ምስል- አሚኮ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20/2015 ዓ.ም፡- ጥቂት የሚባሉ አንቂዎች ማህበራዊ ሚዲያውን በመጠቀም የአማራ ህዝብና መንግስት ማኀበራዊ እረፍት እንዳይኖራቸው በሃሰት መረጃ የጥፋት መንገድን በመከተል ላይ ይገኛሉ ሲል የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ፡፡
ቢሮው ይህን ያለው በአማራ ክልል ከትላንት ሰኔ 19 ጀምሮ ለሶስት ቀን የሚቆይ ሰልፍ ይካሄዳል የሚል መረጃ በማህበራዊ ሚዲያ መሰራጨቱን ተከትሎ ነው፡፡
የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ በመግለጫው በስም ለይቶ ያለገለፃቸው አካላት ከአማራ ህዝብ ማኀበራዊ መስተጋብር ፣ ሞራልና እሴት ባፈነገጠ መንገድ የግል ጥቅማቸውን ብቻ በመመልከት ኃላፊነት በጎደለው መንገድ ህዝቡ በሰላም ወጥቶ እንዳይገባ ማኀበራዊ እንቅስቃሴውን ለመግታት የሐሰት መረጃ በማሰራጨት በህዝብ ውስጥ ሁከት፣ ብጥብጥና ትርምስ እንዲፈጠር አልመው እየሰሩ ይገኛሉ ብሏል።
በማከልም አንቂዎቹ የህዝብንና የመንግስትን ግንኙነት ጥርጣሬ ውስጥ የሚጥሉ አፍራሽ እንቅስቃሴዎች ላይ በመጠመድ የአማራ ህዝብን ማኀበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዞ ወደ ኋላ የሚጎትት አሉታዊ ተግባር በመስራት ላይ መሆናቸውን አስታውቋል፡፡
ሀይሎቹ የአማራ ህዝብ ወኪልና ተቆርቋሪ በመምሰል የግል ጥቅማቸውን እንዳይነጥፍ የሃሰት መረጃ በማስራጨት ቢዝነስ ላይ የተጠመዱ ናቸው ያለው ቢሮው መንገድና የንግድ ተቋማት አዘግተው ህዝብ በሰላም እጦት ወደ አመጽና ሁከት በመቀስቀስ ወደ አደባባይ ወጥቶ ስርዓት እንዲፈርስ አስበው የሚንቀሳቀሱ ናቸው ብሏል።
ይህ ደግሞ የክልሉን ኢኮኖሚ በእጅጉ ከመጉዳት ያለፈ ለአማራ ህዝብ አንድ ጠብታ እሴት የሚጨምር ባለመሆኑ ህዝቡ በተሳሳተ መረጃ ሳይወናበድ ትክክለኛ የመረጃ ምንጮችን እንዲጠቀም አሳስቧል።
የተሳሳተ መረጃ የሚሰጡ የዲጂታል ማኀበራዊ ሚዲያዎችም የአማራን ህዝብ ከድጡ ወደ ማጡ ከሚገፋ እኩይ ዓላማ እንዲቆጠቡ አሳስቧል፡፡
የአማራ ክልል የጸጥታ ኃይል ማለትም የፖሊስ፣ ሚሊሻና የማረሚያ ቤት አደረጃጀት የሰው ኃይል ቁመናና ስምሪት ከመቸውም ጊዜ በላይ በተሻለ ደረጃ መደራጀቱን የገለፀው መግለጫው የዜጎችን ሰላምና ደህንነት በማረጋገጥ በክልሉ ውስጥ የተጀመረው የልማት እንቅስቃሴ ያለ ስጋት እንዲተገበር ሁሉም ዜጋ በቁርጠኝነት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪውን አቅርቧል። አስ