ዜና፡ ፕሬዘደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ከኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ጋር ተወያዩ ፤  “ዘር እና ሃይማኖትን” ለፖለቲካ ጥቅም ማዋል “ቀይ መስመርን መተላለፍ ነው” አሉ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 7/ 2015 ዓ.ም፡- ፕሬዘደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን  ፓትሪያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አቡነ ማትያስን ጨምሮ የቤተክርስቲያኒቷን መሪዎችን ካነጋገሩ በኋላ ሰኞ የካቲት 6 ቀን 2015 ዓ.ም በማኅበራዊ  ትስስር ገጾቸው  ባሰፈሩት መግለጫ  “ዘር እና ሃይማኖትን ለፖለቲካ ጥቅም ማዋል ቀይ መስመርን መተላለፍ ነው” አሉ።

 “የሰው ልጅ በህይወቱ፣ በስራው፣ በማህበራዊ ኑሮው ድንበር ከሌለው እራሱ የአደጋ ምንጫ ነው” ሲሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከገጠማት  ወቅታዊ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ሀሳባቸውን ገልፀዋል፡፡

ፕረዝዳንቷ በምእመናን እና በፀጥታ አካላት መካከል በጠፈጠረው ግጭት ለጠፋው ሕይወት ሀዘናቸውን ሲገልፁም “እምነታችን ለእኛ አማኞች የመጨረሻ ምሽጎቻችን ናቸው፡፡ ብርታት፣ተስፋና ፅናት ይሰጣሉ” ሲሉ ገልፀዋል፡፡

ፕሬዘደንት ሳህለ ወርቅ የሃይማኖት ጉዳይ ለቤተ እምነቶች፣ ለእምነት አባቶችና አምእመናን መተው አለባቸው ያሉ ሲሆን አንዲጠበቁና ከጥቃት እንደከላከሏቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡ አክለውም “ጥንቃቄ፣ ብልሃት፣ጥበብ፣የሰከነ አእምሮ፣ እርጋት፣ አርቆ አስተዋይነት  የችግሮች መፍቻ ዘዴዎች ናቸው” ብለዋል፡፡

ፕሬዝዳንቷ  የተደረጉትም ይሁን ያልተደረጉት የሀገር ፅኑ መሰረት የሆኑና ለድርድር የማይቀርቡ ያሏቸውን  “የዜጎች መሰረታዊ መብቶች፣ የህግ የበላይነት፣ለህግ ተገዢነት፣ ተጠያቂነት፣ የሀሳብ ነፃነት፣ መረጃ የማግኘት መብት ለአደጋ እንዳይጋለጡ መጠንቀቅ ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡

«ከነበርንበት መከራ ወጥተን ሳናበቃ ፣ በሀገርና በህዝብ ላይ የደረሱ በርካታ ስብራቶችን ሳንጠግን ፣ ሕይወት የሚቀጥፉ ግጭቶችን ሳናስወግድ ፣ በርካታ ዜጎቻችን በተፈናቀሉበት ፣ በሚሊዮኖች የሰብአዊ ዕርዳታ በሚሹበት ተመካክረን ተግባብተን ከመሥራት ሌላ አማራጭ አይታየኝም » ሲሉም ፕረዝዳንት ሳህለወርቅ አክለው ገልፀዋል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.