ዜና፡ 85 ተጠርጣሪ ግለሰቦች የተሰታፉበትና በህገ-ወጥ መንገድ ተሰበሰበ የተባለ ከ20 ሚሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ማገዱን መንግስት ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 18/ 2015 ዓ.ም፡- መንግስት በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሂሳብ ደብተር የሚከፍቱበትን የዲያስፖራ አካውንት ህግ እና የአሠራር ስርዓት ላይ ባደረገው ክትትል፣ የትንተናና ማጣራት ስራዎች 85 ተጠርጣሪ ግለሰቦች የተሰታፉበት እና በህገ-ወጥ መንገድ ተሰበሰበ የተባለ መጠኑ 20,226,583 ዶላር የውጭ አገር ገንዘብ በባንክ እንዲታገድ መደረጉን የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት አስታወቀ

ወንጀሉ የተፈፀመው የተለያዩ ሀሰተኛ ሰነዶችንና የማጭበርበር ስልቶችን በመጠቀም ሲሆን ከነዚህም መካከል አንደኛ ውጭ አገር ሳይሄዱ ውጭ አገር ሄደው የተመለሱ በማስመሰል ሀሰተኛ ዲክላራሲዮን በማቅረብና በመጠቀም፣ ሁለተኛ ከውጭ አነስተኛ የውጭ ምንዛሪ ይዘው በመግባት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ይዘው እንደገቡ በማስመሰል ቀሪውን በህገ-ወጥ መንገድ ከጥቁር ገበያ ላይ በመሰብሰብና ሀሰተኛ ሰነድ/ዲክላራሲዮን በማቅረብ መሆኑ ተገልጧል፡፡

ሶስተኛ የሌላውን ሰው ዲክላራሲዮን የራስ አስመስለው በመጠቀም፣ አራተኛ ህጉ ከሚፈቅደው ውጪ በተለያዩ ባንኮች የዲያስፖራ አካውንት በመክፈትና በመጠቀም በአጠቃላይ ሌሎች ሀሰተኛ ዲክላራሲዮን በመጠቀም የወንጀል ተግባራት መፈጸማቸውን መረዳት ተችሏል ብሏል።

የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ባካሄደው ክትትል፣ ትንተናና ማጣራት ሂደት ውስጥ ግለሰቦቹ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የዲያስፖራ አካውንትን በሚመለከት ያወጣውን መመሪያ፣ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 780/2005 እንዲሁም የወንጀል ህግን በመተላለፍ የተፈጠረውን ዕድል ለወንጀል መጠቀሚያ ማዋላቸውን ማረጋገጥ ተችሏል።

በመሆኑም በወንጀል ድርጊቱ ተሳታፊዎች ላይ ተገቢው ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ጉዳዩ ለወንጀል ምርመራ የተላለፈ መሆኑን የገለፀው አገልግሎቱ ወንጀሎቹን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብርና በቅንጅት እያከናወናቸው ያሉ ስራዎችን የበለጠ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡

በቀጥታም ሆነ በተዘዋወሪ በመሰል የወንጀል ድርጊቶች ውስጥ ተሳትፎ ያላቸው አካላት የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ከህግ ተጠያቂነት እንደማያመልጡ ተገንዝበው ከድርጊቱ እንዲታቀቡ አገልግሎቱ በጥብቅ አሳስቧል።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.