ዜና፡ ጋዜጠኛ መዓዛ መሀመድ እና ደራሲ አሳዬ ደርቤ ከእስር ተፈቱ፤ ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ የዋስትና መብቱ ታገደ

ጋዜጠኛ መዐዛ መሃመድ ደራሲ አሳየ ደርቤ እና ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ.፡፡ ፎቶ፡ ከቪዲዮ የተወሰደ

በብሩክ አለሙ @Birukalemu21

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4/2015 ዓ.ም፡-ጋዜጠኛ መዓዛ መሀመድ እና ደራሲ አሳዬ ደርቤ በትናንትናው እለት እያንዳንዳቸው በ10 ሺህ ብር ዋስ ከእስር የተፈቱ ሲሆን ዛሬ በዋለው ችሎት ግን ጠቅላይ ፍርድ ቤት የጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይን የዋስትና መብት ማገዱን ጠበቃ ሄኖክ አክሊሉ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናገሩ፡፡

የአማራ ድምጽ የበይነ መረብ ሚዲያ ባለቤትና ምስራች ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ በ 20 ሺህ ብር ዋስትና እንዲፈታ ተወስኖ ከሀገር እንዳይወጣ እግድ ስላለበት ከኢሚግሬሽን ጋር ያለው ሂደት እስኪጠናቀቅ ትናንት ከእስር ሳይለቀቅ የቀረ ሲሆን ዛሬ በዋለው ችሎት ዓቃቤ ህግ ይግባኝ በመጠየቁ የተፈቀደው የዋስትና መብት ታግዶ ክርክሩን ለመስማት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለጥቅምት 11 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል ሲሉ አቶ ሄኖክ አክለው ገልፀውልናል፡፡

“ሮሃ ሚዲያ” የተሰኘው የዩቲዩብ መገናኛ ብዙኃን መስራች እና ባለቤት የሆነችው ጋዜጠኛ መዓዛ መሐመድ  እና ደራሲ አሳዬ ደርቤ ከእስር የተፈቱት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዋስትና ከፈቀደላቸው ከአንድ ሳምንት በኋላ ነው።

ባለፈው ሳምንት አርብ መስከረም 27 ቀን በዋለው ችሎት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ የወንጀል ችሎት ለሶስቱም ተከሳሾች በዋስ እንዲፈቱ ወስኖ የነበር ቢሆንም ሳይፈቱ መቆየታቸውን የገለፁት ጠበቃ ሄኖክ ፖሊስ  “የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዓቃቢ ህግ ይግባኝ ስለሚል እኛ ልንለቃቸው አንችልም” በማለት የፍርድ ቤቱን ትእዛዝ ሳይፈፀም በመቅረቱ ለአንድ ሳምንት በእስር ላይ እንዲቆዩ ተደርጓል ብለዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ተከሳሾች ባለመፈታታቸው የፌደራል ፖሊስ የፀረ-ሽብር ወንጀል ምርመራ ክፍል ኃላፊ ኮሚሽነር ተስፋዬ አሽኔ እና አጠቃላይ የፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ኃላፊ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ ለትናንት ጥቅምት 3 ቀርበው የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ተፈጻሚ ባለማድረግ ተከሳሾቹ ያልተፈቱበትን ምክንያት ቀርበው እንዲያስረዱ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር።

ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ የታዘዙት ኮሚሽነር ተስፋዬ እና ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ ችሎቱ ላይ ባይቀርቡም ትናንት አመሻሽ ላይ መዓዛ መሀመድ እና አሳዬ ደርቤ እንዲፈቱ አድርገዋል ሲል አቶ ሄኖክ ገልፀዋል፡፡

የፌዴራል ዐቃቤ ህግ በጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ፣ ጋዜጠኛ መዐዛ መሃመድ እና ደራሲና አክቲቪስት አሳዬ ደርቤ ላይ   የሃሰት ወሬን ነዝተዋል፣ በውጊያ ውስጥ የወገን ጦር አሰላልፍና ቦታን ለጠላት እና ለህዝብ አሳውቀዋል በሚል እና በሌሎች ወንጀሎች መስከረም 20/2015 ዓ.ም. ክስአንደተመሰረተባቸውይታወሳል፡፡

