አዲስ አበባ፣ ሓምሌ 11 /2015 ዓ.ም፡- የኢትዮ ቴሌኮም 2015 በጀት ዓመት 75.8 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ በማግኘት የእቅዱን 101% ማሳካቱን አስታወቀ፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም ከሐምሌ 2014 እስከ ሰኔ 2015 ያለውን የሥራ አፈጻጸሙን የሚገልፅ ሪፖርቱ ዛሬ ሓምሌ 11፣ 2015 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል፡፡ በሪፖርቱም የገቢ ምንጩን በማስፋት በዋናነት ከመሠረታዊ ቴሌኮም አገልግሎቶች ባሻገር ያሉ በርካታ ተቋማትና አጠቃላይ ደንበኞችን ማዕከል ያደረጉ የዲጂታል መፍትሔዎች፣ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን በማቅረብ እንዲሁም የኔትወርክና የሲስተም አቅም በማሳደግ ከአቀደው በላይ ገቢ ማግኘቱን ገልጧል፡፡
የተገኘው ገቢ ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ23.5% ብልጫ አለው ያለው ሪፖርቱ የተገኘው ገቢ በአገልግሎት አይነት ሲታይ የድምጽ አገልግሎት 43.7% ድርሻ ሲኖረው ዳታና ኢንተርኔት 26.6%፣ ዓለም አቀፍ ገቢ 9%፣ እሴት የሚጨምሩ አገልግሎቶች 6.9%፣ የቴሌኮም መጠቀሚያ መሣሪያዎች (ቀፎ፣ ዶንግል፣ ሞደም) 4.7% እንዲሁም ሌሎች አገልግሎቶች 7.2% ድርሻ አላቸው ብሏል፡፡
የውጭ ምንዛሪ ከሚያስገኙ አገልግሎቶች አጠቃላይ 164.1 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ማግኘት የተቻለ ሲሆን አፈጻጸሙም 107.8% መሆኑ በሪፖርቱ ተገልጧል፡፡ የገቢ እድገቱ የተመዘገበው በሁሉም አገልግሎቶች ላይ የተስተናገደው የትራፊክ መጠን በመጨመሩ ነው ያለው ኩባንያው ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር በድምጽ ትራፊክ የ34.5% እና በዳታ ትራፊክ የ94.5% እድገት ተመዝግቧል ሲል አስታውቋል፡፡
በበጀት አመቱ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ደንበኞች ብዛት 72 ሚሊዮን መድረሱን የጠቀሰው ኩባንያው አፈፃፀሙ ካለፈው በጀት ማጠናቀቂያ ከነበረበት ጋር ሲነጻጸር የ8% እድገት፣ እንዲሁም ከእቅድ አንጻር የ98% አፈጻጸም ተመዝግቧል ነው ያለው፡፡ በመሆኑም የሞባይል ድምፅ ደንበኞች ብዛት 69.5 ሚሊዮን፣ የመደበኛ ብሮድባንድ 618.3 ሺህ፣ የመደበኛ ስልክ ደንበኞች 853.6 ሺህ እንዲሁም የዳታና ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች 33.9 ሚሊዮን ናቸው ብሏል፡፡
ኢትዮ ቴልኮም ዓለም ላይ ካሉ 774 ኦፕሬተሮች መካከል በሞባይል ደንበኛ ቁጥር በአፍሪካ 2ኛ ደረጃ ፣ በዓለም ደግሞ 21ኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡
በተጨማሪም የሀገራችንን ዲጂታል ኢኮኖሚ ለማሳደግ፣ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት ፍላጎት ለማርካትና የፋይናንስ አካታችነትን ለማረጋገጥ ታስቦ የተጀመረው “የቴሌብር” አገልግሎት 34.3 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን በማፍራትና አጠቃላይ በኢኮኖሚው ላይ የግብይት መጠኑም 679.2 ቢሊዮን ብር ማንቀሳቀስ ተችሏል ተብሏል፡፡
