አዲስ አበባ፣ጥር 18 2015 ዓ/ም፡- የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ቅርንጫፍ የመጀመርያው የሰብአዊ መብት ችሎት የቀድሞው የህውሓት ታጋይ አቶ ስብሓት ነጋ ከሀገር እንዳይወጡ በመከልከላቸው በከፈቱት ክስ ላይ የኢሜግሬሽን ባለስልጣን ኃላፊ ፍርድ ቤት ቀርቦ ቃል ባለመስጠቱ በፖሊስ ተይዞ ቃል እንዲስጥ ፍርድ ቤቱ ማዘዙን የከሳሽ ጠበቃ ታደለ ገ/መድህን ለአዲስ ስታንዳርድ ተናገሩ፡፡
አቶ ታደለ እንደገለፁት አቶ ስብሓት ነጋ ባለፈው አመት ነሃሴ ወር ላይ በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ እንዲሁም በኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ላይ ክስ የከፈቱት ለህክምና ወደ ናይሮቢ እንዳይሄዱ ተከልክለው ፓስፖርታቸውን ከተነጠቁ በኋላ ነው።
ህዳር 28፣ 2015 ዓ.ም የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ አቶ ስብሃት ነጋ በኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ከሀገር እንዳይወጡ መከልከላቸው መሰረት እንደሌለው በመግለጽ የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ እና የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ሃላፊዎቸ ቀርበው ማብራሪያ እንዲሰጡ ትእዛዝ አስተላልፎ ነበር።
የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ጥር 17፣ 2015 ዓ.ም ፍርድ ቤት ቀርቦ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ተቀብሎ አቶ ስብሃት እንዲጓዙ የተላለፈውን ውሳኔ ተግባራዊ ለማድረግ መዘጋጀቱን ለፍርድ ቤቱ ያስረዳ ሲሆን ነገር ግን የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ባለስልጣን ቀርቦ ማብራርያ እልሰጠም።
የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ቅርንጫፍ የመጀመርያው የሰብአዊ መብት ችሎት ፖሊስ በሚቀጥለው ቀጠሮ ጥር 24፣ 2015 ዓ/ም የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ባለስልጣን ሃላፊ ይዞ ለፍርድ ቤት እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
የ88 አመት የእድሜ ባለጸጋ የሆኑት እቶ ስብሓት ነጋ፣ ሁለት ዓመት ባስቆጠረ የትግራይ ክልል ጦርነት ግዜ የታሰሩ ሲሆን ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በሃይል ለመናድ ህገ-ወጥ ቡድን በማደራጀት ወጣቶችን በማነሳሳት በሰሜኑ መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በማድረስ ክስ ከተመሰረተባቸው 20 የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች መካከል አንዱ ናቸው።አቶ ስብሓት ነጋ በጥር 2014 ዓ/ም ላይ ነበር ከሌሎች የሕውሓት ከፍተኛ አመራሮች ጋር ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር ቤት የተፈቱት። አስ