ዜና፡ የኢትዮጵያ መንግስት ሂዩማን ራይትስ ዎች በምዕራብ ትግራይ የሚካሄደው የዘር ማጽዳት ወንጀል ቀጥሏል በማለት ያወጣውን ሪፖርት እንደማይቀበለው ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2015፡-  የኢትዮጵያ መንግስት ሂዩማን ራይትስ ዎች በምዕራብ ትግራይ የሚካሄደው የዘር ማጽዳት ወንጀል እንደቀጠለ ነው በማለት ያወጣውን ሪፖርት እንደማይቀበለው አስታወቀ፡፡

በፌደራል መንግስቱ እና በትግራይ ሀይሎች መካከል የሰላም ስምምነት ቢፈረምም አሁንም በምዕራብ ትግራይ የሚካሄደው የዘር ማጽዳት የወንጀል ተግባር መቀጠሉንና የሰብአዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ አካላትም ለፈጸሙት ግፍ ተጠያቂ አልተደረጉም በማለት ሂዩማን ራይት ወች ግንቦት 24 ቀን 2015 ያወጣውን ሪፖርት አስመልክቶ መንግስት  ምላሽ ሰጥቷል፡፡

መንግስት ምላሹም ሪፖርቱ በአንዳንድ አካባቢዎች ጉልህ የሆኑ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን የሚገልጽ መሰረተ ቢስ ሪፖርት ነው ሲል ተችቷል።

አክሎም በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የነበረው ግጭት በርካታ አካባቢዎችን ለጉዳት ያጋለጠ ቢሆንም በልዩ ሁኔታ የተወሰነ አካባቢን መርጦ ደጋግሞ ሪፖርት በማዘጋጀት በሰብዓዊ መብት አጀንዳ ሽፋን የተለየ የፖለቲካ ተልዕኮዉን ለማሳካት ዓላማ ያደረገ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም ሲል ገልጧል፡፡ የመብት ጥሰት ተፈጽሟል ለማለት የቀረበው ሪፖርት ይዘት ሲታይም ተገቢው ምርመራ ያልተደረገበት እና በበቂ ማስረጃ ያልተደገፈ ከመሆኑ አንጻር እምነት የሚጣልበት አይደለም ብሏል።

በተጨማሪም በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የነበረው ግጭት በአፋር፣ አማራ እና ትግራይ ክልሎች ውስጥ የሚኖሩ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ጉዳት ያደረሰ መሆኑ የሚታወቅ ሆኖ ሳለ ድርጅቱ አንድ አከባቢን ለይቶ በመምረጥ ሪፖርት ማውጣቱ ድርጅቱ ድብቅ አጀንዳውን በሀገራችን ላይ ለማራመድና የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተዛባ ዕይታ እንዲኖረው ለማድረግ እየሰራ ለመሆኑ ማሳያ ነው ሲል አጣጥሎታል፡፡  

በአጠቃላይ በድርጅቱ የቀረበው ሪፖርት የተዛባና በአካባቢው ያለውን ነባራዊ ሁኔታ የማይገልጽ፣ ለዘመናት አብረው የቆዩ ሕዝቦችን አብሮ የመኖር እሴት የሚያጠለሽ፣ በሕዝቦች መካከል ግጭት ቀስቃሽ የሆነና ሀገራችን እያደረገች ያለውን የእርቅ እና ምክክር ሂደት የሚያደናቅፍ አሉታዊ ተፅዕኖ ያለው ሪፖርት ሆኖ አግኝተነዋል ብሏል መንግስት በመግለጫው።

በሰሜኑ ሀገራችን ክፍል የነበረውን ግጭት ለማቆም በፕሪቶሪያ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ለማስፈጸም ብሎም በሀገራችን የሚታዩ አለመግባበቶችን በዘላቂነት ለመፍታት የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ አማራጮችን በማዘጋጀት በሀገር አቀፍ ደረጃ በርካታ ውይይት እየተደረጉ ይገኛሉ ያለው መግለጫው የሽግግር ፍትህ ሂደቱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት የፈጸሙ ወገኖች ላይ ተገቢው ማጣራትን በማድረግ ተጠያቂነትን ማስፈንን ጨምሮ እውነትን የማፈላለግ እና ተጎጂዎችንም መልሶ ለማቋቋም የሚያስችል ማእቀፍ ይፈጥራል ሲል አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን እና የተ.መ.ድ. የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽ/ቤት ጥምር የክትትል ቡድን ተደራጅቶ ግጭቱ በነበረባቸው አካባቢዎች ያለውን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል እንዲያደርጉ በመጋበዝ መንግስት በሀላፊነት መንፈስ እየሰራ ባለበት ወቅት ይህንን ከግንዛቤ ሳያስገባ እና በቂ ማስረጃ በሌለበት ከላይ በተጠቀሰው ድርጅት የወጣው ሪፖርት ገንቢ ያልሆነና ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ምንግስት ገልጧል።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.