የቴሌብር የዲጂታል ስርዓት የፋይናንስ አካታችነትን እና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ቴሌብር ሳንዱቅ፣ ቴሌብር እንደኪሴ፣ ቴሌብር መላ የተሰኙ የቴሌብር የፋይናንስ አገልግሎቶችን ከዳሽን ባንክ ጋር በመሆን እ.አ.አ ከነሀሴ ወር 2022 ጀምሮ ለደንበኞቹ በማቅረብ ለ2.4 ሚሊዮን ደንበኞች በቴሌብር መላ እና እንደኪሴ ከ4.1 ቢሊዮን ብር በላይ የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ኩባንያው አስታውቋል፡፡ ከ768 ሺህ በላይ ደንበኞች በቴሌብር ሰንዱቅ (ቁጠባ) ከ3.6 ቢሊዮን ብር በላይ ቆጥበዋልም ብሏል፡፡
በተጨማሪም ቴሌብር ስንቅ፣ ቴሌብር እንደራስ፣ ቴሌብር አድራሽ እና ቴሌብር ድልድይ የተሰኙ የቴሌብር የፋይናንስ አገልግሎቶችን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በአጋርነት እ.አ.አ ከሰኔ ወር 2023 ጀምሮ ለደንበኞቹ ለወኪሎቹና ለአጋር ነጋዴዎች በማቅረብ በ13 ቀናት ውስጥ 25,666 ደንበኞች 155.3 ሚሊዮን ብር ብድር ተጠቃሚ የሆኑ ሲሆን 2,564 ደንበኞች 14.2 ሚሊዮን ብር መቆጠብ ችለዋል ሲል ሪፖርቱ ገልጧል፡፡
በሰሜኑ የሀገራችን ክፍልና በተለያዩ አካባቢዎች ከጸጥታ ጋር በተገናኘ ተቋርጦ የነበረውን አገልግሎት በአጭር ጊዜ ውስጥ ማስቀጠል ተችሏል ሲል የገለፀው የኩባንያው ሪፖርት በዚህም በ186 ከተሞችና ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ 943 የሞባይል ጣቢያዎች እንዲሁም 1,886 ኪ.ሜ የፋይበር መስመር በመጠገንና መልሶ በማቋቋም አገልግሎት መስጠት ተችሏል ብለዋል፡፡
በተለያዩ የሀገራችን ክፍል ባጋጠመው የፀጥታ ችግር ምክንያት የአገልግሎት መቋረጥ፣ በወቅቱ የጥገናና የማስፋፊያ ወይም የማሻሻያ ሥራዎች ማከናወን አለመቻል፣ የሃይል አቅርቦት መቆራረጥ፣ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት እጥረት፣ በኔትዎርክ ሀብትና በተቋም ንብረት ላይ የሚደርሱ አደጋዎች እንዲሁም የፋይበርና የኮፐር መስመሮች ስርቆትና መቆራረጥ፣ የመሬት አቅርቦት መዘግየት፣ የቴሌኮም ማጭበርበር፣ የነዳጅ እጥረት፣ የግንባታ ስራ ግብአቶች እጥረት፣ የገበያ አለመረጋጋት እንዲሁም የኮንትራክተሮች በውላቸው መሠረት የመፈጸም አቅም ውስንነት በዋናነት ኩባንያው በበጀት ዓመቱ ካጋጠሙት ችግሮች መካከል መሆናቸው ገልፆ ችግሮቹን ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት በማድረግ እንዲሁም የተለያዩ የቢዝነስና የቴክኖሎጂ አማራጮችን በመውሰድ የሚያስከትሉትን ተጽዕኖ መቀነስ ተችሏል ብሏል፡፡
ኩባንያችን በበጀት ዓመቱ ያስመዘገበው የላቀ አፈጻጸም የተመዘገበው የተቋሙ የሥራ አመራር ቦርድ ከኩባንያው አመራር ጋር በመናበብና በመደጋገፍ፣ የኩባንያችን አመራርና ሠራተኞች ለኩባንያቸው ያላቸው የባለቤትነት ስሜትና በውድድር ገበያው በሁሉም መስክ የመሪነት ሚናውን ለማስቀጠል ካላቸው ህልምና ለውጤታማነቱ ባሳዩት ቁርጠኝነት እንዲሁም በየወቅቱ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በጽናትና በአግባቡ በመወጣት ላቀዷቸው ግቦች መሳካት ባደረጉት ያልተቆጠበ ጥረትና ሰፊ ርብርብ ነው ሲል ገልጧል፡፡አስ