አዲስ አበባ፡ህዳር 06/2015 ዓ/ም፦ በደቡብ አፍሪካ በተደረገው የሰላም ስምምነት ላይ ወልቃይት ወደ ትግራይ ይሁን ወደ አማራ ይሁን የሚል ስምምነት አለመደረሱንና አጠቃላይ ችግሩ የሚፈታው በህገ መንግስቱ መሰረት እንደሚሆን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ገለፁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን የተናገሩት በዛሬው እለት ከህዝብ ተወካዮች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አክለውም “ወልቃይት ብቻ አይደለም፤ ሰሜን ሸዋ ላይ ኦሮሚያ እና አማራ ጥያቄ አላቸው። እሱም ደቡብ አፍሪካ ይሂድ? ሲዳማ እና ወላይታ፤ ብላቴ ላይ ጥያቄ አላቸው። እሱም ደቡብ አፍሪካ ይሂድ? ቦታው አይደለም። የተስማማነው በኢትዮጵያ ህግ እና ስርዓት ይፈጸም ነው።”
የወልቃይት ህዝብ የሁለቱ ቋንቋ ተናጋሪ ሲሆን ለትግራይ እና ለአማራ ህዝቦች ድልድይ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የራሱን ጉዳይ ራሱ መወሰን እንዲችል እድል ካልተሰጠው ዘላቂ ሰላም አይመጣም ብለዋል፡፡ “ያ ህዝብ የራሱን ዕጣ ፈንታ እንዲወስን፤ ዲሞክራሲያዊ ዕድል እንዲያገኝ ማድረግ ከቻልን ብቻ ነው መፍትሔ የሚመጣው” ብለዋል።
አያይዘውም ጉዳዩን በሚመለከት ስለ ሕዝበ ውሳኔ ለሚነሱ ሓሳቦች ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ “ከአማራ ወገን ላለፉት 30 ዓመታት ብዙ ወልቃይቴዎች ሲፈናቀሉ፤ ሲሰደዱ ኖረዋል። እነሱ በሌሉበት ህዝበ ውሳኔ ቢባል፤ የተመናመነ ህዝብ ነው እና እንጎዳለን። በትግራይ በኩል አሁን በተፈጠረው ግጭት ብዙ ሰው ወጥቷል። ስለወጣ አሁን ባለው ቢወሰድ አማራ ክልል አድቫንቴንጅ ይወስዳል የሚሉ ስሞታዎች ይሰማሉ። ወልቃይቴ፤ ወልቃይቴ ነው፤ ይታወቃል። ከአድዋም የሄደ፤ ከደብረ ማርቆስም የሄደ ሰው ሊኖር ይችላል። ግን ወልቃይቴ ይታወቃል። አትላንታም ይኑር፣ አውስትራሊያም ይኑር፣ ጅማም ይኑር፤ ስለዚያ ቦታ ሀሳብ እንዲሰጥ ዕድል ካልተሰጠው በስተቀረ ዘላቂ ሰላም አያመጣም” ሲሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ከትግራይ ሃይሎች ጋር በደቡብ አፍሪካ የተፈራረመዉን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል ስር እየተዳደረ የሚገኘዉ በቀድሞ በትግራይ ምዕራባዊ ክፍል ይተዳደር የነበረዉ የወልቃይት እና አከባቢዉ ጉዳይ አነጋጋሪ ሆኖ ቆይቷል።
የሰላም ስምምነቱ ምዕራፍ 10 ቁጥር 4 የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸዉን አከባቢዎች ሁለቱ አካላት በህገመንግስቱ መሰረት ተነጋግረዉ ለመፍታት መስማማታቸዉን ይጠቅሳል።
“ይህን በህግ እና በስርዓት ብንፈጽም ለወልቃይት ይጠቅማል ለአማራ ይጠቅማል ለትግራይ ይጠቅማል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ከህገ መንግስት በፊት ህወሓት በግድ ስለወሰደ አሁን እኛ ደግሞ በግድ ወስደን፤ እዚያ ዘመኑን በሙሉ ወታደር ልናቆም አንችልም። በስምምነት ካልሆነ በወታደር ነው የሚሆነው። በወታደር ከሆነ ዘላቂ አይሆንም” በማለት ተናግሯል።
መንግስት ከህወሓት ጋር የተፈራረመውን የሰላም ስምምነት ተግባዊ ለማድረግ በታማኝነት በሙሉ አቅም መረባረብ ይኖርብናል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በስምምነቱ መሰረት ቃላችንን መጠበቅ እና ስምምነቱን በአግባቡ ወደ መሬት ማውረድ ይጠበቅብናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒሰትሩ የነበረው ጦርነት በተራዘመ ቁጥር የህዝቦች ስቃይ እየበዛ ስለሚሄድ በሰላም መቋጨት አትራፊ እንጂ አጉዳይ አይደለም ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒሰትሩ አያይዘውም አንዳንድ ሰላሙን የማይሹ ወገኖች የወልቃይትን ጉዳይ እያነሱ ስምምነቱ የተዛባ ትርጉም እንዲሰጥ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
የሰላም ስምምነቱ እንዲፈረም ድጋፍና ጥረት ላደረጉ ሁሉም ወገኖች ምስጋናቸውን ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒሰትር ዓብይ ባለፈው የተፈፀመን ስህተት መድገም አይኖርብንም በመሆኑም ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ ችግር ላይ ያሉን ወገኖችን መደገፍ የፈረሰን መገንባትና ወደ ነበረበት መመለስ የመንግስት ቀዳሚ ተግበር እንደሚሆን አብራርተዋል፡፡
ስለ ሀገሪቷ ኢኮኖሚ…
ጠቅላይ ሚኒሰትር አብይ የተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በርካታ ፈተናዎች የታዩበት ቢሆንም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ፈተናዎቹን በመቋቋም በ6 ነጥብ 4 በመቶ ማደጉንና በያዝነው የበጀት ዓመትም በ7 ነጥብ 5 በመቶ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የኢቲዮጵያ ኢኮኖሚ ኮሮና ድርቅ የእርስ በርስ ግጭትና በሩሲያና ዩክሬይን የተፈጠረው ጦርነት ቀላል የማይባል ጫና ያሳደሩበት ፈተና በመቋቋም የአገሪቱ አጠቃላይ ኢኮኖሚ 126 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር መድረሱንና የነፍስ ወከፍ ገቢም ወደ 1 ሺህ 2 መቶ 12 ዶላር ማደጉን ተናግረዋል፡፡
ግብርና በ 6 ነጥብ 1 በመቶ እድግት ያሳየ ሲሆን የስንዴ ሩዝ እና በቆሎ ምርቶች መጨመር በዋናነት ተጠቃሽ መሆናቸውን ገልፀው በዚህ ዓመት 4 ሺ የቡና ችግኞች በመተከላቸው የቡና ምርት በቀጣይ የ20 በመቶ እድገት እንደሚኖር ይታመናል ብለዋል፡፡
አግልግሎትን ለማሻሻል በተደረገው ጥረትም ባለፈው የተሌኮምና የሞባይል ባንኪንግ 25 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎችን የተሌ ብር ተጠቃሚ መሆኑን ገልፀው 40 የመንግስት ተቋማትም እና ከ200 በላይ የሚሆኑ የግል ድርጅቶችም የዲጂታል አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል ብለዋል፡፡ አስ