በዚህ መሰረትም አንደኛ ተከሳሽ በሆነው ጎበዜ ሲሳይ፤ Amhara Perspective ተብሎ የተከፈተ የቲዉትር አካዉንት ላይ በቀን 26/12/2014 ቀርቦ ባደረገዉ ንግግር “ጠቅላላ ህዝቡ የሀገር መከላከያ ሰራዊትን የማይደግፍ ይልቁንም ህወሃት ወደ አዲስ አበባ እንዲመጣ የሚፈልግ እና የሚደግፍ እና ወጣቱ ከመንግስት ጎን መሰለፍ የማይፈልግ” አድርጎ በማቅረብ ሰራዊቱ በአካባቢዉ ያለ ህዝብ አይደግፈኝም ብሎ እንዲያስብ በማነሳሳት በህዝብና እና በሰራዊት መካከል ያለዉን መልካም ግንኙነት የሚጎዳ እሳቤ እንዲኖር የሰራ፣ የመንግስት የመከላከል አቅም ላይ ህዝቡ ያለዉን አቋም የሚያፈርስ መረጃ እስተላፏል ሲል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ክስ መስርቶበታል፡፡

በተጨማሪም ነሃሴ 30/2014 ዓ.ም በፌስቡክ ገፁ “የሃገር መከላከያ ሰራዊቱ እና ጥምር ጦሩ የት አካባቢ እንዳለ እና የት አካባቢ ሳይዝ እንደቀረ” በፅሁፉ በመግለፅ በዉጊያ እንቅስቃሴ ዉስጥ የወገን ጦር አሰላለፍ እና ቦታ ከፍተኛ ቁምነገር ሆኖ መያዝ የሚገባዉን ለጠላት እና ለህዝቡ በማጋራት ወንጀል በአጠቃላይ ሶስት ተደራራቢ ክሶች እንደተመሰረተበት ተገልጿል፡፡

ሁለተኛ ተከሳሽ አሳዬ ደርቤ እና 3ኛ ተከሳሽ መዐዛ መሃመድ በተመለከተም 2ኛ ተከሳሽ አሳዬ ደርቤ የሃሰት ወሬዎችን 3ኛ ተከሳሽ መዐዛ መሃመድ በምታስተዳድረዉ በሮሃ ሚዲያ ለማህበረሰብ በማድረስ እና የሃሰት ወሬዎች እንዲሰራጩ በማድረግ ወንጀል በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የተደራጁ እና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጄኔራል ዐቃቤ ሕግ ክስ መስርቶባቸዋል፡፡

ተከሳሾቹ በሮሃ ሚዲያ አማካኝነት ነሃሴ 19/2014 ዓ.ም ባደረጉት ቃለ ምልልስ በወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አቅም እና ስልቶች ምክንያት የሚወሰኑ ዉሳኔዎችን ፍፁም ሃሰት በሆነ መንገድ በመቀየር መንግስት ሆነ ብሎ ህወሃት ሲዳከም ጥቃት የሚያቆም እና እንዲጠናከር እድል የሚሰጥ፣ ለማሸነፍ ፍፁም ፍላጎት የሌለዉ አድርጎ በማቅረብ የሃሰት ወሬዎችን በመንዛት ወንጀል ክስ ተመስርቶባውቸዋል፡፡

ሮሃሚዲያ” የተሰኘው የዩቲዩብ መገናኛ ብዙኃን መስራች እና ባለቤት የሆነችው ጋዜጠኛ መዓዛ መሐመድ ረቡዕ ጷጉሜ 2፤ 2014 ዓ.ም በፌደራል ፖሊስ አባላት ተይዛ መታሰሯን አዲስ ስታንዳርድ መዘገቧ ይታወሳል።

