በሞላ ምትኩ @MollaAyenew
አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 12/2015 ዓ.ም፡- ላለፉት ሶስት ዓመታት የሲሚንቶ ምርትና ስርጭት መዛባት እየሰፋ መምጣቱን ተከትሎ ኑሯቸውን በሲሚንቶ ግብይት ላይ የተመሰረተ ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው ዜጎችን ለከፋ ችግር መዳረጋቸውንና የልጆቻቸውና የራሳቸው የእለት ተለት ጉርስ ለማግኘት ከማይችሉበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ይገልፃሉ።
የሲሚንቶ እንዱስትሪ በተደጋጋሚ የሚለዋወጡትን የፖሊሲ ደንቦችንና የተለያዩ ውጣ ውረዶችን ያስተናገደ ኢንዱስትሪ ነው። ሐምሌ 2014 ዓም የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሲሚንቶ ዋጋን የሚቆጣጠር እና በሚኒስቴሩ የሚተገበረው መመርያ ማውጣቱንና መመሪያው ከወጣበት ቀን ጀምሮ ሌሎች ቀደምት መመሪያዎች መሰረዛቸውን ያስታወቀ ሲሆን የሲሚንቶ ገበያው ላልተወሰነ ጊዜ በነጻ የገበያ ዋጋ ላይ ተመስርቶ እንደሚወሰንም ገልፆ ነበር።
በመስከረም 2015 ዓም ደግሞ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በሀገሪቱ ያለውን የሲሚንቶ ምርት የዋጋ ንረት ለመግታት አዲስ የሲሚንቶ ዋጋ ደንብ ማውጣቱን አስታውቋል፣ ይህም ከአንድ አመት በፊት ከወጣው እጅግ በጣም የራቀ ነው። የነፃ ገበያ ኢኮኖሚውን የሚወስን ነበር።
እንደነዚህ ያሉት የፖሊሲ ለውጦች በባዶው የተከናወኑ አልነበሩም። በሰኔ 2012 ዓም መንግሥት ስድስት ኩባንያዎች ብቻ ሲሚንቶ በሀገሪቱ ውስጥ እንዲያከፋፍሉ የሚፈቅድ አዲስ መመሪያ አውጥቷል። መመሪያው በወጣበት ወቅት በአዲስ አበባ ብቻ የሲሚንቶ ንግድ ሰንሰለት ወደ 600,000 ለሚጠጉ ሰዎች የስራ እድል ፈጥሮ ስለነበር ብዙዎች በለውጡ መነቃቃት ጀምረው እንደነበር ይታወቃል።
ቀውሱ በዘርፉ የምርት እና የአቅርቦት ሰንሰለት የገበያ ኢኮኖሚ ላይ ህይወታቸውን የመሰረቱ በርካታ የጉልበት ሰራተኞች እና ነጋዴዎችን ህይወት እና መተዳደሪያ ላይ ብቻ ሳይሆን እንደ የመኖሪያ ቤት ግንባታ በመሳሰሉት መሰረታዊ ፕሮጀክቶች ጀምሮ እስከ ቅንጡ ተቀማጭነቱ ዱባይ በሆነው ኤጊል ሂልስ የሚገነባው ህንፃ ድረስ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድሯል።
የሲሚንቶ ግብይት ለዕለታዊ ጉርስ
የሲሚንቶ ግብይት መዛባት ያስከተለው ጫና በርካሰራተኞችንና ነጋዴዎች ሊቋቋሙት የማይችሉበት ሆኗል።
ከመገናኛ ወደ ኮተቤ በሚወስደው መንገድ ዳርና ዳር የተደረደሩት የሲምንቶ መሸጫ ሱቆች ላለፉት ስድስት ወራት ለግብይት የሚያውሉት ሲምንቶ እንዳያገኙ በመታገዳቸው ምክንያት የተዘጉ ቢሆንም ቀደም ሲል ከፍተኛ ግብይት የነበረው አካባቢ ነበር። አሁን ግን ምንም አይነት ግብይት ባለመኖሩ ፀጥ ረጭ ብሏል። ሱቆቹም ተዘግተዋል።
