ዜና፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ተከስቶ የነበረው ችግር በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት መፈታቱን አስታወቀች፤ በሲኖዶሱ ተወግዘው የነበሩት ሶስቱ አባቶች ወደ ቀድሞ ክብራቸው ተመልሰዋል ተብሏል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9/ 2015 ዓ.ም፡– የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በውስጧ ተከስቶ የነበረው ችግር በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት መፈታቱን አስታወቀች። ሦስቱ ሊቃነ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ሳዊሮስ፣ ብጹዕ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ እና ብጹዕ አቡነ ዜና ማርቆስ ወደ ቀደመ ሀገረ ስብክታቸውና የክነት ማዕረጋቸው እንዲመለሱ መወሰኑንም ገልጻለች።

በተጨማሪም ቤተ ክርስቲያኗ በሦስቱ አባቶች መመለስ ታላቅ ደስታ ተሰምቷታል፣ ካህናት፣ ምእመናን በሀዘናችን ተካፋይ የነበራችሁ በሙሉ የዚህ ደስታ ተካፋዮች በመሆናችሁ እንኳን ደስ ያላችሁ በማለት ቅድስት ቤ ክርስቲያን ደስታዋን ትገልጻለች ብሏል መግለጫው።

በችግሩ አፈታት ወቅት መንግሥት በተለይም ክቡር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ፖለቲካዊ ችግሩን በፖለቲካዊ መንገድ ከመፍታታቸውም ባሻገር የቤተ ክርስቲያን ችግር በቀኖናና በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን መሠረት እንዲፈታ ታላቁን አስተዋጽኦ አበርክተዋል ስትል ቤተክርስቲያኗ በሰጠችው መግለጫ አወድሳለች። ለአበርክቷቸውም ምስጋናዋን አቅርባለች።

በሁለቱ ጎራ የነበሩት አባቶች እንደቀድሞው ወደ አንድነት ለመምጣት የደረሱት ስምምነት በዝርዝር ቀርቧል። በስምምነቱም መሰረት በኦሮሚያ ክልል በኦሮምኛ ቋንቋ ትምህርት፤ ቅዳሴ እና ሌሎችም አገልግሎቶች እንዲሰጡ የተጀመረው ሥራ የሕዝቡን ጥያቄ በሚመልስ መልኩ እንዲጠናከር የተወሰነ መሆኑን አስታውቆ ለዚህም ከዚህ በፊት ከተደረገው በተጨማሪ አስፈላጊው በጀትና የሰው ኃይል እንደሚመደብ አመላክቷል። በተጨማሪም በኦሮሚያ እና በሌሎች አካባቢዎች የሚያገለግሉ ቋንቋውን የሚያውቁ አገልጋዮችን የሚያሠለጥኑ ተጨማሪ ኮሌጆች እና ማሠልጠኛዎች እንዲከፈቱ፣ የተከፈቱትም እንዲጠናከሩ እንደሚደረግ ተካቷል።

ለኦሮሚያ አህጉረ ስብከት በቂ የሆነ የኦሮምኛ ቋንቋን የሚያውቁና በቋንቋው የሚያገለግሉ ኤጲስ ቆጶሳት በቀጣይ ግንቦት እንደሚሾም የጠቆመው የስምምነቱ ዝርዝር በእነ አቡነ ሳዊሮስ በጳጳስንት ከተሾሙት ውስጥ በቤተ ክርስቲያን ሕግና ሥርዓት ተመዝነው የሚያሟሉት እንደገና በቅዱስ ሲኖዶስ እንዲሾሙ ይደረጋል ብሏል።

ጥላቻን የሚያባብሱ ጉዳዮችን ከማድረግ መቆጠብ ይገባል ያለው የስምምነቱ ሌላኛው ነጥብ ሚዲያዎች፣ አክቲቪስቶች፣ መምህራን እና አባቶች ፍቅርን ከሚያጠፋ፣ ጥላቻን ከሚያበዛና መለያየትን ከሚያሰፋ ነገር ሁሉ እንዲቆጠቡ በእግዚአብሔር ስም ጠይቋል።  

