ዜና፡ የአልፋ ሚዲያ መስራቹ በቃሉ አላምረው በአፋጣኝ ከእስር እንዲፈታ የጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪ ተቋም የሆነው ሲፒጄ ጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 5/2015 ዓ.ም፡- አለም አቀፉ የጋዜጠኞች ተቆርቋሪ ተቋም የሆነው ሲፒጄ የአልፋ ዩቲዩብ ሚዲያ መስራች የሆነው በቃሉ አላምረው በኢትዮጵያ የጸጥታ ሀይሎች አላግባብ መያዙን አስታውቆ በአፋጣኝ እንዲለቀቅ ጠይቋል። ሲፖጄ ነሃሴ 4 ቀን 2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ መንግስት በቃሉ አላምረውን በአፋጣኝ እንዲፈታ እና የፕሬስ ነጻነትን እንዲያስጠብቅ ጠይቋል።

ሐምሌ 30 ቀን 2015 ዓ.ም ሶስት የጸጥታ ሀይል መለያ የለበሱ እና ሁለት የሲቪል ልብስ የለበሱ ፖሊሶች አዲስ አበባ ከሚገኘው ቤቱ አስረው እንደወሰዱት ጉዳዩን ከሚያውቅ እና ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ ሰው ለተቋሙ ባደረሰው መረጃ መረዳቱን አስታውቋል። በተጨማሪም በሀገሪቱ ከሚሰራጩ ነጻ ሚዲያዎች ዘገባዎች መረዳቱን ገልጿል።

የኢትዮጵያ መንግስት በሀገሪቱ ግጭቶች ሲከሰቱ ገለልተኛ ድምጾችን እና ተቺ ጋዜጠኝነትን ማፈን የተለመደ ተግባሩ አድርጎታል ሲሉ የተቋሙ የአፍሪካ አስተባባሪ አንጀላ ኩይንታል መናገራቸውን ያስታወቀው መግለጫው በቃሉ አላምረውን ጨምሮ ሌሎች በዘገባዎቻቸው እና በሰጡት ምልከት ምክንያት በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአፋጣኝ እንዲፈቱ እና በነጻነት ያለመሸማቀቅ እንዲሰሩ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠርላቸው ማሳሰባቸውን አስታውቋል።

በቃሉ በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት አለመቅረቡን እና ስለታሰረበት ምክንያትም እንዳልተነገረው የበቃሉን የእስር ሁኔታ የሚከታተል ሰው መረጃውን ለተቋሙ ማድረሱን መግለጫው አካቷል።

በቃሉ አላምረው ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ በመንግስት ሀይሎች ለእስር መዳረጉን እና ያለምንም የፍርድ ቤት ክስ እዲቆይ ተደርጎ መለቀቁን ሲፒጄ በመግለጫው አስታውሷል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.