ከተዘጉት ሱቆቹ መካከል በአንዱ ፊት ለፊት ቁጥራቸው በግምት 10 የሚሆኑ ወጣቶች ሰብሰብ ብለው ቁማር ይጫወታሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ አለፍ አለፍ ብለው ሁለት ሶስት ሆነው ተቀምጠዋል ሌሎቹም የቆሙት መኪኖች ተደግፈው ቆመዋል።
ቻሌ አግኝ የ30 ዓመት ወጣትና የሁለት ልጆች አባት ሲሆን ላለፉት 8 አመታት ሲሚንቶን ከሱቆች ወደ መኪናዎች በመጫን ወይም ከመኪኖች በማውረድ ወደ ሲሚንቶ ሱቆች በማስገባ በሚያገኘው ገንዘብ ራሱን እና ቤተሰቡን ያስተዳድር ነበር። “የእለት እንጀራዬ የተመሰረተው በእነዚህ ሱቆች ውስጥ የሲሚንቶ ግብይት በመኖሩ ነበር። አሁን ግን ሲሚንቶ እንዳይገዙ እና እንዳይሸጡ በመከልከላቸው ሁሉም ሱቆች ተዘግተዋል። እኔን ጨምሮ በዚህ አካባቢ ብቻ በማህበር የተደራጁ ከ70 በላይ የቀን የጉልበት ሰራተኞች አለን። የሁላችንም ኑሮ በዚህ ስራ ላይ የተመሰረተ ነው። ካለፈው ሐምሌ ወር 2014 ዓም ጀምሮ ግን ሱቆቹ በመዘጋታቸው ከባድ ችግር ላይ ወድቀናል” ሲል ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግሯል።
ቻሌ አያይዞም ጠዋት እንመጣለን ያለምንም ስራ ተቀምጠን ውለን ማታ እንመለሳለን። ከጭንቀት የተነሳ አንዳንዶቹ ከሱቁ ፊት ለፊት እንደሚትመለከተው ቁማር እየተጫወቱ ይውላሉ ምንም ዓእነት የሚሰራ ነገር ባለመኖሩ ነው። ስራ በነበረበት ወቅት አንድም ሰው በዚህ መልክ አይታይም ነበር።
ወጣት ወንድሙ ሙልዬ በበኩሉ “መንግስት ስራ አጥነትን ለመቀነስ እየሰራ መሆኑን በተለያየ መንገድ እየሰማን ነው፣ ብዙ ሰዎችም ስራ እያገኙ እንደሆነ እንገነዘባለን። ሆኖም ግን እኛን ለብዙ ዓመታት ስንተዳደርበት ከነበርንበት ሥራ እየበታተነን ነው” ብሏል።
ፀጋዬ ዘርጋ የ48 ዓመት ጎልማሳ ሲሆን ባለትዳር እና የሶስት ልጆች አባት ነው። ለሲሚንቶ ገዥዎች የጭነት አገልግሎት በመስጠት ህይወቱን ይመራ እንደነበር ይናገራል። ” ላለፉት ስድስት ወራት በማለዳ እመጣለሁ፣ ቀኑን ሙሉ ያለ ምንም ስራ እዚህ አሳልፌ ማታ ወደ ቤት እመለሳለሁ፣ ስራ ስለሌለ ቤተሰቦቸን መመገብ አልቻልኩም። በዚህ ስፍራ የጭነት አገልግሎት የሚንሰጥ ሰዎች 200 ያህል ነን። ከፍተኛ ችግር ላይ በመሆናችን መንግስት መፍትሄ እንዲሰጠን እንጠይቃለን” ይላል።
አቶ ፀጋዬ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደገለፀው ተስፋው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሟጠጠ መጥቷል። ሲሩባቸው የነበሩ መኪኖችን ሸጠው ወደ ሌላ ስራ ለመሰማራት መኪኖቹ ያረጁ በመሆናቸው ዋጋ አያወጡም። በዝቅተኛ ዋጋ ለመሸጥ እንኳን ቢሞከር ገዥ የለም።
ሰለሞን አሰፋም የሚተዳደረው በተመሳሳይ ስራ ነው። “ወደ ስድስት ወር ገደማ ምንም ገቢ አልነበረንም። በአሁኑ ወቅት የቤት ኪራይ መክፈልና የልጆቻችንን የእለት ምግብ መሸፈን የማንችልበት ደረጃ ላይ እንገኛለን” ይላል።
አቶ ወልዴ ግርማ በበኩሉ ‹‹ችግሩን መንግሥት ያውቀዋል የተለያዩ ሚዲያዎችም ዘግበውታል። ከዚህ በተጨማሪ የንግድና የቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ኃላፊዎች በተለያዩ ጊዜያት በመምጣት ችግሩን በቅርቡ እንደምያስተካክሉ ተስፋ ሰጥተውናል፣ ነገር ግን መፍትሔ ሳይገኝ ስድስት ወራት አለፉ”።
