ዜና፡ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ትግራይ ቅርንጫፍ በአቅርቦት እጥረት ምክንያት አገልግሎት መስጠት አለመቻሉን አስታወቀ

ብርሃኑ መኮንን፤ ፎቶ ከቪዲዮ የተወሰደ/ዶቸ ቨለ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 13/2015 ዓ.ም፡ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ትግራይ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በትግራይ በድርቅና በግጭት ለተጎዱ ወገኖች በመድኃኒት እጥረትና ከሎጂስቲክስ ጋር በተያያዙ ተግዳሮቶች አገልግሎቱን ማድረስ እንዳልቻለ አስታወቀ። 

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል በበኩሉ በትግራይ ከሚገኘው ቅርንጫፉ ጽህፈት ቤቱ ጋር በተፈጠረው ችግር ምክንያት ግንኙነት ማድረግ እንዳልቻለ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ትግራይ ቅርንጫፍ ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ መኮንን እንዳሉት የቅርንጫፉ የህክምና አገልግሎት ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ አግልግሎት አለመስጠቱን ጠቁመው በአሁኑ ወቅት ያለው ሁኔታ ይሻሻላል የሚል እምነት ቢኖርም እየባሰ እንደሄደ ለክልሉ ሚዲያ ተናገረዋል።

በተለያዩ የትግራይ ክልል አካባቢዎች ለሚገኙ የቀይ መስቀል ፋርማሲ ቅርንጫፎች መድኃኒት ማቅረብ አልቻልን፣ ለዚህ ዋናው ምክንያት ደግሞ መድሃኒት ስለሌ መሆኑን የተናገሩት አቶ ብርሃኑ   በክልሉ የባንክና የስልክ ግንኙነት አገልግሎት ባለመኖሩ ቅርንጫፎቹ በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ ለማወቅ አልቻልንም ብለዋል።

አቶ ብርሃኑ ከክልሉ መገናኛ ብዙሀን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለፁት በትግራይ ባለስልጣናት እና በኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት መካከል የተደረገውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በቂ የመድሃኒት እና የቁሳቁስ አቅርቦት ይገባል የሚል ተስፋ የነበረን ቢሆንም  የአቅርቦት እጥረቱ አሁንም ቀጥሏል ብለዋል።

በትግራይ ክልል ያለው የመድሃኒት እጥረት ችግር በጣም ክፍተና በመሆኑ የችግሩን ስፋት ግምት ውስጥ በማስገባት አለም አቀፉ ማህበረሰብ  አስፈላጊውን የመድሃኒት አቅርቦት ላይ ትኩረት እንዲሰጥም ሃላፊው  አሳስበዋል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል በተፈጠረው ችግር ምክንያት ለመቀሌ የሚላክ መሰረታዊ መድሃኒት እጥረት  እንዳለ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል የሰብአዊ ዲፕሎማሲ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ መስፍን ደረጀም አረጋግጠዋል።

“ስልክ ባለመኖሩ የተነሳ  በትግራይ ከሚገኘው የቀይ መስቀል ቅርንጫፍ ቢሮ ጋር ምንም አይነት መረጃ ልውውጥ እና ግንኙነት እንደሌለ አቶ መስፍን  ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል።

ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ከአለም አቀፍ የቀይ መስቀል ማህበረሰብ ጋር በመተባበር 17 ሚሊየን ብር የሚገመት እህል እና ቁሳቁስ ሁለት ዙር ወደ ትግራይ ክልል መላኩንም አስታውሰዋል።

አቶ መስፍን አያይዘውም የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል በግጭት የተጎዱ አካባቢዎችን ለመደገፍ እቅድ ማውጣቱን ጠቁመው የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ሁኔታ ከተፈጠረ በሙሉ አቅሙ እንደሚረዳም ተናግረዋል።

የሰላም እርቁን ተከትሎ የተ በውስን ደረጃ መድሃኒት ወደ ትግራይ እንዲገባ የተደረገ ቢሆንም ክልሉ   የረዥም ወራት ግጭት በማስተናገዱ የተነሳ ከፍተኛ ጉዳት ስለደረሰበት   ሆስፒታሎች ተጎድተዋል ወይም ወድመዋል።  የውሃ፣ የመብራት እና የመድኃኒት አቅርቦት እጥረት እንዳለ እንደዚሁም ሰዎች ለከፋ ረሃብ መጋለጣቸውን የአለም አቀፍ ቀይ መስቀል ማህበረሰብ ዘግቧል።

እሁድ እለት የትግራይ ክልል መሪ ዶክተር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል በሰጡት መግለጫ የሚሰጠው ድጋፍ በተወሰኑ አካባቢዎች የተገደበ በመሆኑ መድሀኒት አቅርቦት እና የመሰረታዊ አገልግሎቶችን መልሶ የማቋቋም ሁኔታ ትክክለኛ ፍሰት እንደሌላቸው ተናግረዋል።  አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.