አዲስ አበባ፣ ህዳር 19 / 2015 ዓ.ም፡- ሰሜን ጎንደር ዞን የሚገኙ አንዳንድ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የአንቡላንስ ተሽከርካሪዎች ለተፈለገው ዓላማ አገልግሎት ባለመስጠታቸው እናቶች በቤታቸው እንዲወልዱ መገደዳቸው የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ያላለም ፈንታሁን ገለፁ፡፡
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ያላለም ፈንታሁን እንደገለፁት ተሽከርካሪዎቹን ከተቀጠረ የመንግስት ሹፌር ውጭ ሌሎች በመንግስት ያልተቀጠሩ አሽከርካሪዎች እንደሚያሽከረክሩ እና በመንግስት ተቀጥረው መኪናቸው በተለያዬ መንገድ ከጥቅም ውጭ የሆነባቸው ሹፌሮች ስራ ፈትተው መቀመጣቸው የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ማስነሳቱን ገልፀዋል፡፡
አስተዳዳሪው ለወላዶች የመጡ አንቡላንሶች ከተፈለገው ዓላማ ውጭ በማገልገላቸው እናቶች በቤት ውስጥ እንዲወልዱ መሆናቸው የችግሩን አሳሳቢነት ያጎላዋል ማለታቸውን ከሰሜን ጎንደር ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የሰሜን ጎንደር የሲቪል ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት መምሪያ ኀላፊ አቶ ያሬድ አበበ በስሜኑ ጦርነት ብዙ ተሽከርካሪዎች ተወስደውብናል ያሉ ሲሆን በዞኑ ያለን ተሽከርካሪ ለተፈለገው ዓላማ በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