አዲስ አበባ፡ህዳር 5/2015 ዓ/ም፦ በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ወለጋ ዞን በጋሎ ቀበሌ ሙለታ ገላ ቤተክርስቲያን በአማኞች ላይ የተፈጸመውን ኢ-ሰብአዊ ግድያ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነየሱስ አወገዘች። ከቤተክሪስትያኗ ባለፈው ሳምንት ዐርብ ህዳር 02፣ 2015 በወጣዉ መግለጫ እንደተመለከተው በ15 አማኞቿ ላይ የተፈፀመውን ግድያ በማውገዝ ለሟች ቤተሰቦች እና ለቤተክርስቲያኑ አባላት መጽናናትን ተመኝቷል። የሟቾችን ስም ዝርዝር የያዘዉ መግለጫ እንደሚለዉ ጥቃቱ የተፈፀመው እሁድ ጥቅምት 27 ቀን 2022 ሲሆን የቤተክርስቲያኑ አባላት ለጸሎት በተሰበሰቡበት ወቅት መሆኑንም ጠቁሟል።
መግለጫው አያይዞም ወንጀሉን የፈፀሙት በአካባቢው የማይታወቁ የታጠቁ ሰዎች መሆናቸውን ገልጿል። ቤተ ክርስቲያኒቱ አያይዛም መንግስት አደጋው እንዳይፈፀም በመከላከልም ሆነ ከተፈፀመ በኋዋላ ምርመራ በማድረግ ወንጀለኞችን ለህግ ማቅረብ አለመቻሉ እንዳሳዘናት ቅሬታዋን አቅርባለች።
“በምንም አይነት ሁኔታ ለሰላማዊ ዜጎች ከለላ ማድረግ የመንግስት ግዴታ ነዉ” ያለዉ መግለጫው “መንግስት ሰላማዊ ዜጎች ለእርድ እየተዳረጉ በዝምታ የሚያልፈው ከሆነ ኃላፊነቱን የመወጣቱ ጉዳይ አጠያያቂ ነው” ብሏል። መግለጫው መንግስት እርምጃ አለመውሰድ ብቻ ሳይሆን የደረሰውን አደጋ በውል አላወገዘም ብሏል።
ጥቃቱ ከጸጥታ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ መልኩ የተከሰተ እንዳልሆነ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከአደጋው ከተረፉ ሰዎች እንዳረጋገጠች መግለጫው ጠቁሟል።
መግለጫው አክሎም ሌሎች 14 የ የቤተክርስቲያኒቱ አባላት መሪዎች እና አገልጋዮች በመንዲ ከተማ በተፈፀመ የአየር ጥቃት መገደላቸዉን ጠቅሷል።
“በመንዲ ከተማ ብቻ ከአምልኮ በኋላ ወደሰፈር በመመለስ ላይ የነበሩ በቁጥር 14 የሚሆኑ የቤተክርስቲያናችን ምዕመናን፣ መሪዎች እና የወንጌል አገልጋዮች ላይ የሞት አደጋ መድረሱ ተሰምቷል” ይላል መግለጫዉ።
አዲስ ስታንዳርድ በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ዞን በመና ሲቡ ወረዳ መንዲ ከተማ በአየር ድብደባ በርካታ ንፁሀን ዜጎች መሞታቸውን ዘግቦ እንደነበር ይታወቃል።
በመጨረሻም ቤተክርስቲያኗ የኢትዮጵያ መንግስት በኦሮሚያ ያሉ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት አበክሮ እንዲሰራ ስትል አሳሰበች። አስ