ትንታኔ፡ አዲስ የተመሰረተው የሸገር ከተማ ኃላፊዎች ህገ-ወጥ መኖሪያ ቤቶችን ያለ አንዳች ማስጠንቀቂያ ማፍረስ ቀጥለዋል፤ ድርጊቱ የብሄር አድሎ እንደሌለው ይገልፃሉ

በሸገር ከተማ አስተዳደር በለገጣፎ ለዳዲ አርባ አራት አካባቢ የፈረሱ ቤቶች

አዲስ አበባ፣ የካቲት 27/2015 ዓ.ም፡-የኦሮምያ ክልል መንግስት በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ ከተሞችን አስተሳስሮ” ሸገር ከተማ አስተዳደር” በሚል ስያሜ ከመሰረታቸው  ውስጥ አንዱ በሆነው በለገጣፎ ለገዳዲ አከባቢ የሚገኙ በርካታ ቤቶች በመፍረስ ላይ ይገኛሉ። የክልሉ መንግስት በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ ከተሞችን አንድ ላይ በማዋቀር ሸገር ከተማ የሚል ስያሜ በመስጠት በመሰራታቸው ከተሞች በተለምዶ “የጨረቃ ቤቶች” የሚባሉ መኖሪያ ቤቶች መገንባት ከጀመሩ ከሁለት አስርት አመታት በላይ ተቆጥሯል። ግንባታዎቹን ተከትሎም መሰረታዊ አገልግሎቶች ተዘርግተው ተጠቃሚ ሁነዋል። ይሁን እንጂ አብዛኛዎቹ ቤቶች ህጋዊ የግንባታ ማረጋገጫ ሰነድ የላቸውም። በዚህም ሳቢያ ከቅርብ አመታት ወዲህ የቤት ፈረሳ ዜና መስማት እየተለመደ መጥቷል። ባለፉት ሁለት ሳምንታት በተለይ በለገጣፎ ለገዳዲ አከባቢ የሚገኙ በርካታ ቤቶች በመፍረስ ላይ ይገኛሉ። አብዘሃኛዎቹ ከአስር አመታት በላይ ቤቶቹን ገንብተው መኖራቸውንም ይገልጻሉ። አዲስ ስታንዳርድ በቦታው በመገኘት ይህንኑ ለማረጋገጥ ችላለች።

የፈረሰ ቤቱ በር ላይ ያገኘነው መሃመድ ካሳ የተባለ የለገጣፎ አከባቢ አርባአራት ተብሎ በሚጠራ ቦታ ነዋሪ ቤቴ እንደ ሚፈርስ ቢነግሩኝ ምንኛ መታደል ነበር ሲል ገልጾ ማስጠንቀቂያ ሰጥተውን ቢሆን አስበንበት፣ ተዘጋጅተን አንዳንድ ነገሮችን እናመቻች ነበር በማለት ቁጭቱን ለአዲስ ስታንዳርድ አጋርቷል። የሁለት ልጆች አባት መሆኑን እና ባለቤቴ የሰባት ወር ነፍሰጡር መሆኗን የገለጸልን መሃመድ ቤቱን ከአከባቢው አርሶ አደሮች በመግዛት በ2004 ዓ.ም እንደሰራው ነግሮናል።

በአከባቢው የተከልናቸው ባህርዛፎች በእጅ ሊታቀፉ በማይችሉበት ደረጃ በቅለዋል ሲል በአከባቢው የኖረበትን ዘመን በማስረጃነት የጠቀሰልን መሃመድ ካሳ ይሄ እራሱ ብዙ ይናገራል ይላል። በጣም ያመመን፣ የተሰማን እና የከፋን ብሔር ተኮር መሆኑ ነው፤ ከየትም ይምጡ፣ ትላንትም ይምጡ ዛሬም ይምጡ፤ ከጋምቤላም ይሁን፣ ከአሶሳም ይምጡ፣ ከሰሜን ሽዋም ቢሆን የአንድ የኦሮሞ ቤት አልፈረሰም ሲል ቤት ፈረሳው ማንነት ላይ ያተኮረ ነው ሲል በምሬት ገልጿል። በሚስት ወይም በባል የኦሮሞ ብሔር አባል ከሆንክ ቤትህ እንዲፈርስ አይደረገም ሲል ሁኔታውን አብራርቷል።

