ዜና፡ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ከህዳር 26 ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ የስራ ማቆም አድማ ሊያደርጉ መሆኑን አስታወቁ

በብሩክ አለሙ @Birukalemu21

አዲስ አባበ፣ ህዳር 17/ 2015 ዓ.ም፡ – በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች በመስራት ላይ ያሉ መምህራን እና ቴክኒካል ረዳቶች ለትምህርት ሚንስቴር እና ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በፃፉት ደብዳቤ መሰረት ከህዳር 26 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ላልተወሰነ ጌዜ የስራ ማቆም አድማ እንሚያደርጉ አስታወቁ።

አዲስ ስታንዳርድ በጉዳዩ ላይ ያነጋገራቸዉ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ጥያቄያቸው ስላልተመለሰላቸው ወደዚህ ዓይነት ውሳኔ እንደደረሱ ይናገራሉ፡፡

የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ማህበር ፕሬዘዳንት ፍቅረስላሴ አካሉ  እንደዚህ ዓይት ውሳኔ ላይ የተደረሰው አጠቃላይ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ኃላቲዎች ውይይት ካደረጉ በኋላ መሆኑን ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል፡፡ ስራ የማቆሙ ሃሳብ ሁሉም መምህራን የሚጋሩት ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ በቀጣይም የዩኒቨርሲቲዎች መምህራን ማህበር መግለጫ እንደሚያወጣ ተናግረዋል፡፡

የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ መምህር ጥላሁን ረጋ በበኩላቸው የመምህራኑ ደሞዝ አነስተኛ በመሆኑ በአገሪቱ ያለውን የኑሮ ውድነት መቋቋም እንዳልተቻለ ይናገራሉ፡፡ በሁለተኛ ዲግሪ ደረጃ ላሉ መምህራን የሚደርሳቸው የተጣራ ደሞዝ  8 ሺህ 5 መቶ ብር ብቻ ነው ያሉት መምህሩ  እንዲሻሻልልን የጠየቅን ቢሆንም እስካሁን ድረስ አልተመለሰልንም ብለዋል፡፡

መንግስት የመምህራንን ጥያቄ ባለመመለሱና ችላ  በማለቱ በትምህርት ጥራቱ ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ እያደረሰ ነው ያሉት መምህር ጥላሁን ከምስራቅ አፍሪካ በኢኮኖሚ ትልቅ ሆና ለመምህራን ዝቅተኛ ደሞዝ የምትከፍል ሀገር ኢትዮጵያ ብቻ መሆኗን አስገንዝበዋል፡፡ መምህር ጥላሁን አያይዘውም  የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ መምህራን በሙሉ ስራ ለማቆም ዝግጁ መሆናቸውን ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል፡፡

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የዲላ ዩኒቨርሲቲ መምህር  በበኩላቸው  የመምህራን ማህበር ለጥያቄዎቻችን ትኩረት መስጠት ባለመቻሉ ከሁሉም ዩኒቨርሲቲ የተውጣጡ መምህራን ተመካክረንበት ዩኒቨርሲቲ መምህራን እና ቴክኒካል ረዳቶች በኩል መግለጫችንን ይፋ አድርገናል ብለዋል፡፡

መምህራን ወር በደረሰ ቁጥር የቤት ኪራይ ምን እከፍላለሁ ልጆቼን ምን አበላለሁ እያለ በመጨናነቅ ለማስተማር በቂ ዝግጀት ስለማያደርግ የትምርት ጥራቱ ላይ ተፅኖ እያደረሰ ነው ይላሉ፡፡

መምህራኑ በፃፉት ደብዳቤ እንዳሰፈሩት የመነሻ ደመወዝ ማነስ፣ የአገልግሎት ጭማሪ አለመደረግ፣ ወቅቱን የሚመጥን ከታክስ ነጻ የሆነ የቤት ኪራይ አለማግኘት፣ የሶስተኛ ዲግሪ የምርምር ገንዘብ መጠን በቂ አለመሆን፣  የትርፍ ሰዓት ክፍያዎች አለመስተካከል እና  የደረጃ ዕድገት መቋረጥ በሚመለከት እንዲሻሻል ጠይቀዋል።

የስራ ማቆም አድማው የሚካሄደው ላልተወሰነ ጊዜ መሆኑንም በደብዳቤው ሰፍሯል፡፡ 

መንግስት የዩኒቨርሲቲ መምህራን ጥያቄ አለመመለሱ ለትምህርት ጥራት የተሰጠው ትኩረት እጅግ አናሳ መሆኑን በግልጽ ያሳያል ያሉት መምህራኑ የኢትዮጵያ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ክትትል እንዲያደርጉ በማሳሰብ ጥያቄዎቹ ካልተመለሱልን ከህዳር 26/2015 ዓ.ም ጀምሮ ምንም አይነት የመማር ማስተማር ሂደት እንደማይኖር አስታውቀዋል፡፡

የመምህራን ማህበር ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሐምሌ 27 ቀን 2014 ዓ.ም. በፃፉት ደብዳቤ ለዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ እና ቴክኒካል ረዳቶች የተሰራውን አዲሱን የስራ ደረጃ ማሻሻያ ተገቢነት እንደሌለው እና የፕሮፌሰር ማዕረግ ላላቸው መምህራን የተሻሻለ ነገር አለመኖሩንም ይጠቁማል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በሐምሌ ወር 2011 ዓ.ም የፌዴራል መንግስት ሰራተኞች የስራ መደቦች ምዘና የደረጃዎች ምደባና የደመወዝ ስኬል ደንብ በዩኒቨርሲቲ መምህራን ላይ ተፈፃሚ ባለመደረጉ ቅሬታ ተሰምቶናል ብለዋል፡፡

የትምህርት ሚንስቴር የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አመለወርቅ ህዝቅኤልን በጉዳዩ ላይ ለማነጋገር አዲስ ስታንዳርድ ስልክ የደወለ ቢሆንም ለምን እንደፈለግናቸው ጉዳዩን ከሰሙ በኋላ ምላሽ ሳይሰጡን ስልክ በመዝጋታቸዉ ከመንግስት ወገን ያለውን ሃሳብ ማካተት አልቻልንም፡፡

መምህራኑ ከዚህ ቀደም መንግስት እስከ መስከረም 1 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ ለጥያቄዎቻቸዉ መልስ የማይሰጥ ከሆነ የራሳቸውን እርምጃ እንደሚወስዱ ያስጠነቀቁ ሲሆን በወቅቱ የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ፕሬዘዳንት ዶክተር ዮሐንስ በንቲ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ያቀረቡትን ጥያቄዎች ለትምህርት ሚኒስቴርና ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት አቅርበዉ አንዳንድ ለውጦች መደረጋቸውን ለአዲስ ስታንዳርድ ገልፀው ነበር ፡፡ አስ 

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.