የውይይቱ ተሳታፊዎች፤ ፎቶ የአማራ ክልል ኮሙኑኬሽን ቢሮ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 25፣ 2015 ዓ.ም፡- በምዕራብ ጎንደር ዞን፣ የቋራ ወረዳ ነዋሪዎች እና የሱዳኑ አንኩራና ከርቸዲ ማኅበረሰቦች ታህሳስ 23፣ 2015 ዓ.ም. በተደጋጋሚ የሚፈጠሩ የፀጥታ ችግሮች ለመፍታት እና በድንበሮቹ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የህዝብ ለህዝብ ውይይት አድርገዋል፡፡
ከአማራ ክልላዊ መንግስት ኮሙኑኬሽን የተገኘው መረጋ እነደሚያመላክተው በሁለቱ አጎራባች ማህበረሰብ መካከል የተካሄደው ውይይት የሁለቱም አካላት የፀጥታ አካላት መሪዎች በተገኙበት ሲሆን ተሳታፊዎቹ ዘላቂ ሰላምን እንዴት ማረጋገጥ እንደሚቻል እና የእንስሳት ስርቆትና ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል ዘንዳ ውይይት አካሂደዋል፡፡
የቋራ ወረዳ የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ሞገስ የህዝብ ለህዝብ ውይይቱ በአጎራባች ማህበረሰቦቹ በሚፈጠሩ የፀጥታ ችግሮች በተለይም የእንስሳት ስርቆትን እና ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለማስቆም ትኩረት ያደርገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከአሁን በፊት ተደጋጋሚ የተደረጉ ውይይቶች፣ የእንስሳት ስርቆትን በሁለቱም ሃገራት በኩል እንዲመለስ ማድረግ ያስቻለ መሆኑን አክለው ጠቅሰዋል። እንዲህ አይነት ውይይቶችን በማስቀጠል ከእንስሳት ስርቆቱ በተጨማሪ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን በማስቆም በሁለቱም ሃገራት አጎራባች ወረዳዎች ሰላማዊ ግንኙነት መፈጠር መቻል እንዳለበት ገልፀዋል፡፡
በተለይም ጥቅምት 24/ 2013 በትግራይ ጦርነቱ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ያለው የድንበር አለመግባባት በተለያዩ የድንበር መግቢያ ቦታዎች ላይ በተደጋጋሚ የሚከሰት ሲሆን ሁለቱም ሀገራት በንፁሃን መኖሪያ ላይ ጥቃት ተፈጽሟል በማለት እርስ በእርስ ሲወነጅሉ ቆይተዋል፣ አንዳንዴም በድንደሮቻቸው በመካካላቸው ያሉትን መግቢያዎች ሲዘጉ ይስተዋላሉ፡፡
ታህሳስ 19 ቀን 2013 ዓ.ም. በወቅቱ የምዕራብ ጎንደር አስተዳደር የነበሩት አቶ ደሳለኝ ጣሰው የሱዳን ሀይሎች ሰፊ መሬት በመያዝ ነዋሪዎችን እየዘረፉ እና እየገደሉ ነው ሲሉ ወቅሰዋል። መግለጫው የወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ታህሳስ 22 ቀን 2020 ኢትዮጵያ እና ሱዳን በግዛታቸው ላይ ለረጅም ጊዜ የዘለቀውን አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መስማማታቸውን ካስታወቁ ከአምስት ቀናት በኋላ ነው።
ነገር ግን በድንበር አካባቢ ያለው ውጥረት እና እርስ በርስ መወቃቀስ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጋብ ያለ ይመስላል። በአሁኑ ሰዓት በሱዳን ሃይሎች ቁጥጥር ስር በሚገኘው በአል-ፋሻጋ ድንበር አካባቢ በተፈጠረው ግጭት እ.አ.አ. በታህሳስ 18 ሁለቱ ሃገራት የታሰሩ ወታደሮችን ተለዋውጠዋል፡፡አስ