ዜና፡ 85.9 በመቶ የሚሆኑት አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና 70.9 በመቶ የሚሆኑት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከሚጠበቀው “ደረጃ በታች” መሆናቸውን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት/15 2015 .ም፡በኢትዮጵያ ካሉ አጠቃላይ 47 ሺህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 85.9 በመቶ የሚሆኑት አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች “ፍጹም ከደረጃ በታች” መሆናቸው እና 70.9 በመቶ የሚሆኑት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ደግሞ ከሚጠበቀው “ደረጃ በታች” ላይ እንደሚገኙ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ። አጠቃላይ ካሉ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚፈለገውን ከፍተኛ ደረጃ ያሟሉ ት/ቤቶች “አራት” ብቻ ናቸው ሲል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስታውቋል፡፡

የትምህርት ሚንስቴር ትላንት ግንቦት 15፤ 2015 የዘጠኝ ወር የስራ አፈጻጸም ሪፖርቱን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበበት ወቅት አክሎ እንደገለፀው በ2015 ዓመት የሁሉም የፊደራል ሰራተኞች የትምህርት ማስረጃ ትክክለኛነት እንደሚረጋገጥም አስታውቋል፡፡

በኢትዮጵያ ባሉ አጠቃላይ 47 ሺህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ በተደረገ ግምገማ መሰረት የሚፈለገውን ከፍተኛ ደረጃ ያሟሉ ት/ቤቶች “አራት” ብቻ መሆናቸውን ይህም ካሉት አጠቃላይ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ያላቸው ድርሻ  0.001 በመቶ ባቻ መሆኑን ሚንስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገልፀዋል፡፡ የተቀሩት ትምህርት ቤቶች “የተጠበቀውን ደረጃ ያላሟሉ ናቸው” ተብሏል፡፡

ትምህርት ሚኒስቴር የእነዚህ ትምህርት ቤቶችን ደረጃ እና ጥራት ለማሻሻል እስካሁን 8,700 ገደማ ትምህርት ቤቶች ጥገና እና እድሳት እንደተደረገላቸም መገለፁን ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ዘግቧል፡፡

ከትምህርት ጥራት ጋር በተያያዘ፤ በትምህርት ሚኒስቴር በተደረገ ሌላ ጥናት መሰረትም ዘንድሮ ፈተናዎችን ከወሰዱ የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች ውስጥ፤ ከግማሽ በላይ ውጤት ያመጡት 12 በመቶው ብቻ እንደሆኑ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ለፓርላማ አባላቱ አስረድተዋል። ከአራተኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል ደግሞ ከግማሽ በላይ ያመጡት 20 በመቶው እንደሆኑ ገልፀዋል።

“በአጠቃላይ ካሉ 47 ሺህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ወደ 99 በመቶ የሚሆኑት፤ ለተማሪዎች፣ ለልጆች አመቺ ሁኔታ የላቸውም” ያሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ “የትምህርት ግብአት በበቂ አለመኖር” እንዲሁም “የትምህርት ቤቶች መሰረተ ልማት ጥሩ አለመሆን” በትምህርት ጥራቱ ላይ ተፅዕኖ ካደረጉ ጉዳዮች መካከል መሆናቸውን ፕሮፌሰሩ ተናግረዋል፡፡

የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ጨምሮ ወላጆች፣ የቀድሞ ተማሪዎች እና መምህራንን የሚያሳትፍ፤ ሀገር አቀፍ የትምህርት ዘመቻ በአንድ ወር ተኩል ጊዜ ውስጥ ይፋ እንደሚያደርግም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስታውቋል። 

ከዚህ በተጨማሪም ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት 18 ሽህ የትምህርት ማስረጃዎች ውስጥ 921 (አምስት በመቶዎቹ) ህገ-ወጥ መሆናቸውን መስሪያ ቤቱ አስታውቋል፡፡ ቀጣሪ ተቋማት ለሚንስቴሩ ይረጋገጥልን ብለው ባቀረቡት ጥያቄ ደግሞ 225 የትምህርት ማስረጃዎች ተመርምረው 40 በመቶዎቹ ሀሰተኛ ሆነው መገኘታቸውንም ተገልጿል።

ከመስሪያ ቤቱ የሁሉም የፊደራል ሰራተኞች የትምህርት ማስረጃ ትክክለኛነት እንደሚረጋገጥም አክሎ መግለፁን አል አይን የዜና ወኪል ዘግቧል፡፡

ይህን በተመለከተ ፕሮፌሰር ብርሃኑ፣”በሁሉም የፌደራል ተቋማት የሰራተኞችን ማህደር መመርመር ጀምረናል። ምን ያህሉ እውነተኛ የትምህርት ማስረጃ ይዞ ነው? ምን ያህሉ አይደለም የሚል ምርመራ እያካሄድን ነው፤ ከራሳችን ጀምረን። ማህበረሰቡ ልክ እንደፈተናው [የ12ተኛ ክፍል ፈተና] እንዲያውቅልን የምንፈልገው ከአሁን በኋላ በተጭበረበረ ድግሪ፤ በተጭበረበረ ዲፕሎማ የሚሰራ ስራ አይኖርም የሚለውን ለማሳወቅ ነዉ። በዚህ ዓመት እሱን እንጨርሳለን ብለን እናስባለን” ብለዋል።

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.