የመአዛ እስር የጸጥታ ሃይሎች “የአማራ ድምጽ” የተባለውን ሌላኛውን የዩቲዩብ ሚዲያ ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይን በድጋሚ ካሰሩት ከሰዓታት በኋላ ነው። መአዛ ለሶስተኛ ጊዜ በቁጥጥር ስር ስትውል የጎበዜ እስር ከብዙ ወራት በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት በዋለው ችሎት ፖሊስ ሁለቱንም በሽብርተኝነት ወንጀል መጠርጠራቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል። ፖሊስ ሁለቱንም ጋዜጠኞች ከህወሓት ከፍተኛ አመራር ጋር በተለያየ መንገድ ግንኙነት እያደረጉ እና ተልዕኮ ተቀብለዋል ሲል ከሷል።

ጎበዜ ሲሳይ

የአማራ ድምጽ የብይነ መረብ ሚዲያ ባለቤትና ምስራች ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ጳጉሜ 2፣ 2014 ዓ.ም በፌደራል ፖሊስ ተይዞ በድጋሜ መታሰሩ ይታወቃል። በእለቱ ማለዳ 2 ሰዓት ላይ የፌደራል ፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሱና ሲቪል በለበሱ የደህንነት ሰዎች መያዙን ታናሽ ወንድሙ አቶ ከድር ሲሳይ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል

የየኛ ቲቪ የበይነ መረብ ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ እሁድ ከሚያዝያ 23 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ለዘጠኝ ቀናት ወደማይታወቅ ቦታ በጸጥታ ሃይሎች ከተወሰደ በኋላ ግንቦት 1 ከምሽቱ ሶስት ሰዓት አካባቢ ከእስር ተፈትቶ ነበር።

ጎበዜ ሲሳይ ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ሚያዝያ 23 ቀን 2014 ዓ.ም የዒድ በዓል ዋዜማ ላይ በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ አያት አካባቢ ተብሎ ከሚጠራው ቦታ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ መወሰዱን ገልጿል። መጀመሪያ መታወቂያቸውን ለማሳየት ፈቃደኛ ያልነበሩና ማንነታቸውን ለመግለጽ ያልወደዱ 7 እና 8 የሚጠጉ ሲቪል ልብስ የለበሱ የጸጥታ ሃይሎች ወደ ቤቱ ገብተው ለምርመራ እንደሚፈለግ ነግረው እንደወሰዱት የተናገረው ጋዜጠኛው፣ “አይኔን ጨፍነው አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ወዳልታወቀ ቦታ ወሰዱኝ” ብሏል። ከታሰረበት ጊዜ ጀምሮ ፍርድ ቤት እንዳልቀረበም አስረድቷል።

ጋዜጠኛ ጎበዜ የአማራ ክልል የጸጥታ ሃይል እና ፌዴራል ሃይል በጋር በመሆን ከትግራይ ሃይል ጋር የተቀሰቀሰው ወታደራዊ ግጭት ከቀጠለ በኋላ ወደ አማራ ክልል ተጉዞ ነበር። በፌስቡክ ገፁ ላይ ገዥውን የብልጽግና ፓርቲ ተችቷል። ጎበዜ በግል የፌስቡክ ገፁ ላይ “የአማራ ሕዝብ በተለይ ከትግራይ ክልል ጋር የሚዋሰነው ህዝብ ጦርነት ሰልችቶኛል ፣ መንግስት በይደር በሚተወው ጦርነት በየአመቱ እያገረሸ ለሞትና ለስደት ዳርጎኛል ። ጦርነት አንፈልግም ዝመቱም አትበሉን የሚል አርሶ አደር አለ።” ሲል ፅፏል፡፡

