በብሩክ አለሙ @Birukalemu21
አዲስ አበባ፣ የካቲት 16/ 2015 ዓ.ም፡- የካቲት 8 በወልቂጤ ከተማ በውሃ እጥረት ምክኒያት ጄሪካን ይዘው ሰላማዊ ሰልፍ በወጡ የከተማዋ ነዋሪዎች ላይ የፀጥታ ሃይሎች ጥቃት ማድረሳቸውን ተከትሎ ተቋርጦ የነበረውን እንቅስቃሴ በተመለከተ በሽማግሌዎች፣ በሃይማኖት አባቶች፣ በከተማ አስተዳደሩ ውይይት ተደርጎ የተከማው ማህበረሰብ ቅድመ-ሁኔታዎችን በማስቀመጥ ከአንድ ሳምንት በኋላ ወደ መደበኛ እንቂስቃሴ መግባቱን የውይይቱ ተሳታፊዎች ለአዲስ ስታንዳርድ ገለፁ፡፡ በተደረገው ውይይትም የደቡብ ክልል ልዩ ሀይል ከወልቂጤ ከተማ ለቆ እንዲወጣ አቅጣጫ ተሰጥቷል ብለዋል፡፡
በትላንትናው እለት በተደረገው ውይይት በፀጥታ ሃይሎች ለተገደሉተና ለቆሰሉ መንግስት ሀላፊነት ወስዶ ለህዝቡ ይፋ ከላደረገ ማህበረሰቡ ወደ ሌላ ንግናቄ እንደሚገባ ቅድመ-ሁኔታ አስቀምጦ ወደ እንቅስቃሴ መመለሱን የውይይቱ ተሳታፊ የሆነው ሀይደር ሙራድ ተናግሯል፡፡
የከተማዋ ከንቲባም የክልሉ ልዩ ሀይል ከተማዋ ላይ እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን ሀይደር ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጧል፡፡ “ ከተማዋ በህዝባዊ ሰራዊትና በፖሊስ ጥበቃ እንዲደረግለት፣ የከፋ የፀጥታ ችግር ካለ የሀገር መከላከያ ሰራዊት እንጂ ልዩ ሃይል ገብቶ ምንም አይነት እንቅስቃሴ እናዳያደርግ ህዝቡ ባስቀመጠው ቅድመ-ሁኔታ መሰረት የከተማዋ ከንቲባ ጉዳዩን ከሚመለከተው አካላት ጋር በማውራት አቅጣጫ እንደሚያስቀምጡ ቃል ገብተዋል” ብሏል፡፡
ሌላኛው የከተማዋን ወጣቶች በመወከል ከከተማ አስተዳደሩ፣ሰላም ኮሚቴ፣ ሀገር ሽማግሌዎች ጋር በተደረገው በውይይት የተሳተፈው አንድነት፣ የካቲት 8 በፀጥታ አካላት የተወሰደውን እርምጃ የከተማው አስተዳደር ሃላፊነቱን እወስዳለው ማለቱን ጠቅሶ ጥቃቱን ያደረሰው ልዩ ሀይሉ ከከተማው ይውጣ በተባለው መሰረት አባላቱ በተወሰነ መልኩ ከከተማዋ ወጥቶ ወደ ካምፕ መግባቱን ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጧል፡፡
የካቲት 8 በነበረው ሰላማዊ ሰልፉ በክልሉ ልዩ ሃይል በተወሰደ እርምጃ 6 ሰዎች መሞታቸውን አዲስ ስታንዳርድ ዘግባለች፡፡ የኢትዮጵያ ሰበዓዊ መብቶች ኮሚሽን በቡሉ የሟቾቹ ቁጥር ሶስት መሆኑን ባወጣው ሪፖርት ገልጧል፡፡ ይህን በተመለከተም ምላሽ የሰጠው ሀይደር የሟቾች ብዛት ስድስት መሆኑን ገልፆ ለኮሚሽኑ ማስረጃ ስለተላከለት የማስተካከያ መግለጫ ያወጣል ብለን እንጠብቃለን በማለት አስረድቷል፡፡
እንደ ሀይደር ገለፃ ኢሰመኮ ባወጣው መግለጫ የሟቾቹ ብዛት ሶስት መሆኑን የገለፀው ቀደም ብለው የሞቱት ሶስት ወጣቶች ሪፖርት ስለደረሰው ነው፡፡ ሆስፒታል ከገቡ በኋላ ተጨማሪ ሶስት ሰዎችን በመሞታቸው በአጠቃላይ ስድስት ሰዎች ናቸው ብሏል፡፡
ሀይደር አያይዞም ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች የተወሰኑት ወደ አዲስ አበባ ሪፈር ተፅፎላቸው በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል እና ጴጥሮስ ሆስፒታል ከፍተኛ የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ጠቅሷል፡፡
የጥቃቱ መንስዔ የሆነው የውሃ እጥረት በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ መሻሻል መኖሩንም አንድነት ተናግሯል፡፡ አክሎም ጥቃቱ እንዲፈፀም ዝዕዛዝ የሰጠውን አካል የማጣራት ስራ ለማከናወን ለመጪው ቅዳሜ መቀጠሩን ተናግሯል፡፡
የከተማዋ እንቅስቃሴ በተመለከተም “ማህበረሰቡ ወደ እንቅስቃሴ ቢገባም ቀዝቀዝ ያለ ድባብ ነው ያለው፡፡ ትምህርት ቤቶች እና የመንግስት መስሪያ ቤቶች ቢከፈቱም ሙሉ ለሙሉ ወደ ስራ አለተገባም” በማለት ገለጧል፡፡
የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ.ም. በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ ውስጥ ውሃ እጥረት ችግር ምክኒያት ጄሪካን ይዘው ሰላማዊ ሰልፍ በወጡ የከተማዋ ነዋሪዎች ላይ የፀጥታ ሃይሎች በከፈቱት ተኩስ 6 ሰዎች ሲሞቱ ከ15 ሰዎች በላይ ላይ በጣም ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን የከተማዋ ነዋሪዎችን ዋቢ በማድረግ ለአዲስ ስታንዳርድ መዘገቧ ይታወቃል፡፡
ከህዳር 16 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ የጉራጌ ዞን በተደረጃ ኮማንድ ፖስት እንዲመራ መወሰኑ ይታወቃል፡፡ የክልሉ ልዩ ሃይል፣ የፌድራል ፖሊስ እና ሌሎችም የፀጥታ አካላትን ጨምሮ በቅንጅትና በተደራጀ መንገድ በዞኑ ውስጥ እየተፈጠረ ያለውነን የፀጥታ ችግር እንዲፈታ መወሰኑን የደቡብ ክልል ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ሀላፊ አቶ አለማየሁ ባውዲ በእለቱ መግለፃቸው ይታወሳል፡፡አስ