በተመሳሳይ የሁለቱ አባቶችን ስምምነት ተከትሎ በሀገሪቱ ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ከአቡነ ማትያስ ጋር በመሆን ሲያስተላልፉ የተደመጡት ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ ‘’የዛሬው ተሳክቷል፤ የቀረው ደግሞ ወደ ትግራይ ሄደን የቀሩትን ማምጣት ነው፤ አንድ እንድትሆኑ ነው እኛ የምንፈልገው’’ ሲሉ ተደምጠዋል።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በበኩላቸው ስምምነት ላይ በመደረሱ እጅግ ደስ ብሎኛል፤ ጠ/ሚኒስትሩ ብዙ ለፍተዋል፣ ደክመዋል፤ እናመሰግናለን ብለዋል። 

መግለጫው ከጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ላለፉት ሶስት ሳመንታት ቤተክርስቲያኗ ሀዘን ላይ እንደቆየች ያተተው መግለጫው የእምነቱ ተከታዮች ለከፈሉት መስዋዕትነት እውቅና መስጠቷን አመላክቷል።

ዳራ

ጥር 18/ 2015 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከቀኖና እና ከእውቅናዬ ውጭ የሆነ ሕገ ወጥ የኤጲስ ቆጶሳት እና ጳጳሳት ሹመት ተስጥቷል በተባለው ጉዳይ ላይ ቅዱስ ሲኖዶሱ ባካሄደው አስቸኳይ ምልአተ ጉባኤ፣ ሲመቱን በሰጡ ሶስት ሊቀጳጳሳት እና 25 ተሿሚዎች ላይ የውግዘት ውሳኔ ማስተላለፏ ይታወቃል፡፡ የተወገዙት ሶስቱ  ጳጳሳት እና 25 ኤጴስ ቆጶሳት እሁድ ጥር 20 በምላሹ 12 የነባሩን ሶኖዶስ አባላትን በማውገዝ የራሳቸውን ኤጴስ ቆጶሳት በመሾም ወደ ተመደቡበት ሀገረ ስብከት እየተሰማሩም ነበር፡፡

ቤተክርስቲያኗ ለሁለት እንድትከፈል ሊያደርግ የነበረው ክስተት፣  በኦሮምያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን በሶዶ ዳጬ ወረዳ በወሊሶ ከተማ በበአለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን በአቡነ ሰውሮስ እና ሌሎች ሁለት ጳጳሳት መሪነት በርካት ህዝበ ክርስቲያንን ያስቆጣው  ለኦሮሚያ ክልል 17 ጳጳሳት እንዲሁም 9 ጳጳሳት ከኦሮሚያ ውጭ በጥቅሉ 26 ጳጳሳትን ከቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ቀኖና ውጭ መሾማቸው ነው፡፡

አቡነ ሳዊሮስ በዓለ ሲመቱ ከተከናወነ በኋላ በሰጡት መግለጫ ሲመቱን ለመፈጸም ያበቋቸውን አስገዳጅ ሁኔታዎች መዘርዘራቸው ይታወሳል። ከተዘረዘሩት ምክንያቶችም መካከል በበርካታ የሀገሪቱ ክፍሎች የቤተክርስቲያኗ ተከታዮች አገልግሎት ለማግኘት ያስችላቸው ዘንድ አከባቢያቸውን የሚያውቁ እንዲሁም ቋቋቸውን የሚናገሩ አገልጋዮች ሊኖራት እንደሚገባ አመላክተው ይህ ባለመደረጉ ቤተክርትሲያኗ በተለይም በኦሮምያ እና ደቡብ ክልል በሚሊዮን የሚቆጠሩ አማኞቿን አጥታለች የሚለው ይገኝበታል።

የጳጳሳቱ ሹመቱ ከሲኖዶሱ እውቅና ውጭ የተደረገ ህገ-ወጥ ሹመት ነው ያሉት የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ድርጊቱ “በቤተ ክርስቲያን ላይ ያነጣጠረ ታላቅ ክስተት” ነው በማለት አስቸኳይ ምልአተ ጉባኤ መጥራታቸው ይታወሳል፡፡አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.