የጭነት አገልግሎት ሰጪዎቹ እና የጉልበት ሰራተኞች ችግሩ የተፈጠረው በመልካም አስተዳደር እጦት እና በሙስና እንደሆነ ይናገራሉ። ምክንያቱም ይላሉ በዚህ ሲሸጥ በነበረበት ጌዜ ኩንታል ሲምንቶ በዛ ቢባል እስከ 800 ነበር አሁን ግን አንድ ኩንታክ ከ1800 እስከ 2000 ብር ውስጥ ለውስጥ እየተቸበቸበ ነው እኛ ነን በመካከል የተጎዳነው ይላሉ።
በኢትዮጵያ የሲምንቶ አምራቾች ማህበር ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ ሀይሌ አሰግድ በበኩላቸው ኩንታል ሲምንቶ እስከ 2000 ብር እንደሚሸጥ ያምናሉ። ከዚህም በላይ የምርት እጥረት ማጋጠሙ የነበረውን ችግሩን እንዳባባሰው ነው የሚገፁት። “የሰላም እጦት፣ የመለዋወጫ ዕቃዎችን እና የድንጋይ ከሰል መግዣ የውጭ ምንዛሪ አለመኖር የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው እንዳያመርቱ ከፍተና ማነቆ እንደሆነባቸው” ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንቱ አያይዘውም ከሶስት አመት በፊት ከነበረን አጠቃላይ ምርት አሁን ያለው 30 በመቶ ቀንሷል በተለይ ደግሞ በሰሜን ኢትዮጵያ በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ከመቀሌ ከተማ በ7 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ሞሶቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ 9 መቶ ሺህ አመታዊ የማምረት አቅም የነበረው ቢሆንም ለሁለት አመታት ማምረት ማቋረጡ አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩን ይገልፃሉ።
“ቸርቻሪዎች ቀድሞውንም ከገበያ ወጥተዋል። ተቋራጮች ከፋብሪካዎች ሲሚንቶ መግዛት አይችሉም። አከፋፋዮች ምንም ዓይነት ግንባታ ላላቸው ግለሰቦች አይሸጡም በዚህ ምክንያት በሲሚንቶ ግብይት ይተዳደሩ የነበሩ ሰዎች ኑሮ መዛባቱ አይካድም” ይላሉ አቶ ሀይሌ።
እንደ አቶ ኃይሌ አሰግድ ገለፃ የሲሚንቶ ምርት በመቀነሱና እና በችርቻሮ ሱቆች ላይ እገዳ በመደረጉ ኑሯቸው ከሲምንቶ ንግድ ጋር የተቆራኘ ሰዎች በእጅጉ እየተጎዱ ነው።
በእንዚህ የችርቻሮ ሱቆች የጉልበት ሰራተኞችና እንደዚሁም የጭነት አገልግሎት የሚሰጡ ሾፌሮች ላለፉት ስድስት ወራት ምንም ዓይነት ስራ ባለመኖሩ ለከፋ ችግር ከተዳረጉ ሰዎች መካከል መሆናቸው እሙን ነው።
ከስድስት ወራት በፊት በመንግስት የወጣው የሲሚንቶ ስርጭት መመሪያ ህብረተሰቡን ከድላሎች፣ አስፈላጊ ካልሆነ የዋጋ ንረት፣ ከስርቆት እና ከቢሮክራሲያዊ አሰራር ለማላቀቅ ታስቦ የነበረ ቢሆንም ባለፉት አምስት ወራት ትግበራ እንታየው ችግሮቹ እንዳልተቀረፉና መንግስት አሰራሩን እንደገና በመፈተሽ ላይ መሆኑን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ቁምነገር እውነቱ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል።
