አዲስ አበባ፣ታህሳስ 12/2015 ዓ.ም፡ – የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ኮሚቴ (ሲፒጄ) ማክሰኞ ታህሳስ 11 ቀን 2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ “የኢትዮጵያ ፖሊስ የኦንላይን ጋዜጠኛ መስከረም አበራን ከለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈታና የፕሬስ አባላትን ማስፈራራት ማቆም አለበት” ሲል አሳሰበ።
የፌደራል ፖሊስ የኢትዮ ንጋት በይነ መረብ ሚዲያ መስራች እና ባለቤት የሆነችውን መስከረም አበራ ታህሳስ 4 ቀን 2015 ዓ.ም በቁጥጥር ስር ያዋላት ሲሆን ፖሊስ ጋዜጠኛዋ በማህበራዊ ገፅ እና ኢትዮ ንቃት በተሰኘ የራሷ ሚዲያ ህግ መንግስታዊ ስርዓትን ለመናድ፣ ብሔርን ከብሔር ለማጋጨትና በመከላከያ ሰራዊት ላይ እምነት እናዳይኖር ለማድረግ እንዲሁም በአዲስ አበባ የኦሮሚያ መዝሙርና ባንዲራ ጉዳይ ላይ እና በጉራጌ ዞን በተነሳው ግጭት ላይ ቅስቀሳ በማድረግ ወንጀል መጠርጠሯን ለፍርድ ቤት ማስረዳቱን ጠበቃዋ አቶ ሰለሞን ገዛሀኝ ለአዲስ ስታንዳርድ ገለፀዋል፡፡
መስከረም ታህሳስ 6 ቀን 2015 ዓ.ም የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ችሎት የቀረበች ሲሆን በችሎቱም የፌድራል ፖሊስ ክስ ለመመስረት ይረዳው ዘንድ ወደ ጉራጌ ዞን በማምራት የሰው ምስክር ለማሰባሰብ የጠየቀውን ተጨማሪ 14 የምርመራ ቀን ፈቅዷል ሲሉ ጠበቃው አክለው ገልፀዋል፡፡
“መስከረም በመንግስት እስራት ሳምንታትን አሳልፋለች፤ ከስራዋ ጋር በተያያዘ እንደገና መታሰሯ በጣም ያሳዝናል” ሲሉ የሲፒጄ ከሰሃራ በታች የአፍሪካ ተወካይ ሙቶኪ ሙሞ ተናግረዋል። “የኢትዮጵያ ባለስልጣናት መስከረምን በአስቸኳይ እንድትፈታና በእሷ ላይ የቀረበውን የወንጀል ክስ ማቋረጥ እንዲሁም ካለምንም ጣልቃ ገብነት ስራዋን እንድትቀጥል ሊፈቅድ ይገባል” ብለዋል ሙተኪ።
መስከረም አበራ ግንቦት 12/ 2014 ዓ.ም በፀጥታ ሀይሎች በቁጥጥር ስር ውላ የነበር ሲሆን፣ ፖሊስ “ሁከትና ብጥብጥ በማስነሳት እና የፌደራል መንግስት እና የአማራ ክልልን ለመነጠል ገንዘብ ተከፍሏት እንደምትሰራ” ጠርጥሬያታለሁ ማለቱ ይታወሳል፡፡ በኋላም ፍርድ ቤቱ የቀረበባት ክስ የዋስ መብት የማያስከለክል በመሆኑ በ 30 ሺ ብር ዋስ ከእስር እንድትፈታ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ መስከረም ሰኔ 6 /2015 ዓ.ም ከተፈታች በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ታህሳስ 4 ቀን 2015 ዓ.ም ዳግም ታስራለች፡፡ አስ