ዜና፡ ከኢትዮጵያ ፌዴራል ጦር ጋር አንድ ሁነን ተባብረን በመዋጋታችን ትልቅ ልምድ እና ትምህርት ቀስመናል ሲሉ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ገለጹ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 6/ 2015 ዓ.ም፡- ከኢትዮጵያ ፌዴራል ጦር ጋር አንድ ሁነን ተባብረን በመዋጋታችን ትልቅ ልምድ እና ትምህርት ቀስመንበታል እንዲሁም በቀጠናው ሰላም ለማስፈን ጥሩ ተሞክሮችን ተለዋውጠናል ሲሉ የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ተናገሩ።

የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ  ይህን ያሉት በኢትዮጵያ በሰሜኑ ክፍል በተለይም በትግራይ ላይ ስለተካሄደው ጦርነት እና ተያያዠ ጉዳዮች ላይ ከሀገሪቱ መንግስት ቴሌቭዥን ጣቢያ ጋር ትላንት ባደረሁት ቃለምልልስ ነው።

ጦርነቱ ምንም አይነት አላማ ሳይኖረው በህወሓት እና ዘዋሪዎቹ የዋሽንግተን አካላት የተለኮሰ ነው ሲሉ ፕሬዝዳንቱ በተደጋጋሚ ገልጸዋል። በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የሚፈጠር ሰላም ለዋሽንግተን ትልቅ ራስ ምታት ነው ሲሉም ተናግረዋል። ህወሓቶች አቅማቸውን አያውቁም፤ እነሱን የሚይዟቸው እና የሚያሽከረክሯቸው የዋሽንግተን ቡድንም ከነሱ የባሱ ናቸው ሲሉ የተደመጡት ፕሬዝዳንቱ የዋሽንግተን የተሳሳተ ስሌት ለህወሓት የልብ ልብ ሰጥቶታል ብለዋል።

በመጀመሪያው እና ሁለተኛው ዙር ጦርነት ወቅት የነበሩ ልምዶችን አቀናጅተን፤ ሉአላዊነት የሚለውን ጉዳይ ወደ ጎን ትተን፤ ተዋህደን (ከኢትዮጵያ ጦር ጋር) ነው ወደ ጦርነት የገባኑት ያሉት አቶ ኢሳያስ ወደ ጦርነቱ የገባነው የህወሓት ፉከራ እና ፀብ አጫሪነት አላርፍ ስላለ ነው፤ ሀገራችን፣ መሬታችን፣ ህዝባችን፣ አከባቢያችን ሰላም ማግኘት ስላለበት ነው ሲሉ በምክንያትነት ዘርዝረዋል። የህወሓት ዝርዝር የጦርነት እቅድ ትንንሹንም እቅድ ጨምሮ እጃችን ላይ ስለነበረ ወረራችን ለመመከት ሊያስቸግረን አይችልም ሲሉ ገልጸው እናም ቀጠናውም ሰላም እንዲያገኝ የሶስተኛ ዙር ጦርነቱን እንደ መልካም እድል መጠቀም ነበረብን ብለዋል።

በፕሪቶርያ ስለተደረሰው ስምምነት በተመለከተ ፕሬዝዳንቱ እንዳስታወቁት የህወሓት ተወካዮች በአሜሪካ የጦር አውሮፕላን ከመቀሌ ወደ ጅቡቲ ተጓዙ፣ ከጅቡቲ ወደ ፕሪቶርያ ሄዱ፣ ከዚያም ወረቀት ተሰጥቷቸው ይህንን ወረቀት ፈርሙ ተባሉ። ሁሉንም የጨረሰችው ዋሽንግተን ነች ብለዋል። ኦባሳንጆ፣ ኡሁሩ የአፍሪካ ህብረት አጃቢዎች ነው የነበሩት፤ ወረቀቱ አልቆ የተሰጣቸው በዋሽንግተን ነው ሲሉም ተደምጠዋል።

የፌደራል መንግስቱ እና ህወሓት የሰላም ስምምነት በመፈጸማቸው ለእኛ የሚያሳስበን ነገር የለም፤ መፈራረማቸው ጥሩ ነው፤ ስምምነቱ ወደ ተግባር ተለውጦ ሳናይ የምንሰጠው አስተያየት የለም ብለዋል። ስምምነቱን ተግባራዊ ከማድረግ ይልቅ የተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ዘመቻ በማካሄድ ህወሓቶች እና ላኪዎቻቸው ተጠምደዋል ሲሉ አስታውቀዋል።

ኤርትራ ከትግራይ አልወጣችም፣ ኤርትራ ሰው እየገደለች ነው የሚሉ የስምምነቱን ተግባራዊነት ለመጎተት የሚነገር ነገር አለ ያሉት አቶ ኢሳያስ ይህ የዋሽንግተን የተለመደ ተግባር ነው፤ ነገሩን በማጓተት ሌሎች የብጥብጥ እድሎች እንዲፈጠሩ እድል ለመስጠት ነው፤ ግዜ ለመግዛት እየተጣረ ነው ሲሉ ኮንነዋል።

በተደጋጋሚ ህወሓት የብጥብጥ አመለኛ ነው ሲሉ የኮነኑት ኢሳያስ አፈወርቂ ይህን አመሉን ስለማይተው በየዋህነት አጠቃላይ ሁኔታው ተጠናቋል ወይንም እልባት አግኝቷል ማለት አይቻልም ሲሉ ገልጸዋል።

አመል የማይለቅ ቢሆንም የመጨረሻው ዙር ጦርነት ትምህርት ሊሆናቸው ይችላል ያሉት ፕሬዝዳንቱ ስንት መቶ ሺ ሰው ሞተ?፣ ስንቱ ቆሰለ? ሲሉ ጠይቀው ጉዳቱ በየትኛውም የአለም ክፍል ታይቶ አይታወቅም ብለዋል። አላማ እና ግብ የሌለው ጦርነት ነው የተካሄደው በማለት በተለይም ህወሓትን ተጠያቂ ያደረጉት ኢሳያስ በርካታ ህዝብ በማስጨረሳቸው እና ውድመት በማስከተላቸው ተጠያቂነት ሊኖር ይገባል ብለዋል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.