ወ/ሮ ቁምነገር አያይዘውም “ቀደም ሲል የተነሱትን ችግሮች ባለፉት አምስት ወራት ገምግመን የለየን በመሆኑ የሲምንቶ ቸርቻሪዎች በግብይት እንዲቀጥሉ ወስነናል። የሚኖረንን አጠቃላይ የአሰራር ሂደት በቅርቡ ለህዝብ እናሳውቃለን” ብለዋል።
ከደርባ የሚመረት ሲምንቶ ሙሉ በሙሉ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እና የኮይሻ ፕሮጀክት የመሳሰሉ የመንግስት ፕሮጀክቶች የሚውል በመሆኑና ሌሎች ፋብሪካዎችም በሙሉ አቅማቸው እያመረቱ ባለመሆኑ አጥረት እንዳለ የገለፁት ወ/ሮ ቁምነገር ባለፉት አምስት ወራት ውስጥ 16 ሚሊዩን 650 ሺሀ 8 መቶ 26 ኩንታል ሲሚንቶ መሰራጨቱንና ይህ ደግሞ ከሚፈለገው አጠቃላይ የሲሚንቶ መጠን 72 በመቶ መሆኑን ገልፀዋል።
ፕሬዝዳንቱ አያጠይዘውም መንግስት ለሲሚንቶ ምርትና ስርጭት ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ አሳስበዋል። “መንግስት የችርቻሮ ነጋዴዎች ወደ ቀድሞ ስራቸው እንዲቀጥሉ እና ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች የውጭ ምንዛሪ መፍቀድ ከድንጋይ ከሰል ገዝተው ወደ ሀገር ውስጥ እንዲያስገቡ እንዲሁም መለዋወጫ እቃዎችን መግዛት እንዲችሉና በሙሉ አቅማቸው እንዲሰሩ ማበረታታት ይኖርበታል” ይላሉ።
የቀን ሰራተኞቹ፣ እና ሹፌሮች ቀደም ሲል ይሰሩት በነበረው ስራ ላይ ተሰማርተው የእለት ተእለት ፍጆታቸውን እንዲያሟሉ መንግስት ችግሩን እንዲፈታላቸው ሲጠብቁ ቆይተዋል። በሌላ በኩል የሲሚንቶ ችርቻሮ ነጋዴዎች በሲሚንቶ ገበያ ግብይት ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ለመቀጠል ወይም ሙሉ በሙሉ ወደ ሌላ ንግድ እንዲሸጋገሩ ውሳኔ ለማግኘት አሁንም እየጠየቁ ይገኛሉ። እነዚህን ችግሮች ለመፍታት መንግሥት ቃል የገባ ቢሆንም፣ በሲሚንቶ ንግድ ላይ ጥገኛ የሆኑ በርካታ ዜጎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በሚፈጥ ችግር መጓተት እንዳለ አዲስ ስታንዳርድ ያነጋገራቸው ሰዎች ይናገራሉ። እንደ አቶ ሃይለ አሰግድም መንግስት እየተባባሰ ለመጣው ከሲምንቶ ጋር ተያያዥነት ያለው ችግር አስቸኳዓይ መፍትሄ ሊሰጥ ይገባል ይላሉ።
የሲሚንቶ ምርትና ስርጭት መዛባት ከፈጠሩት ምክንያቶች አንዱ በሙስና የተዘፈቁ ባለስልጣናት የሚፈጥሩት እንደሆነ መንግስት በቅርቡ አስታውቋል። በቅርቡ የፍትህ ሚኒስቴር በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የኮንስትራክሽንና ሎጂስቲክስ ምክትል ዳይሬክተር በሆኑት በአቶ ተስፋዬ ደሜ እና በሌሎች ሶስት የሙስና ክስ መመስረቱን ይታወቃል። ባለስልጣናቱ ከ29,200 ኩንታል በላይ ሲሚንቶ በድርጅቱ ስም ከደርባን እና ከዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች በመግዛት በጥቁር ገበያ በውድ ዋጋ ይሸጣሉ በሚል ጥርጣሬ መከሰሳቸው ይታወቃል። አስ