ዜና: በአሶሳ ከተማ የምሽት ሰዓት እላፊ ገደብ ተጣለ

ረዳት ኮሚሽነር ቡሽራ አልቀሪብ ፡፡ ምስል፡ የ ቤንሻንጉል ክልላዊ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ

አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 4፣ 2014 ዓ.ም፦ በቤንሻንጉል ክልላዊ መንግስት መዲና አሶሳ ከተማ ጊዚያዊ የእንቅስቃሴ ገደብ መጣሉን የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ፡፡

የአሶሳ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ቡሽራ አልቀሪብ ለክልሉ መገናኛ ብዙሃን በሰጠት ጋዜጣዊ መግለጫ የሰዓት ገደቡ ከሃምሌ 01 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ እንደሚቆይም ተናግረዋል፡፡

ረዳት ኮሚሽነሩ የእንቅስቃሴ ሰዓት ገደቡን አስመልክተው ሲያብራሩም ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት ጀምሮ እሰከ ንጋቱ 12፡00 ሰዓት ሆቴሎች፣ ግሮሰሪዎች፣ መጠጥ ቤቶች እና ማናቸውም የንግድ ተቋማት አገልግሎት መስጠት የማይቻል መሆኑን የገለፁ ሲሆን ተሽከርካሪዎችን በተመለከተ የጸጥታ ስራ ከሚሰሩና የአምቡላንስ አገልግሎት ከሚሰጡ ውጭ ማንኛውም ተሸከርካሪ ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት በኋላ መንቀሳቀስ እንደማይፈቀድ ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም እግረኞች እስከ ምሽቱ 3፡00 ሰዓት ብቻ መንቀሳቀስ የሚቻል መሆኑን ገልጸው፣ ድንገተኛ ህመም ወይም መሰል ማህበራዊ ችግር ካጋጠመ በአቅራቢያው የሚገኙ የጸጥታ አካላትን በማስፈቀድ መንቀሳቀስ የሚቻል መሆኑን ተናግረዋል።

ረዳት ኮሚስነር ቡሽራ አክለውም ማህበረሰቡ የተጣለውን የሰዓት ገደብ እንዲያከብር እና “አጠራጣሪ ነገር” ሲያጋጥመውም ለጸጥታ ሃይሉ በመጠቆም ተባባሪ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።

አዲስ ስታንዳርድ በመዲናይቱ የተጣለውን ገደብ ምክንያት አስመልክታ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገችው ጥረት አልተሳካም። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.