ዜና፡ የአፋር ህዝብ ፓርቲ በፌዴራል መንግስት እና ትግራይ ክልል መካከል በተደረገው የግጭት ማቆም ስምምነት ላይ አመኔታ እንደሌለው ገለጸ

አዲስ አበባ መጋቢት 17 /2014፡ የአፋር ህዝብ ፓርቲ (አ.ህ.ፓ.) ዛሬ ጠዋት  ባወጣው መግለጫ  በፌዴራል መንግስት እና በትግራይ ክልል መካከል የሰብአዊ የግጭት ማቆም ስምምነት መታወጁ  ጥርጣሬ አንዳሳደረበት ገልጿል። ፓርቲው  ስምምነቱ የአፋር ህዝብን  አላካተተም ሲል ቅሬታውን አሰምቷል።

የትግራይ ክልልም ሆነ የፌደራል መንግስት ግጭቱን ለማቆም የወሰዱትን አወንታዊ እርምጃ ፓርቲው ያደነቀ ቢሆንም ሁለቱም ኣካላት የሰጡት መግለጫ አንዳንድ የአፋር ክልልን አካባቢዎች በትግራይ ሃይሎች መያዛቸውን እና በክልሉ ያለውን ሰብአዊ ቀውስ ችላ ማለቱ ፓርቲው ቅር እንዳሰኘው ገልጿል።

“አስከፊ የሆነው ሰብአዊ ቀውስ ግምት ውስጥ መግባት አለበት” ያለው ፓርቲው፣ አለም አቀፉ ማህበረሰብ የአፋር ህዝብን ሚና እንዲገነዘብ ጠይቋል። በግጭቱ ወደ 700,000 የሚጠጉ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውንም መግለጫው አመልክቷል። “ተፈናቃዮች ወደ መኖሪያቸው ለመመለስ ዘላቂ ሰላም እና ጸጥታ ይረጋገጥ ” ሲል መግለጫው ያሳሰበ ሲሆን፣ ተፈናቃዮችን መልሶ ማቋቋም በአስቸኳይ መጀመር አለበትም ብሏል።

ፓርቲው አክሎም የትግራይ ተዋጊ ሀይሎች  ‘ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ’ ከአፋር ክልል በአስቸኳይ ለቀው እንዲወጡና  መከላከያ ሰራዊት ወደ ክልሉ እንዲሰማራ ጠይቋል። መግለጫው የፌደራል መንግስት ከተጠያቂነት ለማምለጥ እና የአፋርን ህዝብ የተኩስ አቁም ስምምነቱ እንቅፋት አድርጎ ለማሳየት ሞክሯል ሲል ወንጅሏል።

በየካቲት ወር ላይ ፓርቲው በአፋር ክልል ሰሜናዊ ክፍል እየተከሰተ ያለውን ሰብአዊ ቀውስ በአስቸኳይ ሰብአዊ እርዳታ እንዲፈታ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ተመሳሳይ  ጥሪ አድርጓል። ፓርቲው በአፋር ጦርነት እየተካሄደ ባለበት ወቅት በህወሓት እና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል አሳታፊ ያልሆኑ የሁለትዮሽ ስምምነቶች ወይም ድርድር መካሄዱን እንደማይቀበል ማስታወቁ ይታወሳል። አስ 

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.