እኔ ኦሮሞ ነኝ፣ የቤት መፍረሱ ሰለባም ነኝ ሲል የገለጸልን ጌታቸው የተባለ የአከባቢው ነዋሪ በበኩሉ ቤት ፈረሳው ማንነት ላይ ያተኮረ ነው መባሉ የሚኮነን ነው ሲል ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጿል። በአከባቢው ተገኝተን የፈረሰበትን ቤት የጣሪያ ቆርቆሮ አስጪኖ ሲሄድ ያገኘነው ጌተቸው በአከባቢው ቦታውን ገዝቶ መኖር ከጀመረ አስር አመት እንደተጠጋው አስታውቋል። እንደሌሎቹ ሁሉ ቤቱ ከመፍረሱ በፊት ምንም አይነት ማስጠንቀቂያም ይሁን ውይይት ከአከባቢው የመንግስት ሃላፊዎች ጋር እንዳልነበረ አስታውቋል።

በቦታው ተገኝተን ባደረግነው ቅኝት በርካታ ቤቶች ቆርቆሯቸው ተነስቶ፣ በራቸው ምንም አይነት መዝጊያ የሌለው እንዲሁም ቤቶቹ ውስጥም ምንም አይነት እቃ የሌላቸው ሁነው አይተናቸዋል።

ቤቱን የገዛችው ከአስራ አንድ አመት በፊት ባለቤቴ ነበረች ሲል የገለጸልን ከድር አሊ የተባለ ወጣት የለገጣፎ ለገዳዲ አርባአራት አከባቢ ነዋሪ በበኩሉ ሲጀመር የጤና መድህን ክፈሉ አሉን፣ ከፈልን፣ እኛ ነዋሪ ነን ብለን ሁሉንም ስናደርግ ነበር፤ እነሱ ግን እያዘናጉ ነበር ያኖሩን ሲል ብሶቱን አጋርቶናል። እኔ ወጣት ስለሆንኩ ችግሩን እቋቋመዋለሁ ተሯሩጬ እኖራለሁ ሲል ገልጾ ቤተሰብ ያላቸው ልጆቻቸው ትምህርት የጀመሩ ግን ያሳዝናሉ፤ ልጆቻቸው ትምህርታቸው ተቋርጦ ተበትነዋል ብሏል። አናስፈርስም ያሉት ላይ ድብደባ ተፈጽሟል፤ በአከባቢው ከጸጥታ ሀይሎች ጋር በተፈጠረው ረብሻ አንዲት ሴት በጥይት ተመትታ በመቁሰሏ ህክምና እየተከታተለች ትገኛለች ሲል በቦታው የተፈጸመውን ሁኔታ አጋርቶናል። እንደ መሃመድ ካሳ ሁሉ ከድር አሊም ቤት የማፍረሱ እርምጃ ብሔርን መሰረት ያደረገ ነው የሚል እምነት ነው እንዳለው ለአዲስ ስታንዳርድ አስታውቋል። ቦታው ለልማት ተፈልጓል ብለው ሁሉንም ቢሆን ያፈረሱት አያመኝም፤ ድንገት መጥተው ነው ያፈረሱብን ሲል በምሬት ገልጿል።

እዛ አከባቢ ቤት ሰርተው የሚኖሩ ሁሉም ገዝተው የገቡ ናቸው ሲል የነገረን መሃመድ ካሳ ከልጅነት እስከ እውቀት ያፈራናትን ሁሉ ነው እዛው ላይ(ቤታችን) ያፈሰስነው ብሏል።

የሸገር ከተማ የለገጣፎ ለገዳዲ ክፍለ ከተማ የመንግስት ሃላፊዎችን አስተያየት አዲስ ስታንዳርድ ያደረገችው ጥረት ባለስልጣናቱ ስልክ ባለማንሳታቸው ምክንያት ሊሳካ አልቻለም። ይሁን እንጂ የለገጣፎ ለዳዲ ክፍለ ከተማ ከንቲባ ዶ/ር ተሾመ አዱኛ በጉዳዩ ዙሪያ በአንከር ኢትዮጵያ በተሰኘ የዩትዩብ ቻናል ቀርበው በሰጡት ምላሽ የሸገር ከተማ እየወሰደ ያለው እርምጃ ከተማን ከማሳደግ እና ህገወጥነትን ከማስወገድ ጋር የተያያዘ ብቻ ነው ሲሉ ገልጸዋል። በቀጣይም ህገወጥ ቤቶችን የማፍረሱ እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። ህገወጥነትን ከሰብአዊነት ጋር ማያያዝ ተገቢ አይደለም ሲሉም ገልጸዋል። ማንነት መሰረት ያደረገ ማፈናቀል ነው መባሉንም ያጣጣሉት ከንቲባው መስፈርታችን ህገወጥነት ብቻ ነው ብለዋል። ቤት ከፈረሰባቸው የአከባቢው ሰዎች ጋርም በቂ ውይይት ተደርጓል ሲሉ አስተባብለዋል።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.