አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28/2015 ዓ.ም፡- የአማራ ክልል መንግስት የፋኖ ታጣቂ ሀይል መሪ የነበረው ዘመነ ካሴን ትላንት ግንቦት 27 ቀን 20015 ዓ.ም ሲፈታው የፌደራል መንግስት የቀድሞው ባልደራስ ፓርቲ ሊቀመንበር አሁን ደግሞ የአማራ አንድነት ግንባር መመስረቱ የተሰማው እስክንድር ነጋን እግር በግር እየፈለገው እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
በአማራ ክልል የባሕር ዳር እና አካባቢው ፍርድ ቤት አቶ ዘመነ ካሴን ከዘጠኝ ወራት እስር ብኋላ ትላንት ግንቦት 27 ቀን 20015 ዓ.ም የሚያስከስሳቸው ምንም ጉዳይ የለም በሚል በነጻ አሰናብቷቸዋል።
በአቶ ዘመነ ካሴ በእስር በነበሩበት ወቅት የተለያዩ ክሶች ቀርቦባቸው የነበረ ቢሆንም ዋነኛው የቀረበባቸው ክስ ግን “በህግ ማስከበር ሥራ ላይ የነበረን ሰው ገድለዋል” በሚል እንደነበር ተገልጿል። ጉዳያቸውን ሲመለከት የቆየው የባሕር ዳር እና አካባቢው ፍርድ ቤት አቶ ዘመነ ካሴን “የሚያስከስሳቸው ጉዳይ ባለመኖሩ” ግንቦት 25 ቀን 2015 ዓ.ም በነፃ እንዳሰናበታቸው ጠበቃቸው አቶ በሙሉ ታደሰ ከጀርመንድ ድምጽ ሬድዮ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስታውቀዋል።
ዘመነ ካሴ ከእስር ከተፈቱ በኋላ አቀባበል ላደረጉላቸው ሰዎች ባደረጉት ንግግር የአማራ ክልል በአስር አቅጣጫ ተከቦ በጦርነት ውስጥ ነው ያለው ሲሉ በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች በተሰራጨው የቪዲዮ መረጃ ሲናገሩ ተደምጠዋል። ይህ ነገር ባስቸኳይ መቆም አለበት ሲሉም አሳስበዋል። እድሜውና ጤናው የሚፈቅድለት ወንድም ይሁን ሴት ከቤቱ መቀመጥ የለበትም፤ በጋራ የምንሰራው ብዙ ስራ ስላለ ተዘጋጁ ሲሉ ለተሰብሳቢው ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ በተለያዩ ወንጀሎች ጠረጠርኩት ያለውን ዘመነ ካሴን መስከረም 11 2015 በባህር ዳር ከተማ ቀበሌ 3 በቁጥጥር ስር ያዋለው ሲሆን በወቅቱ ከ500 ሺህ ብር በላይ በኢግዚቢት መያዙ ይታወሳል፡፡
በሌላ ዜና በአማራ ክልል በምሥራቅ ጎጃም ዞን፣ ደብረ ኤልያስ ወረዳ ሥላሴ ገዳም መሽገው መንግሥትን በትጥቅ ትግል ለመጣል ሲንቀሳቀሱ በነበሩት እስክንድር ነጋ እና ግብረዓበሮቹ ላይ በተወሰደ እርምጃ ክልሉን የማተራመስ ሴራቸው አከሸፍኩ ሲል የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታውቋል። የታጣቂ ቡድኑ መሪና አስተባባሪ የነበረው እስክንድር ነጋ እና ግብረአበሮቹ ከአካባቢው ለመሰወር ቢሞክሩም የመከላከያ ሠራዊት እና የአማራ ክልል የጸጥታ ኃይሎች በጋራ በቁጥጥር ሥር ለማዋል እግር በእግር በመከታተል የተቀናጀ ኦፕሬሽን እያካሄዱ መሆኑንም ግብረ ኃይሉ ገልጿል።
በተወሰደው እርምጃ በእስክንድር ነጋና በግብረዓበሮቹ ለውጊያ ሲውል የነበረው ምሽግ መሰበሩን እና በ200 ታጣቂዎችም ላይ እርምጃ መወሰዱን የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታውቋል።
የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል በመንግስት እና በገዢው ፓርቲ በሚተዳደሩ መገናኛ ብዙኃን ባሰራጨው መግለጫ፤ ባልደራስ በሚል የፖለቲካ ፓርቲ ሽፋን ሲንቀሳቀስ የቆየው እስክንድር ነጋ የሐሳብ የበላይነትን በማረጋገጥ ዓላማውን ማሳካት ሲሳነው በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ጊዜያት ሁከትና ብጥብጥ ለመፍጠር ሲሞክር ነበር ብሏል።
እስክንድር ነጋ ይህ እንዳልተሳካለት ሲያውቅ መንግሥትን በኃይል ለመጣል በማቀድ የአማራ ሕዝባዊ ግንባር የተባለ አደረጃጀት በመፍጠር ሽመልስ ስማቸው፣ ሰውመሆን ወረታውና መንበሩ ካሴ ከተባሉ ግብረዓበሮቹ እንዲሁም የክልሉ ጽንፈኛ ኃይሎች ጋር በመቀናጀትና በህቡዕ በመንቀሳቀስ ታጣቂዎችን ሲመለምል፣ ሲያደራጅና ስምሪት ሲሰጥ እንደነበር መግለጫው ጠቁሟል። ግንባሩን በሀገር ውስጥ ራሱ ሲመራ በውጭ ደግሞ ሻለቃ ዳዊት ወ/ጊዮርጊስ የተባለ ግለሰብ ያስተባብራል ያለው መግለጫው፤ ሁለቱ በፈጠሩት ትስስር በክልሉ የትጥቅ ትግል በማድረግ ሕዝቡን ወደማያባራ ጦርነት ለማስገባት ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸውንም የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ማረጋገጡን አመልክቷል።
በምሥራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ኤልያስ ወረዳ የሚገኘውን የሥላሴ ገዳም አስተዳዳሪ የሆኑትን አባ ኤልሳን ለዚህ ሕገወጥ ተግባር ሲጠቀሙ እንደነበር ግብረ ሀይሉ በመግለጫው ጠቁሟል። አስተዳዳሪውም ከሃይማኖቱ አስተምህሮ ውጭ በገዳሙ ውስጥ ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ እንዲደረግ ከመፍቀድ ባሻገር ከሌሎች መነኮሳት ጋር በማበርና የጦር መሣሪያ ጭምር በማንገብ ከጽንፈኛ ቡድኑ አባላት ጋር ተሰማርተው እንደነበርም አስታውቋል።አስ