አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 20/2015 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ታላቁ የጎረቤት ሱዳን ህዝብ ሰላም ይገባዋል ሲሉ ገልጸው ከሀገሪቱ ተፋላሚ ሀይል መሪዎች ጋር በስልክ ማውራታቸውን አስታወቁ። ጠ/ሚኒስትሩ በትዊተር የማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ ከሁለቱ ተፋላሚ ሀይሎች መሪዎች ጀነራል አብዱል ፈታህ አልቡርሃን እና ከጀነራል መሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ ልዩነቶቻቸውን በመፍታት የሱዳንን ሰላም ማምጣት በሚቻልበት ጉዳይ ዙሪያ መወያየታቸውን አስታውቀዋል።
በተያያዘ ዜና 50 ሀገራት ዜጎቻቸውን ከሱዳን ለማስውጣት በሚያደርጉት ጥረት ኢትዮጵያ ድጋፍ እንድታደርግ በይፋ መጠየቃቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማስታወቁ ተገልጿል። በሱዳን ቀውስ ሳቢያ የተለያዩ ሀገራት ዜጎችን የማስውጣት ስራ ጋር በተያያዘ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ለተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች ማብራሪያ መስጠታቸውም ተጠቁሟል። ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር በአየር እና በየብስ ዜጎችን ለማስወጣት ጥረት መደረጉን ሚኒስትር ዴኤታው መግለጻቸውን እና በማብራሪያው ፕሮግራም ላይ የተካፈሉ አምባሳደሮም በሱዳን ሁሉም ወገን ወደ ሰላማዊ አማራጭ እንዲመጣና አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ያሉ የውጭ ሀገራት ዜጎችን በማስወጣት ስራ ላይ ኢትዮጵያ እየተጫወተች ያለውን ሚና በማድነቅ ምስጋና ማቅረባቸውን ፋና አስነብቧል።
በሌላ ዜና በሱዳን የዩናይትድ ኪንግደም አምባሳደር የሆኑት ጊለስ ሊቨር ስራቸውን በአዲስ አበባ በሚገኘው የሀገሪቱ ኤምባሲ ሁነው በመስራት ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል። የብሪታንያ መንግስት የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በድረገጹ እንዳስነበበው በካርቱም የሚገኘው የብሪቴይን ኤምባሲ ለጊዜው መዘጋቱን ተከትሎ ጊለስ ሊቨር የሀገራቸውን የዲፕሎማሲ ስራዎች እና ጥረቶች አዲስ አበባ ሁነው እንደሚያግዙ አመላክቷል።