አዲስ አበባ፣ መጋቢት 20/2015 ዓ.ም:- የአዲስ አበባ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ “እምነትን ሽፋን በማድረግ የፖለቲካ አጀንዳ ለማራመድ የሚጥሩ አካላትን በጋራ መታገል ይገባል” ሲል አሳሰበ፡፡ ይህ የተባለው ቢሮው በከተማው ሰላምና ልማት ስራዎች ላይ ከሁሉም የሀይማኖት ተቋማት አባቶች ጋር በዛሬው እለት ከተወያየ በኋላ ነው፡፡
በውይይቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ በሀይማኖት ተቋማት ውስጥ በንግግር መፈታት ያለባቸው የውስጥ ጉዳዮች ወደ ውጭ እየወጡ አጀንዳ ሲሆኑ የሚስተዋል በመሆኑ እምነትን ሽፋን በማድረግ የፖለቲካ አጀንዳ ለማራመድ የሚጥሩ አካላትን በጋራ መታገል ይኖርብናል በማለት ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ዛሬ ባወጣው መረጃ መሠረት፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ከተማዋን ለማወክ ከውስጥና ከውጭ ሚዲያን ጨምሮ በማስተባበር የሚደረጉ በርካታ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን መግለጻቸውን ጠቅሶ፣ “ቤተ – እምነቶች ችግሮች ሲያጋጥሟቸው ከሚመለከታቸው የመንግስት መዋቅሮች ጋር በመነጋገር መፍታት እንደሚገባ አስገንዝበዋል” ብሏል።
የአዲስ አበባ ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ፀሀፊ መጋቢ ታምራት አበጋዝ እንዳሉት ሀይማኖቶች የተመሰረቱበት ዋና ዓላማ ሰላም በመሆኑ ለሰላም መረጋገጥ እና የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የማድረግ ሚናችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል፡፡
በውይይቱ የተሳተፉ የእምነት አባቶች በቤተ እምነቶች ላይ በአንዳንድ አካላት የሚሰነዘሩ ግጭት ቀስቃሽ ተግባራት ለሀገርና ለከተማችን ሰላምና ደህንነት ሲባል ማስቆም እንደሚገባ ተናግረዋልሲልም ቢሮው ጨምሮ ገልጿል። አስ