ዜና፡15ኛው የአውሳ ሱልጣን በአለ ሲመት በሱልጣኔቱ መናገሻ በአይሰኢታ ከተማ በደማቅ ሁኔታ ተካሄደ

አዲስ አበባ መጋቢት 4/ 2015 ዓ.ም፡ 15ኛው የአውሳ ሱልጣን አህመድ አሊሚራህ ሀንፈሬ በአለ ሲመት የሀገር ውስጥ፣ ከጎረቤት ሀገራት ከተለያዩ የአለማችን ክፍሎች የመጡ እንግዶች በተገኙበት በሱልጣኔቱ መናገሻ በአይሰኢታ ከተማ በዛሬው እለት በደማቅ ሁኔታ በዛሬው እለት መካሄዱን የአፋር ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።

በባህላዊ ስነ ስነስረአቱ መሰረት አልጋወራሽ ልኡል አህመድ አሊሚራህ የሱልጣንነት ልብስ በመልበስ 15ኛው የአውሳ ሱልጣን ሆነዋል።

በበአለ ሲመቱ የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ፣ የኢፌዴሪ የ ህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የፌደሬሽን ምክርቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ዛህራ ሁመድ፣ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ ሚኒስትሮች፣ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች፣የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የጂቡቲ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱልቃድር መሀመድ ካሚል እና ከፍተኛ አመራሮቻቸው፣ የሀይማኖት አባቶች ከ 3ቱም ማዕዘናት የመጡ ሱልጣኖች:-የራሀይይቶ ሱልጣኔት ሱልጣን፣ የጎባአድ ሱልጣኔት ሱልጣን፣ የጊሪፎ ሱልጣኔት ሱልጣን፣የተጎሪ ሱልጣኔት ሱልጣን፣ የጎሳ መሪዎች፣ ከተለያዩ የአለማችን ክፍሎች የመጡ ዲያስፖራዎች፣ ከጁቡቲ ከኤርትራና ከአፋር ክልል ሁሉም ዞኖች የተለያዩ አካባቢዎች ከሶስቱም ማዕዘን የመጡ የማህበረሰብ ተወካዮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።

በበአለ ሲመቱ እንግዶች ለሱልጣኑ የእንኳን ደስ አለዎት መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ባስተላለፉት መልእክት የአፋር ህዝብ ከጥንት ጀምሮ ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ ዛሬ ላይ የደረሱ በርካታ የዳበሩና የደረጁ ዘርፈ ብዙ ቱባ የባህል እሴቶች ባለቤት መሆኑን አውስተው ከነዚህ ውስጥ አንድኛው እና ተጠቃሹ የተለያዩ የህዝብ አስተዳደር እና የፍትህ ስርአት ያለው፣ በሀገር በቀል እውቀት የተገነባ መድዓ የተሰኘ ሁሉም የአፋር ህዝብ የሚተዳደርበት ፍትሀዊ፣ ከዘመናዊነት ቀድሞ የዘመነ ስርአት ያለው ህዝብ ነው ብለዋል።

እነዚህ የተደራጁ እና የዘመ’ኑ ቱባ ባህሎቹ ተጠብቀው ትውልድን እየጠቀሙ ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፉ በተለያዩ የአፋር ጫፎች ያሉ ስልጣኔቶች ትልቅ ሚና እንዳላቸው ገልፀው ከነዚህ ሱልጣኔቶች አንዱ የሆነው የአውሳ ሱልጣኔት የአፋር ህዝብ ራስን በራሱ እንዲያስተዳድር፣ በተለያዩ ቦታዎች ተከፋፍሎ የነበረው ህዝብ በአንድ ክልል እንዲደራጅ፣ ዘመናዊ ትምህርት ወጣቱ ተሳታፊ እንዲሆን ስኮላርሺፕ በሌሎች ሀገሮች በማመቻቸት፣ የተለያዩ የዲፕሎማሲ ስራዎችን በመስራት ለአፋር ህዝብ ብሎም አጠቃላይ ለኢትዮጵያችን ትልቅ የሆነ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን ተናግረዋል።

አቶ አወል አርባ ባስተላለፉት መልእክት “ስለ አፋር ሱልጣን ስናነሳ ሁሌም ከልባችን የማይጠፉት “ባንዲራችንን እንኳን እኛ ግመሎቻችንን ያውቋታል” በሚለው ዘመን ተሸጋሪ ንግግራቸው የባንዲራንና የሀገርን ፍቅር ያስተማሩ የተከበሩ ሱልጧን አለሚራህ ሀንፈሬ አሁንም ማውሳት ግድ ይላል ብለዋል።

ሱልጣን አሊሚራህ ሀንፈሬ በሁሉም አቅጣጫ የሚገኘውን የአፋር ህዝብ ያስተሳሰሩ፣ በኢትዮጵያ አንድነትና ሉአላዊነት ፅኑ እምነት የነበራቸውና የኢትዮጵያን የግዛት እና የህዝብ ህብረ ብሄራዊ አንድነት እንዲከበር፣ እንዲጠነክርና የሰው ልጅ ሰው በመሆኑ ብቻ የተከበረ መሆኑን በተግባር ያሳዩ፣ የዱንያን ነገር ችላ ያሉ፣ በኢባዳ የበረቱ እና ሌሎችም እንዲበረቱ ያለፉ ታላቅ መሪ እንደነበሩ አውስተዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ባስተላለፉት መልእክታቸው በሀገራችን በተለያዩ ዘርፎች እየተመዘገበ ያለው ውጤት በተወሰነ አካል ብቸኛ ጥረት ሳይሆን መንግስት፣ ህዝብ፣ ባለሀብቶች፣ የመንግስት አመራር፣ የተለያዩ ባህላዊ የአመራር ስርአቶችና አደረጃጀቶች ትልቅ ሚና እንደበረው አውስተው ወደፊትም አጠናክረን በምናስቀጥለው የልማት እና እድገት ስራችን እንደ አንድ ሰው ልብ በመሆን እጅ ለእጅ በመያያዝ ሁሉም ዜጋ በባለቤትነት ስሜት መረባረብ ያሻል ብለዋል።

አያይዘውም በመተባበርና አንድ በመሆን ልዩነቶችን በማክበር ህብረ ብሄራዊ አንድነታችን አጠናክረን ከቀጠልን ሁሌም የምናስበውና የምናልመው፣ ዕቅድ የምናወጣለትና ሰፊ ጥረት የምናደርግለት የተሻለች፣ የበለፀገችና ያበበች፣ ደስተኛ ዜጎች ያላት ሀገርን መፍጠር እንችላለን በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.