ዩቲዩብ ላይ ባደረገው ቃለ ምልልስ የአማራ ህዝብ መጪውን የሰላም ቀን እንደሚመኝ በመግለፅ እንዲሁም በፌስ ቡክ ገፁ ላይ ያሰፈረው ተመሳሳይ ይዘትን በማስተጋባት የሰነዘረው ትችት የመንግስት ደጋፊ በሆኑ አክቲቪስቶች ከፍተኛ ቅሬታ ቀስቅሷል። “አንተን መንግስት አይደለም የሚከስህ ህዝብ ነው:: የኢትዮጵያ ህዝብና መከላክያ ሰራዊት:: በህይውቴ እንደ አንተ አይነት ለቃሉ ይቅርታ <<ቆሻሻ>> ሰው አይቼም ሰምቼም አላውቅም:: እኔ በግሌ እንተን በኢትዮጵያ ስም እፋረድሃለሁኝ!!“ የሚል ትችት አክቲቪስቱ የትዊተር ገፅ ላይ ተለጥፏል፡፡

መአዛ መሃመድ

መአዛ መሃመድ ሂሳዊ አስተያየቷን የምታቀርብበት ሮሃ ሚዲያ የጎበዜን መታሰር ከዘገቡ ሚዲያዎች አንዱ ነው። መአዛ ራሷ ከመታሰሩ ከጥቂት ሰአታት በፊት በትዊተር ገጿ ላይ አዲስ መረጃ ለጥፋለች።

ሮሃ ሚዲያ” የተሰኘው የዩቲዩብ መገናኛ ብዙኃን መስራች እና ባለቤት የሆነችው ጋዜጠኛ መዓዛ መሐመድ ረቡዕ ጷጉሜ 2፤ 2014 ዓ.ም ከቀኑ 11 ሰዓት ገደማ በሽሮ ሜዳ አካባቢ አብረው በግብይት ላይ ባሉበት ወቅት በፌደራል ፖሊስ አባላት ተይዛ መወሰዷን የስራ ባልደረባዋ እና ጓደኛዋ ምስራቅ ተፈራ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግራ ነበር

በዕለቱ የነበረውንም ሁኔታ ምስራቅ ለአዲስ ስታንዳርድ ያስረዳች ሲሆን ጋዜጠኛዋ በፖሊሶች ከመያዟ በፊት፤ አንድ ሲቪል የለበሰ ሰው መታወቂያዋን እንድታሳየው ጠይቋት ነበር” ያለች ሲሆን አክላም መዓዛ “ለምንድን ነው መታወቂያ የማሳይህ?” የሚል ምላሽ እንደሰጠች ተናግራለች። ጥያቄውን ያቀረበው ግለሰብ መታወቂያ ማውጣት ሲጀምር፤ ሁለት የፌደራል ፖሊስ መለዮ የለበሱ የጸጥታ አካላት ወደ እነሱ መምጣታቸውን ምስራቅ ተናግራለች።

ጋዜጠኛ መዓዛ እየተገባደደ ባለው 2014 ዓ.ም. ለእስር ስትዳረግ የአሁኑ ለሶስተኛ ጊዜ ነው። መዓዛ ለመጀመሪያ ጊዜ የታሰረችው በጥቅምት ወር ላይ ታውጆ በነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት ባለፈው ታህሳስ ወር ላይ ነበር። ፖሊስ መዓዛን “ሁከት እና ብጥብጥ የሚያነሳሱ መልዕክቶችን በማስተላለፍ” እንደጠረጠራት በወቅቱ ቢገልጽም፤ ጋዜጠኛዋ አንድም ጊዜ ችሎት ፊት ሳትቀርብ ለአንድ ወር ገደማ በእስር ላይ ከቆየች በኋላ ተፈትታለች።

መዓዛ ለሁለተኛ ጊዜ የታሰረችው ከሶስት ወራት በፊት ባለፈው ግንቦት ወር ውስጥ ነበር። መዓዛ በዚህኛውም እስር የተጠረጠረችው በተመሳሳይ “ሁከት እና ብጥብጥብ በማነሳሳት ወንጀል” ሲሆን ለ20 ቀናት ገደማ በእስር ላይ ቆይታ በሰኔ ወር አጋማሽ ላይ በ10 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር መፈታቷ ይታወሳል።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.