ዜና፡ የኢትዮጵያ ዓየር መንገድ  ዋና ስራ አስፈጻሚ ከነገ ጀምሮ ወደ መቐለ መደበኛ በረራ እንደሚጀመር ገለፁ

መቐለ አሉላ አባ ነጋ አየር ማረፊያ ፎቶ፡ናሽናልፓርከ.ኮም

አዲስ አበባ፣ታህሳስ 18/ 2015 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ ዓየር መንገድ  ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ዛሬ ለሚዲያ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፣ ተቋርጦ የነበረው ከአዲስ አበባ-መቀሌ የአየር ትራንስፖርት በነገው ዕለት ይጀምራል፡፡ ዋና ስራ አስፈጻሚው በህዳር ወር  ወደ ትግራይ ክልል ተቋርጦ የቆየውን መደበኛ በረራ ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆኑን ቢገልፁም እንካሁን ሳይጀመር ቆይቷል፡፡

በትላንትናው እለት በመቐለ ጉብኝት ያደረገው የፌደራል መንግስት ከፍተኛ የልዑካን ቡድን አባል የሆነው መስፍን የመቐለ አሉላ አባ ነጋ አውሮፕላን ማረፊያ ለበረራ ምቹ ሁኔታ ላይ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በመሆኑም አየር መንገዱ ነገ በሚጀምረው በረራ በቀን አንድ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን የደንበኞቹ ፍላጎትን መሰረት በማድረግም የበረራው ቁጥሩ ከፍ ሊል የሚችልበትን ሁኔታ እንደሚፈጠርም ነው ዋና ስራ አሰፈጻሚው የገለፁት፡፡

ዋባ ስራ አስፈጻሚው አክለውም ተቋርጦ የነበረውን የበረራ እንቅስቃሴ በሁሉም የትግራይ ክልል የበረራ መዳረሻዎች ለማስጀመር ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡

ልክ እንደ ሁሉም አገልግሎቶች፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በክልሉ ሲደርጋቸው የነበረውን በረራዎች ያቋረጠው ሰኔ 21 ቀን 2014 ዓ.ም የትግራይ ሃይሎች መቐለን ጨምሮ አብዛኛውን የትግራይ ክፍል ሲቆጣጠሩ ነው።

ዋና ስራ አስፈጻሚው በህዳር ወር እንደተናገሩት በክልሉ ከሚገኙት ኤርፖርቶች መካከል መቀሌ እና ሽሬ ኤርፖርቶች በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኙ እና በረራቸውን ለመጀመር ምቹ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። ነገር ግን በኢትዮጵያ ከፍተኛ የቱሪስት መዳረሻ የሆነው የአክሱም አውሮፕላን ማረፊያ በግጭቱ የወደመ በመሆኑ ለበረራ ምቹ እንዲሆን መጠገንና መስተካከል አለበት ማለታቸው ይታወሳል።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.