ዜና፡ ጋዜጠኛ መዓዛ መሃመድ በዋይት ሃውስ ከሚሸለሙ 11 የአመቱ “ብርቱ አለም አቀፍ ሴቶች ሽልማት” ተሸላሚዎች አንዷ መሆኗ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 28/ 2015 ዓ.ም፡–  ሮሃ ሚዲያ” የተሰኘው የዩቲዩብ መገናኛ ብዙኃን መስራች እና ባለቤት የሆነችው ጋዜጠኛ መዓዛ መሐመድ በዋይት ሃውስ ከሚሸለሙ ከአስራ አንድ የአመቱ “ብርቱ አለም አቀፍ ሴቶች ሽልማት” (IWOC) ተሸላሚዎች ውስጥ አንዷ መሆኗ ተገለጸ።

መአዛ መሃመድ ከተመረጡት አስራ አንድ ብርቱ አለም አቀፍ ሴቶች ተሸላሚዎች አንዷ ሆና በመመረጧ በነገው እለት ሮብዕ የካቲት 29 ቀን 2015 ዓ.ም በነጩ ቤተመንግስት  የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን እና የሃገሪቱ ቀዳማዊ እመቤት ጂሊ ባይደን በሚገኙበት የሽልማት ስነስርአት ሽልማቱ እንደሚበረከትላት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃላ አቀባይ ቢሮ መግለጫ አመላክቷል።  

ለአስራ ሰባተኛ ግዜ የሚከናወነው ሽልማት ዋነኛ አላማ በአለም ላይ ራሳቸውን ለአደጋ በማጋለጥ እና መስዋዕትነት በመክፈል በተለየ መልኩ ድፍረትን፣ ጥንካሬን እና ብልህ አመራርን ተላብሰው ለሰላም፣ ለፍትህ፣ ለሰብዓዊ መብት እና ለሴቶች እኩልነት የሰሩ ሴቶች እውቅና ለመስጠት ያለመ መሆኑ ተጠቁሟል።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃላ አቀባይ ቢሮ መግለጫ እንዳመላከተው ጋዜጠኛ መአዛ መሃመድ ለሽልማት ያበቃት በመሰረተችው ሮሃ ሚዲያ” የተሰኘው የዩቲዩብ መገናኛ ብዙኃን የምታስተላልፋቸው መረጃዎች እና የወሰደቻቸው መስዋዕትነት መሆኑን ገልጿል። በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በተካሄደው ጦርነት ወቅት የጾታዊ ጥቃት ሰለባዎችን በማናገር እና ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግ ያካተቱ ዘገባዎችን መስራቷን መግለጫው አስታውቋል።

በሰሜኑ ጦርነት የተደፈሩ በርካታ ሴቶችን በማቅረብ ቃለምልልስ ማካሄዷን የጠቆመው መግለጫው በጦርነቱ ወቅት የተፈጸሙ ወንጀሎች እንዲጣሩ እና  ወንጀል የፈጸሙ ሰዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ ትታገል እንደነበር አትቷል። ይህ አቋሟ እና ደፋር ውሳኔዋ ከውጭ ሁነው የሚመለከቷትን ለመማረክ በቅታለች ሲል አወድሶ ያየቻቸውን እውነቶች አለም እንዲያውቀው ያሳየችውን ጽናት አድንቋል።

ከዩኒቨርስቲ ታግተው ስለተወሰዱ 17 ሴት ተማሪዎች የሰራችውን ዶክመንተሪ ያወሳው መግለጫው ይህ ሁሉ ስኬቷ የተገኘው ከበርካተ ውጣ ውረዶች ጋር በመጋፈጥመሆኑን አስታውቋል።

ሮሃ ሚዲያ” የተሰኘው የዩቲዩብ መገናኛ ብዙኃን መስራች እና ባለቤት የሆነችው ጋዜጠኛ መዓዛ መሐመድ በተደጋጋሚ ለእስር መዳረጓ የሚታወቅ ሲሆን ለመጨረሻ ጊዜ ለእስር የተዳረገችው ጷጉሜ 2፤ 2014 ዓ.ም ከቀኑ 11 ሰዓት ገደማ በሽሮ ሜዳ አካባቢ በግብይት ላይ ባለችበት ወቅት በፌደራል ፖሊስ አባላት ነው፡፡

መዓዛ ለመጀመሪያ ጊዜ የታሰረችው በጥቅምት ወር ላይ ታውጆ በነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት ባለፈው ታህሳስ ወር ላይ ነበር። ፖሊስ መዓዛን “ሁከት እና ብጥብጥ የሚያነሳሱ መልዕክቶችን በማስተላለፍ” እንደጠረጠራት በወቅቱ ቢገልጽም፤ ጋዜጠኛዋ አንድም ጊዜ ችሎት ፊት ሳትቀርብ ለአንድ ወር ገደማ በእስር ላይ ከቆየች በኋላ ተፈትታለች።

መዓዛ ለሁለተኛ ጊዜ የታሰረችው ከሶስት ወራት በፊት ባለፈው ግንቦት ወር ውስጥ ነበር። መዓዛ በዚህኛውም እስር የተጠረጠረችው በተመሳሳይ “ሁከት እና ብጥብጥብ በማነሳሳት ወንጀል” ሲሆን ለ20 ቀናት ገደማ በእስር ላይ ቆይታ በሰኔ ወር አጋማሽ ላይ በ10 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር መፈታቷ ይታወሳል።

ለመጨረሻ ጊዜ ለእስር የተዳረገችው ጷጉሜ 2፤ 2014 ዓ.ም ከቀኑ 11 ሰዓት ገደማ በሽሮ ሜዳ አካባቢ በግብይት ላይ ባለችበት ወቅት ሲሆን ጥቅምት 3 ቀን 2015 ዓ.ም በ10 ሺህ ብር ዋስ ከእስር ተፈታለች፡፡ አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.